ዋዜማ- መንግስታዊው የፖሊሲ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጊዜያዊት ብድር መልቀቅ ማቆሙን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች ።

ንግድ ባንኩ ብድር ለማግኘት የተለያዩ ሂደቶችን አልፈው ፤ ብድሩ ተፈቅዶላቸው የመልቀቅ ሂደት ላይ ያሉትም እንዲቆም ነው ያዘዘው ። ባንኩ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፈው ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ/ም መሆኑንም ሰምተናል ።

ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነ ፤ ንግድ ባንኩ በጊዜያዊነት ብድር መልቀቅ ከማቆሙ በስተቀር ባስተላለፈው ትእዛዝ ላይ ብድር መልቀቅ ያቆመበትን ምክንያት አልገለጸም። ሆኖም ከብድር መልቀቅ መለስ ያሉት የብደር ጥያቄ እና ሂደቶቹ አለመቆማቸውን ሰምተናል ።

መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ የሰጠው ብድርም ሆነ የሰበሰበው ቁጠባ ከአንድ ትሪሊየን ብር ያለፈ ብቸኛ ባንክ መሆኑ የሚታወቅ ነው ።

ባንኩ በቅርቡ በተገበረው የሲስተም ማሻሻያ ሳቢያ በተፈጠረ ስህተት 801 ሚሊየን ብር ለምዝበራ ተዳርጎበት እንደነበረ እና ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ገንዘብ ባደረገው ክትትል ማስመለሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር ። ባንኩ ገንዘቡን የማስመለስ አካል ነው ያለውን ባልተገባ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ተሳትፈዋል ያላቸውን ደንበኞች ፎቶ ሳይቀር ለህዝብ ይፋ አድርጓል ። አሁን በጊዜያዊነት ብድር መልቀቅ ማቆሙ ከዚህ ጋር ይገናኝ አይገናኝ ለማድረግ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አመት ብቻ 151 ቢሊየን ብር ብድር የሰጠ ሲሆን ፤ በተመሳሳይ አመት 165 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ቁጠባን ደግሞ ሰብስቦም ነበር ።ሆኖም ይህ በጀት አመት ከገባ ግን የቁጠባ አሰባሰቡ ከእቅዱ ጋር እየሄደ አለመሆኑ ተሰምቷል ። ለአብነትም በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት የሰበሰበው ቁጠባ ከእቅዱ አንጻር ከግማሽ በታች መሆኑም ተዘግቧል ። ለዚህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው ችግር እንደ ምክንያት ተጠቅሷል ። ምናልባትም የአሁኑ የባንኩ በጊዜያዊነት ብድር የማቆም ውሳኔ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረ የገንዘብ እጥረት ጋር ሊገናኝ አንደሚችል ምንጮቻችን ገልጸዋል ። [ዋዜማ]