ዋዜማበትግራይ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በጦርነትና ድርቅ ሳቢያ  ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ዋዜማ ከየክልሎቹ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።

ትግራይ

ከጦርነቱ በኋላበትግራይ ክልል ብቻ እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመመለሳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዋዜማ ገልጧል። 

ቢሮው ከጦርነቱ በፊት (2012 ዓ.ም) 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እንደነበር ጠቅሶ፣ በዘንድሮው ዓመት ከዚህ ቀደም ያቋረጡትን እና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱትን ጨምሮ፣ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ተማሪዎች በትምህርት ላይ ይገኛሉ የሚል ዕቅድ እንደነበረው ገልጿል። ሆኖም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ረዳኢ ገብረእግዚአብሔር ለዋዜማ እንደነገሯት፣ በ2016 የትምህርት ዘመን የተመዘገቡት ጠቅላላ ተማሪዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን በታች ነው። ከተመዘገቡት መካከልም ድርቅ ባስከተለው ርሃብ ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፈው የካቲት ወር ብቻ ከ20 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ማቋረጣቸውን ገልጸዋል። 

በ57 ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተደረገ ዳሰሳም፣ በ625 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ223 ሺሕ በላይ ለሚሆኑት ተማሪዎች አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት (ምገባ) ካልተከናወነ በስተቀር ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው አይቀሬ ነው ብለዋል። 

ከመጭው መስከረም ወር በፊት እህል ስለማይደርስ እየተባባሰ በሚሄደው ርሃብ እና ድርቅ የተነሳ ትምህርታቸውን የማይጨርሱ ታዳጊዎች ቁጥር አሁን ካለበትም በላይ ይጨምራል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 

በተስፋ መቁረጥ፣ ርሃብ እና መፈናቀል ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ያልፈለጉ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች፣ በስደት፣ በልመና እና ሌሎች ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። የክልሉን ተማሪዎች በ2018 ዓ.ም ከአገር አቀፍ የትምህርት መርሃግብር ጋር አቻ ለማድረግም፣ ድርብርብ የትምህርት መርሃግብር (accelerated learning program) በሚል አሰራር አንድ ዓመት የተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በወራት እንዲያልቅ እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል።

 ኃላፊው የተለየ ድጋፍ ካልተደረገ በስተቀር በመደበኛ ድጋፍ ያለውን ችግር መቅረፍ እንደማይቻል ገልጸው፣ 105 ትምህርት ቤቶች አሁንም የተፈናቃዮች መጠለያ መሆናቸውን አመልከተዋል። 

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ትምህርት እስከተጀመረበት ጊዜ ያሉትን 17 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው መምህራን አሁንም አብዛኞች በሥራቸው ደስተኞች አለመሆናቸውንም አንስተዋል። 

ከጦርነቱ መጀመር በፊት ከ45 ሺሕ በላይ መምህራን ነበሩን የሚሉት ኃላፊው፣ በሞት፣ በአካል ጉዳት እና በስደት እንዲሁም ሥራ በመቀየራቸው ምክንያት 15 ሺሕ ገደማ የመምህር እጥረት መኖሩን ነግረውናል። 

ኃላፊው እንደሚሉት 88 በመቶ የክልሉ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወድመዋል። ክልሉ ወደ ሰላም ከተመለሰ በኋላም የተጎዱት የትምህርት ተቋማትን ከመጠገን ይልቅ ለትምህርት ማህበረሰቡ የስነልቦና ድጋፍ ማድረግን በመምረጡ እስካሁን የተጠገኑ ትምህርት ቤቶች አሉ ማለት አይቻልም ብለዋል።

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ በተለያዩ አካባቢዎች በሚስተዋሉት የጸጥታ ችግሮች የተነሳ፣ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎች አሉ። 

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አማካሪ ኤፍሬም ተሰማ፣ በክልሉ የሚስተዋሉት የጸጥታ ችግሮች ሰው የሚያወራውን ያህል ተጽዕኖ አለመፍጠሩን ለዋዜማ ተናግረዋል። በክልሉ 10 ዞኖች፣ በ420 ገደማ ትምህርት ቤቶች አልፎ አልፎ የመስተጓጎል ችግር እንዳጋጠማቸው ጠቅሰው፣  በዘንድሮው ዓመት 131 ሺሕ 338 ተማሪዎች ከአንድ ሳምንት እስከ ወር የሚያስቆጥር የትምህርት መቆራረጥ ብቻ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል። 

በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ግን በቅርቡ ለዋዜማ በሰጠው መረጃ፣ በዘንድሮው የትምህርት ዓመት ከ47 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ሲሆኑ፣ 212 የአንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከቀላል እስከ ከባድ ውድመት ደርሶባቸዋል ብሏል። 

