ዋዜማ- በአማራ ክልል ከባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በኹሉም የጎጃም ዞኖች መንገዶች መዘጋታቸውን ዋዜማ ሰምታለች። ይህን ተከትሎ በጎጃም በኩል ወደ ክልሉ ከአዲስ አበባ የሚገቡ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖችም ከቆሙ ሳምንት ተቆጥሯል።

በምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች የትራንስፖርት እንቅስቃሴው የተቋረጠው፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ላልተወሰነ ጊዜ ጥለውታል በተባለ የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት መሆኑንም ሰምተናል። 

  የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከቆመበት ጊዜ ወዲህ በጎጃም በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በመንግሥት ወታደሮች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉት ውጊያዎች እንደ አዲስ አገርሽተዋል።  በምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረማርቆስ ዕሁድ ዕኩለ ሌሊት ላይ ለአጭር ጊዜ የቆየ ተኩስ ድምጽ ከተሰማ በኋላ፣ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ኹሉም ዓይነት እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

  የከተማዋ የትራፊክ ፖሊሶች እንቅስቃሴ ያቆሙ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ታርጋ ሲፈቱ እንደነበርም ነዋሪዎች ነግረውናል። ሳምንቱን ከአዲስ አበባም ሆነ ወደሌሎች አካባቢዎች የሚደረገው እንቅስቃሴ መቆሙን ተከትሎ፣ የቤንዚን ዋጋ በመደበኛ ይሸጥበት ከነበረበት በሊትር 82 ብር ገደማ፣ ከሰሞኑ ወደ 150 ብር ከፍ ብሏልም ተብሏል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉትም በሸቀጦች ዋጋ ላይም ጭማሪ ታይቷል። 

  በጎንደር ከተማም እንዲሁ፣ ነዋሪዎቹ በኹለቱ ኃይሎች መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል። በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ያለፉትን ሁለት ቀናት ሥራ አቁመው መዋላቸውን ተረድተናል።

ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እስከ ማክሰኞ(ነሓሴ 14/2016ዓ.ም.) ድረስ ከጎንደር ወደ ባህር ዳር የሚደረግ ምንም ዓይነት የመኪና ጉዞ አለመኖሩንም ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።   

በተመሳሳይ ከትናንት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ የሚደረጉ ጉዞዎችም ተቋርጠዋል። ከደብረብርሃን ወደ ደሴ እንዲሁም ከደሴ ወደ ወልዲያ የሚሄዱ መኪኖች አለመኖራቸውን ዋዜማ ከነዋሪዎች አረጋግጣለች።

በአካባቢዎች የወረዳ ከተሞችን የሚያገናኙ መንገዶች ከትናንት ጀምሮ ብዙዎቹ ተዘግተዋል። 

በክልሉ በብዙ ቦታዎች ትናንሽ የወረዳ ከተሞችን ጨምሮ የዞን ከተሞች በመንግሥት ወታደሮች እጅ ሲሆኑ፣ ከከተማ ወጣ ያሉ ቀበሌዎች ደግሞ በታጣቂዎች የተያዙ እንደሆነም ዋዜማ ተገንዝባለች። 

በአንጻሩ ካለፈው ዐርብ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ተቋርጦ የሰነበተው የባህር ዳር ከተማ እንቅስቃሴ ከትናንት ከሰዓት በኋላ ተመልሷል። 

ሆኖም ከባለፈ ዐርብ ጀምሮ እስከዛሬ ዕለት ድረስ ከባህር ዳር ከተማ የሚወጡም ሆነ ወደ ከተማ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የሉም።  

በየጊዜው በሚፈጠር የመንገድ መዘጋት ምክንያት ጤና ተቋማት የግብዓት ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ በተለይ ወደ ጤና ተቋም ሄደው የሚወልዱ እናቶች ፈተና ሆኖባቸዋል።

ዋዜማ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ባደረገችው ማጣራት ከቅርብ ቀናት ወዲህ የሸቀጦች ዋጋ ከፍ ያለ ጭማሪ አሳይቷል። በብዙ ከተሞች የሚገኙ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችም ነዳጅ የሚያገኙት ዋጋ ጨምረው ከጥቁር ገበያው ነው። 

በክልሉ ለ10 ወራት ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ካበቃ በኋላ ለተጨማሪ ወራት ባይራዘምም፣ በክልሉ አሁንም የምሽት ሰዓት ዕላፊ ገደብ አለመነሳቱን ዋዜማ ተረድታለች። [ዋዜማ]