ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል አዲስ በተዋቀረው ሸገር ከተማ መነ አቢቹና ሱሉልታ ክፍላተ ከተሞች፣ ለኮሪደር ልማት ተብሎ ከአስፋልት ዳር ግራና ቀኝ ያሉ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ያለምንም ካሳና ተለዋጭ እየፈረሱ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀናል ሲሉ ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።

ለኮሪደር ልማቱ ትነሳላችሁ የተባሉት እነዚሁ ነዋሪዎች በሦስት ወረዳዎች ማለትም፣ በቱፋ ሙና፣ ወሰርቢና አባገዳ ወረዳ ነዋሪ እንደሆኑ ዋዜማ ያሰባሰበቻቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ተነሺዎቹ ምንም አይነት ተለዋጭ መሬትና የቤት መስሪያ ገንዘብ እንዳልተሰጣቸው እንዲሁም ካሳም እንዳላገኙ ለዋዜማ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት የክፍላተ ከተሞቹ ሰራተኞችና የጸጥታ ኃይሎች ምንም አይነት ቅድመ ማስጠንቀቅያ ሳይነግሯቸው ግቢያቸው አጥር ላይ የሚፈርሰውን ቤት እና አጥር መጠን በሜትር ምን ያህል እንደሆነ ሲጽፉ እንደነበር ተናግረዋል።

ከአስር ኪሎ አካባቢ የሚጀምረው የኮሪደር ልማት ፈረሳ፣ መጨረሻው ሱሉልታ ክፍለ ከተማ መውጫ በተለምዶ ቆዳ ፋብሪካ ተብሎ እስከሚጠራው ቦታ ድረስ እንደሆነ የገለጹት ነዋሪዎቹ አጠቃላይ ርዝመቱም ሃያ ኪሎ ሜትር አካባቢ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለልማቱ ይነሳሉ የተባሉት ቤቶች አብዛኞቹ ሕጋዊ ካርታና ሰነድ ያላቸው፣ ለመንግሥትም አስፈላጊውን ግብር ሲከፍሉ የነበሩ፣ የንግድ ቤቶቹም በሕጋዊ መንገድ ሲሰሩ የነበሩ ያስረዳሉ ።

ነዋሪዎቹ የመኖሪያ ቤቶቹን ከሰባት እስከ አስር ዓመታት የኖሩባቸው እንደሆነና ምንም አይነት ካሳና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው አፍርሳችሁ ውጡ በመባላቸው ቤተሰብ ይዘን የት እንወድቃለን በማለት ከፍተኛ ጭንቀትና ግራ መጋባት ውስጥ እንደገቡ ይናገራሉ።

በተለይም የንግድ ቤቶቹ አብዛኞቹ በቅርቡ የንግድ ፈቃድ ያደሱ ግብር የከፈሉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን በዚሁ ቅጽበት አፍርሳችሁ ልቀቁ መባላቸው እንዳሳዘናቸው አስረድተዋል።

የንግድ ቤቶችን ራሳቸው ነጋዴዎቹ አፍርሰው መሬቱን እንዲያስረክቡ በጸጥታ ኃይሎች መታዘዛቸውን ጠቁመዋል።

ሕንጻዎች እና ሌሎች የመኖሪያ ቤቶች ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስና ሚሊሻ ባሉበት በቡል ዶዘር እየፈረሱ እንዳሉ ዋዜማ መረዳት ችላለች።

እየፈረሱ ካሉ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች፣ ባንኮች፣ በቅርቡ የግንባታ ፈቃድ ወስደው እየተገነቡ ያሉ ሕንጻዎች እንዲሁም ከሳምንታት በፊት ተመርቀው ሥራ የጀመሩ ሆቴሎች እንደሚገኙበት ዋዜማ ሰምታለች።

የከተማ አሥተዳደሩ በቅርቡ በጉዳዩ ዙሪያ ነዋሪዎችን ለማወያየት በሸገር ከተማ ወሰርቢ ወረዳ በሚገኘው ኃይሌ ሪዞርት ስብሰባ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም ስብሰባው ባለመስማማት መበተኑን ተከትሎ ፈረሳው በኃይል መጀመሩን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በቀሪዎቹ የሸገር ክፍላተ ከተሞችም ሰሞኑን መሰል እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የጠቆሙት የዋዜማ ምንጮች በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደሚስተዋል አውስተዋል።

ከሰሞኑ ደግሞ የገጠር የኮሪደር ልማት በሚል በክፍለ ሀገራት አነስተኛ ከተሞችን መሰል የማፍረስ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ዋዜማ ሰምታለች።

በተለይም በኦሮሚያ ክልል የዞንና የወረዳ እንዲሁም አነስተኛ የገጠር ከተሞችን በዘመቻ የማፍረስ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑ ዋዜማ ከየአካባቢው የደረሳት መረጃ ያመለክታል።

ከዋናው አስፋልት መንገድ ጋርና ዳር ያሉ ቤቶች በግራና በቀኝ 15 ሜትር መስፋት አለባቸው ተብሎ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቤቶች ያለምንም ካሳና ተለዋጭ ቦታ እየፈረሱ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች።

ለአብነትም አዲስ ከተዋቀረው ሸገር ከተማ አንስቶ የአማራ ክልል አዋሳኝ እስከሆነው ፍልቅልቅ ድረስ ቤቶች የገጠር ኮሪደር ልማት ለተባለው ፕሮጀክት እየፈረሱ መሆኑ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአንድ መድረክ ላይ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየርና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የገጠር የኮሪደር ልማት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ሥራ መገባቱን መናገራቸው ይታወሳል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የሸገር ከተማ አሥተዳደርንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረገችው ጥረት ባለመሳካቱ ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። [ዋዜማ]