ዞኑ ከ7 በማያንሱ ወረዳዎች የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን የጸጥታ ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሆነበትም ለዋዜማ ገልጿል። ሆኖም በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በ31 ሺሕ የአንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አማካሪው ኤፍሬም ተሰማ ነግረውናል።

አማራ

በአማራ ክልልም አሁንም ድረስ በቀጠለው ግጭት ምክንያት፣ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ቤት አለመመለሳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በቅርቡ አሳውቋል። 

ቢሮው 300 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች በግጭቱ ምክንያት መውደማቸውን የገለጸ ሲሆን፣ 3 ሺሕ 500 የአንደኛ እና 225 የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ እስከ አመቱ አጋማሽ ድረስ ዝግ መሆናቸውን ጠቁሟል። 

ትምህርት ቤቶች የታጣቂዎች ምሽግ በመሆን ንብረታቸው መዘረፉን ያነሳው ቢሮው፣ ትምህርት ወደተጀመረባቸው ቦታዎች ግብዓቶችን ማድረስም አስቸጋሪ ሆኗል ብሏል። እየተማሩ ያሉትም የተኩስ ድምጽ እየሰሙ ትምህርታቸውን ባግባቡ መከታተል እንዳልቻሉ ጠቅሶ፣ በተለይ በጎጃምና በሸዋ አካባቢዎች ችግሩ ሰፊ መሆኑን አመልክቷል። 

በሰሜን ሸዋ ዞን ከ210 ሺሕ በላይ ተማሪዎች፣ እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም ዞን ከግማሽ በላይ ተማሪዎች የዘንድሮ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አለመሆኑም ታውቋል።

በትውልድ ላይ የመጣ አደጋ

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የቀጠሉት ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA)፣ ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ባወጣው አንድ ሪፖርት፣ በመላ አገሪቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። ይህም ማለት ከ16 ተማሪዎች አንዱ ትምህርት ያቋረጠ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው የትምህርት ቀውስ በዓለም ላይ ቀዳሚው መሆኑንም አመልክቷል። 

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት መራቃቸውንም አመልክቷል። በማስተባበሪያ ቢሮው ጥናት እስከ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ድረስ በመላ አገሪቱ 8 ሺሕ 500 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የወደሙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1 ሺሕ 500 ያህሉ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው። ቢሮው ጦርነቱን ተከትሎ ከ22 ሺሕ በላይ መምህራ ከአንድ ዓመት በላይ ደሞዝ ክፍያ ተቋርጦባቸው ከመቆየታቸው ባለፈ፣ ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አብዛኞቹ እስካሁን ጥገና እንዳልተደረገላቸው በሪፖርቱ ጠቅሷል። 

ወደ ትምህርት ቤታቸው የማይመለሱ ታዳጊዎች፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለወሲብ ጥቃት እንዲሁም ለስደትና ለ ካለእድሜ ጋብቻ እንደሚጋለጡም ይታመናል። 

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩንቨርሲቲ የሥርዓተ-ትምህርት አስተማሪ የሆኑት አማኑኤል ኤሬሞ (ዶ/ር)፣ ትምህርት ማግኘት የዜጎች መብት መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ላይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ዜጎች የመማር መብታቸውን አጥተው ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን እያዬን ነው ሲሉ ለዋዜማ ነግረዋታል። 

የመማሪያ መጽሐፍት እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ህንጻ መቃጠልና መውደም፣ የመምህራን ደሞዝ በወቅቱ አለመከፈል እንዲሁም የመማሪያ ቦታዎች በስጋትና ጭንቀት የተሞሉ መሆን፣ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ በብዙ ቦታዎች እያጋጠመ ያለ ሰፊ ችግር መሆኑንም አውስተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ችግሩ በቶሎ መፍትሄ አግኝቶ ተማሪዎችም በአጭር ጊዜ ውጤታማ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደማይኖርም አማኑኤል  ገልጸዋል። 

የትምህርቱ ጥራት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል የሚሉት መምህሩ፣ በተከታታይ ዓመታት ሦስት በመቶ ተማሪዎችን ወደ ዩንቨርሲቲ እያሳለፍን ጉዳዩን አጀንዳ ለማድረግም ያስቸግራል ብለዋል። 

ከትምህርት ጥራት በፊት መቅደም ያለባቸው የትምህርት ተደራሽነት እና ፍትሃዊነት አደጋ ውስጥ መግባታቸውንም አመልክተዋል። መምህሩ አሁን በአገራችን በብዙ ቦታዎች የሚስተዋለው በትውልድ ላይ እየመጣ ያለውን አደጋ የሚያሳይ ነው ብለዋል። [ዋዜማ]