በሚድሮክ ወርቅ በብክለት ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉና ምስላቸው ሲዘዋወር የነበሩትን ሰዎች መርማሪ ቡድኑ ሊያገኛቸው አልቻለም
በለገደንቢ ብክለት አስከተሏል የተባለውን ኬሚካል ለትግራይ ክልል ኩባንያ እንዲያበድር ሚድሮክ በመንግስት ተጠይቋል

ዋዜማ ራዲዮ- ትውልደ ኢትዮጵያዊውና ሼክ መሀመድ አላሙዲን  ከእስር ከተለቀቁ በሁዋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ካላቸው ኢንቨስትመንት እንዳልሆነ ሆኖ የሚያገኙት የሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ነው። ኢትዮጵያ በዚህ በጀት አመት ስድስት ወራት የተለያዩ ማእድናትን ለውጭ ገበያ አቅርባ ያገኘችው የእቅዷን አምስት በመቶ መሆኑን ይህም ፣ ከ30 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብዙም ያልበለጠ ፣ በብዙ መለኪያም አጅግ ዝቅተኛ ነው። ለዚህ ማሽቆልቆል ደግሞ የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን የማምረቻ ፍቃድ ባለፈው አመት መታገዱን ተከትሎ የተከሰተ ነው። ሚድሮክ ወርቅ ስራ ላይ በነበረባቸው ወቅቶች በአመት እስከ 200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለኢትዮጵያ ያስገኝ እንደነበር መንግስት ራሱ በተደጋጋሚ ሲናገር ተሰምቷል። 

ባለፈው አመት ሜድሮክ ወርቅ ለአስር አመታት ወርቅ እንዲመያርት የሚያስችለው ፍቃድ በማዕድን ነዳጅና የተፈረጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከታደሰለት በሁዋላ አካባቢን በክሏል ተብሎ በተነሳ ተደጋጋሚ ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስት ላይ ተጽእኖ በመድረሱ የወቅቱ የ ማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከግንቦት 1 ቀን 2010 አ.ም ጀምሮ የአካባቢ በካይነት ሁኔታው በገለልተኛ አካል እስኪጠና ድረስ ሜድሮክ ወርቅ ፍቃዱ ታግዶ ምርት እንዲያቆም ይደረጋል። ኩባንያው ስራ ካቆመ ዘጠኝ ወር ሆኖታል።

     ሜድርክ ኩባንያ ወርቅ ለማንጠር የሚጠቀምበት ኬሚካል አካባቢን በክሏል ተብሎ ቢዘጋም ኩባንያው ደግሞ የተነሳብኝ ተቃውሞ እና የተወሰደብኝ እርምጃ ፖለቲካዊ ነው ሲል ይከራከራል።

ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰበችው  ማስረጃ ለሚድሮክ መዘጋት ዋና ሰበቡ የአካባቢ ብክለት ነው የሚለውን ክስ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። ለአብነትም በኦሮምያ በሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ አደገኛ የተባለውን ኬሚካል ሚድሮክ ለትግራይ ክልል እንዲያበድር መንግስት ራሱ አማላጅ ሆኖ ጠይቆታል።

የአሁኑ ማዕድን ሚኒስቴር ሜድሮክ ለወርቅ ማንጠሪያነት የሚጠቀምበትን ሶዲየም ሳናይድ የተሰኘውን ኬሚካል ትግራይ ላለው ወርቅ አምራች ኢዛና ማዕድን ልማት ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በብድር መልክ እንዲሰጠው መጠየቁን የሚያሳይ ደብዳቤ አግኝተናል። ሜድሮክ ምርት እያመረተ ስላልሆነ ለወርቅ ምርት የሚያስፈልገውን ሶዲየም ሳናይድ የተባለውን የወርቅ ማንጠሪያ ኬሚካል ካለው ክምችት ውስጥ 40 ቶን ሶዲየም ሳናይድ ለኢዛና መአድን በብድር መልክ እንዲሰጠው ነው የተጠየቀው። ኢዛና ማዕድን በሶዲየም ሳናይድ ኬሚካል እጥረት ምክንያት ወርቅ ማምረት አቁሟል። ለዚህ ነው በመአድን ሚኒስቴር በኩል የብድር ምልጃ ከሜድሮክ የተጠየቀለት።

