ዋዜማ- የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ ተገንጥሎ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክህነት በሚል የተቋቋመው መንበረ ሰላማ በራያ አካባቢዎች መዋቅሩን እየተከለ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። 

ዋዜማ በአካባቢው ካሉ የእምነቱ ተከታዮች እና የኃይማኖቱ መምህራን ባገኘችው መረጃ፣ የማንነት ጥያቄ በሚነሳባቸው እና በትግራይ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ባሉ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ በርከት ያሉ ቤተክርስትያናት በመንበረ ሰላማ መዋቅር ውስጥ ገብተዋል። 

በተለይ የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች ያሉ አብዛኞቹ አብያተክርስትያናት በመንበረ ሰላማ መዋቅር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ጉዳዩን አንቀበልም ያሉ ካህናት ወደ አላማጣ መጥተው በከተማው ነዋሪ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚኖሩ ሰምተናል። 

ይህን ተከትሎም ነባር የቤተክርስትያን ሰበካ ጉባኤ እንዲፈርስ ተደርጎ አዲስ ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስም የተቀረጹ ማህተሞችም እንዲቀየሩ ተደርጓል። 

በመንበረ ሰላማ ስር ካሉ አህጉረ ስብከቶች አንዱ ለሆነው እና መቀመጫውን ማይጨው ላደረገው የደቡብ ትግራይ አህጉረስብከት ገቢ እንዲከፍሉ የተደረጉ የገጠር አብያተ ክርስትያናት መኖራቸውንም ሰምተናል። 

መንበረ ሰላማ መዋቅሩን ከዘረጋባቸው የገጠር አብያተ ክርስትያናት መካከል ቀድሞ ከነበረው ሰባካ ጉባኤ ጋር ርክክብ አድርገው የራሳቸውን የፋይናንስ አስተዳደር ያደራጁ መኖራቸውም ታውቋል። 

ሆኖም የማንነት ጥያቄ በሚነሳባቸው የራያ አካባቢዎች መዋቅሩን እየተከለ ያለው መንበረ ሰላማ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድም ተቃውሞ አጋጥሞታል። 

ነዋሪዎች እንዳሉት፣ መንበረ ሰላማን አንቀበልም ባሉ አካባቢዎች በመንበሩ የተመደቡ ካህናት በታጣቂዎች ታጅበው ነው አገልግሎት እየሰጡ ያለው። 

በከተሞች ግን እስካሁን መንበረ ሰላማ መዋቅሩን አልዘረጋም። ለአብነትም ከሳምንት በፊት አላማጣ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን በመንበረ ሰላማ እና በአካባቢው ምዕመናን መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። 

መንበረ ሰላማ ቤተክርስትያኑን ተረክቦ በራሱ መዋቅር ለማስተዳደር ሲሞክር ከአካባቢው ማህበረሰብ ይህን አንቀበልም ያሉ ደግሞ አካባቢውን ለሚያስተዳድረው ኮማንድ ፖስት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም የመንበረ ሰላማን እንቅስቃሴ የተቃወሙ የዕምነቱ ተወካዮች ቅሬታቸውን ለኮማንድ ፖስቱ ማቅረባችውን ተረድተናል። 

ይሁን እንጂ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች እና የዕምነቱ አስተማሪዎች የኮማንድ ፖስቱ መሪዎች በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አንገባም በማለት አቤቱታችንን አልተቀበሉም የሚል ቅሬታ አቅርበዋል። 

አክለውም በኃይል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ተነጠሉ በሚል የእምነት ነጻነታችንን እያጣን ነው ብለዋል። 

መንበረ ሰላማ በከተሞች በሚገኙ አብያተ ቤተክርስትያናት መዋቅሩን መዘርጋት ያልቻለው ከእምነቱ ተከታዮች በገጠውመው ከፍ ያለ ተቃውሞ ቢሆንም፣ ጥረቱን ግን አላቋረጠም። 

የማህበረሰቡ የተቃውሞ መነሻ 5 ኪሎ በሚገኘው ሲኖዶስ የተላለፈበት ውግዘት ሳይፈታ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጋር በኃይማኖት ይዘት ልዩነት አለኝ በሚል “መንበር አንገለገልም” የሚል መሆኑን ዋዜማ ተገንዝባለች።  

ከሰሜኑ ጦርነት በፊት፣ አሁን ላይ የማንነት ጥያቄ በሚነሳባቸው ስድስቱ የራያ ወረዳዎች የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት በደቡብ ትግራይ አህጉረስብከት ስር ይተዳደሩ ነበር።  

ከሰሜኑ ጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ራሱን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ነጥሎ መንበረ ሰላማ የተሰኘ መንበር መቋቋሙን ተከትሎ፣ በእነዚህ ወረዳዎች የሚገኙ አብያተክርስትያናት ከቀድሞው አህጉረስብከት እንዲነጠሉ 5 ኪሎ ለሚገኘው ሲኖዶስ ጥያቄ በማቅረባቸው የራያ አህጉረስብከት በሚል አዲስ አደረጃጃት ተሰጣቸው። [ዋዜማ]

ሆኖም አሁን ላይ በገጠር ወረዳዎች ባሉ የእምነቱ ተቋማት መዋቅሩን እያሰፋ ያለው መንበረ ሰላማ፣ አብያተ ክርስትያናቱ ወደቀድሞው አስተዳደር ማለትም ወደ ደቡብ ትግራይ አህጉረስብከት እንዲመለሱ እየሰራ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። 

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጠቅላይ ቤተክህነት ኃላፊዎችን የጠየቀች ሲሆን፣ ዘገባው እየተጠናቀረ ባለበት ወቅት ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ አሳውቀዋል።  

በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከት ሊቃነጳጳሳት በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ በነበረው የቤተክርስትያኗ የአስተዳደር ክፍተት የተነሳ መንበረ ሰላማ የሚባል መንበር እንዲሁም የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስታይን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ ጽህፈት ቤት የተሰኘ መዋቅር ከአንድ ዓመት በፊት መስርተዋል። 

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ ለትግራይ ቤትክህነት እና ለመንበረ ሰላማ፣ እንዲሁም አዲስ ለተሾሙት ጳጳሳት እውቅና እንደማይሰጥ ገልጾ፣ እንቅስቃሴውን ሲመሩ በነበሩት ጳጳሳት ላይ ውግዘት ማስተላለፉ ይታወሳል። [ዋዜማ]