Photo- Amhara regional government
ዋዜማ- የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግስት ተቋማት ገንዘብ አንዳይንቀሳቀስ ማገዱን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ችላለች።
የአስቸኴይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ ለቀናት የተጣለው አጠቃላይ የገንዘብ ዝውውርን እገዳ እንዲነሳ ከፈቀደ በኋላ ዳግም በአማራ ክልል የገንዘብ ቢሮ ትዕዛዝ በበርካታ አካባቢዎች እግድ ተጥሏል።
አሁን እገዳ የተጣለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የፋኖ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸው መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በክልሉ መንግሥት ገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥሎ ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት፣ የአማራ ክልል መንግሥት የባንክ ሒሳቦችን እንዳይንቀሳቀሱ ጥሎት የነበረውን ገደብ ማንሳቱን አስታውቆ ነበር።፡፡
የክልሉ መንግሥት ገንዘብ እንቅስቃሴ የክልሉ አስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ አሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) እና ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ/ር) የጋራ ፊርማ ብቻ እንዲንቀሳቀስ ነበር ውሳኔ የተላለፈው፡፡ ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንክ ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በቀረበለት ጥያቄ እገዱን ካነሳ በኋላ፣ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ በተመረጡ አካባቢዎች እገዳ መጣሉን ዋዜማ አረጋግጣለች፡፡
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ እገዳ ከጣለባቸው አካባቢዎች መካከል አዲስ የተመሰረተው ሰሜን ጎጃም ዞን፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃምና ደቡብ ጎንደር ዞን ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው ታግዷል፡፡ በእነዚህ ዞኖች የዞኑ አስተዳደር የባንክ አካውንቶች ጭምር እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡
በከፊል እገዳ ከተጣለባቸው ዞኖች መካከል አንዱ በሆነው ሰሜን ሽዋ ዞን ሚዳ፣ መርሃ ቤቴ፣ ሞረትና ጅሩ፣ ሲያደብር፣ እነዋሪ መንዝ ጌራ፣ መንዝ ቀያ፣ መንዝ ማማ፣ መሀል ሜዳ፣ ሞላሌ፣ ግሼ ራቤል ወረዳዎችና አለም ከተማ ይገኙበታል፡፡
ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ፣ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጣቁሳ፣ አለፋ፣ ምዕራብ ደንቢ፣ ምስራቅ ደንቢ ወረዳዎች፣ ከደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ፣ ከላላ፣ መካነ ሰላምና ቦረና ወረዳዎች፣ አዊ ብሔሰረብ ዞን ቲሊሊ ከተማ አስተዳደር፣ ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ እግድ ከተጣለባቸው መካከል ናቸው፡፡
እገዳው የተጣለው በአንዳንድ አካባቢዎች የቼክ እና ደረሰኝ መጥፋት አጋጥሟል የሚል ሪፖርት ከዞኖች መቅረቡን ተከትሎ፣ ጉዳዩን ለማጣራት እገዳ መጣል በማስፈለጉ የተወሰነ መሆኑን የክልሉ ገንዘብ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አለምነህ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደነገሩን ከሆነ የተጣለው የገንዘብ እንቅስቃሴ ገድብ መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች ተጣርተው እንደተጠናቀቁ እንደሚለቀቅ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ የማጣራት ሥራው ምን ያክል ጊዜ እንደሚወስድና እግዱ የሚነሳበት ቁርጥ ያለ ቀን አለመኖሩን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት የገንዘብ እንቅስቃሴ ገደብ የተጣለባቸው አብዛኛዎቹ አካባቢዎች መከላከያ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ያልተቆጣጠራቸውና የፋኖ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ተረድታለች፡፡
የፋኖ ታጣዊዎች የተቆጣጠሯቸውና መከላከያ ያልገባባቸው አንዳንድ ወረዳዎችና ከተሞች ላይ የመንግሥት አገልግሎት ተቋርጦ፣ የባንክ አገለግሎት እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ መኖሩ ታውቋል፡፡ በአንጻሩ የፋኖ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸውና የመንግሥት መደበኛ አግልግሎት የቀጠለባቸው ወረዳዎች አሉ፡፡
የገንዘብ እንቅስቃሴ ገደቡ የመንግሥት ሥራዎች እንዲቆሙ እና የመንግሥት ሰራተኛው የደመወዝ መቋረጥ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው እግድ የተጣለባቸው ወረዳዎች ገንዘብ ጽ/ቤት ግጭቱ መስፋፋቱን ተከትሎ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን ውጪ መገደባቸውን ዋዜማ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡
ዋዜማ መረጃ ካሰባሰበችባቸው ወረዳዎቸ መካከል በሰሜን ሽዋ ዞን የሚገኘው ግሼ ራቤል ወረዳ አንዱ ሲሆን፣ በወረዳው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ሺሕ ብር፣ አባይ ባንክ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ለደንበኞቻቸው እንደማይሰጡ ሰምታለች፡፡
ምንም እንኳን የገንዘብ ወጪ ገደቡ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም፣ ባንኮች ብር እንደሌላቸው በመግለጽ ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን ዕለታዊ ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ ነው፡፡ በተፈጠረው አለመረጋጋት ማኅበረሰቡ የገንዘብ እንቅስቃሴ ይገደባል የሚል ስጋት ስላደረበት ወደ ባንኮች የሚገባ ብር አምብዛም መሆኑ ታውቋል። [ዋዜማ]