Commercial Bank of Ethiopia

ዋዜማ ራዲዮ- በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ሂሳብ ከፍተው ከጦርነቱ በኋላ ሂሳባቸው የታገደባቸው ደንበኞች አሁን እገዳው እንደተንሳላቸውና ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ መፈቀዱን ዋዜማ ራዲዮ ስምታለች።


አንድ ዓመት ሊሆነው የተቃረበው ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የባንክ አገልግሎት ሲቋረጥ በትግራይ ክልል የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች እንደይንቀሳቀሱ አብረው መታገዳቸው ይታወሳል። ለእገዳው ምክንያት የነበረው ከፀጥታ ስጋት ጋር የተያያዘ የገንዘብ ዝውውርን መግታት ነበር።


አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የስራ ሀላፊ እንደነገሩን ትግራይ ክልል ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞቹ የታገደባቸውን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ ከፈለጉ አቅራቢያቸው ባለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ቀርበው የታገደባቸውን ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንዲፈቀድላቸው የሚጠይቅ ማመልከቻ በመጻፍና ከማመልከቻው ጋርም ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያን እንዲሁም የሂሳብ ደብተራቸውን በማያያዝ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይችላሉ ።ባንኩም አስፈላጊውን ማጣሪያ አድርጎ ደንበኞቹ ሂሳባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ያደርጋል ።


ትግራይ ክልል ተከፍተው በጦርነቱ ሳቢያ መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሂሳቦችን እንዲንቀሳቀሱ የማድረጉን ስራ ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጭ ሁሉም የግል ንግድ ባንኮች ስለመጀመራቸው ዋዜማ ራዲዮ ማረጋገጥ አልቻለችም። ያነጋገርናቸው የአንድ የግል ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው ነግረውናል።


በፌዴራል መንግስትና በህወሀት መካከል የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ባንኮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በክልሉ ባሉ የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሂሳቦች መታገዳቸው በርካቶችን ለችግር ዳርጓል።በትምህርትም ሆነ በስራ አጋጣሚ ትግራይ ክልል ኖረው እዛው የባንክ ሂሳብ ከከፈቱ በኋላ መኖርያ እና መስሪያ ቦታቸውን የቀየሩ ግለሰቦች የባንክ ሂሳባቸው መታገዱ ያላቸውን ገንዘብም ሆነ የወር ደሞዛቸውን ሳይቀር ማንቀሳቀስ አቅቷቸው ተቸግረዋል። ብዙዎችም ገንዘብን ለማንቀሳቀስ ሌላ የባንክ ሂሳብ ማውጣትንም እንደ አማራጭ ወስደዋል።


የፌዴራል መንግስት ጦር ክልሉን ለቆ ከወጣ በሁዋላ ክልሉን በጊዜያዊነት ሲያስተዳድሩ በነበሩ ሰራተኞች የተጻፉ ቼኮች እንዳይመነዘሩ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትእዛዝ መሰጠቱም ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]