 እዚህ ጋር የሚነሳው ዋናው ጥያቄ ግን ሜድሮክ የሚጠቀመው ኬሚካል አካባቢ በከለ ከተባለ እንዴት መአድን ሚኒስቴር ኬሚካሉን ለኢዛና መአድን አምራች እንዲሰጠው ጠየቀለት የሚለው ነው። ይህ ማለት ማዕድን ሚኒስቴር ኬሚካሉ ወርቅን ለማምረት ምንም ችግር እንደሌለበት ያምናል ማለት ነው። 

ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ታድያ ከ ማዕድን ሚኒስቴር ለተጻፈለት ደብዳቤ ሲመልስ “በኬሚካል አካባቢ በክለሀል ብላቹ ፍቃዴን ነጥቃችሁ ፣ ይህም ጉዳይ እየተጠና እንደሆነ እያወቃችሁ የኬሚካል ብድር ጠይቃችሁኛል ፣ ያላችሁትን 40 ቶን ኬሚካል ለማበደር ፍቃደኛ ነኝ ፣ ነገር ግን ንብረቴ እገዳ ስላለበት የማጓጓዙን ሀላፊነት ራሳችሁ ውሰዱ”  ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

 እርግጥ ሜድሮክ ጎልድ የማምረት ፍቃዱ የታገደው ሶዲየም ሳናይድን ስለተጠቀመ ሳይሆን ኬሚካሉን የተጠቀመበት መንገድ ጥንቃቄ ስላልተሞላበት ነው የሚል ነገር ሊነሳ ይችላል። ግን እዚህም ጋር ሌላ በባለሙያዎችና አካባቢውን በሚያውቁ የሚነሳ አብይ ጉዳይ አለ።

ጥንቃቄ የጎደለው የኬሚካል አጠቃቀም ከተነሳ ሜድሮክ ወርቅ የሚያመርትበት ኦሮምያ ክልል በአዶ ሻኪሶ ወረዳ ለገደንቢ አካባቢ ሻኪሶ ከተማ አቅራቢያ ሜድሮክ ብቻ ሳይሆን በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ወርቅን በዘመናዊም ሆነ ባህላዊ መንገድ ያመርታሉ። እነዚህ አካላት አደጋን የሚያስከትሉ ኬሚካሎችንም ይጠቀማሉ። 

ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው እዚህ አካባቢ ያሉ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ወርቅን  ለማንጠር ሜርኩሪን ሳይቀር ይጠቀማሉ። ከሶዲየም ሳናይድ አንጻር ሲታይ ሜርኩሪ በከፍተኛ ደረጃ አካባቢ በካይና አደገኛ ነው ። ሶዲየም ሳናይድ በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ውሎ ተረፈው ከሌላ ንጥረ ቁስ ጋር ከተዋሀደ የጎላ ጉዳት እንደማያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሀገር ውስጥ ሲገባም ብሄራዊ ደህንነት መስሪያ ቤትም ክትትል ያደርግበታል። ሜርኩሪ ግን ጭራሽ ወርቅ እንዳይመረትበት፣  በሜርኩሪ የተመረተ ወርቅ ራሱ በፍጹም ለአለም አቀፍ ገበያ እንዳይቀርብ አለማቀፍ ስምምነት አለ። ይህም የሚናማታ ስምምነት (ኮንቬንሽን) ይባላል። ስምምነቱ በተፈረመባት የጃፓን ከተማ የተሰየመ ነው። ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ ነች። ነገር ግን ሜርኩሪ በኮንትሮባንድ እየገባ በስፍራው ለወርቅ ምርት እንደሚውል የታወቀ ነው። 

ከጥቂት ወራት በፊት የተዘጋው እዛው ሜድሮክ ወርቅ አካባቢ ያለው የአዶላ ወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ወርቅን ለማንጠር ሜርኩሪን ይጠቀም እንደነበር በግልጽ ተናግሯል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሜድሮክ ወርቅ በሼክ መሀመድ አላሙዲን ከመገዛቱ  በፊት የለገደንብ ወርቅ ማምረቻ በሚል ስያሜ እያለ ከሀይለ ስላሴ ጀምሮ በፋብሪካው ወርቅ ሲመረት የቆየው በሜርኩሪ ነበር። በዚህም ሳቢያ ስፍራው ለበርካታ አመታት ብክለት ሲያጋጥመው የቆየ ነው። ታድያ እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ እነዚህ ውስብስብ ነገሮች ባሉበት ሁኔታና ወርቅ በአደገኛ ሜርኩሪ በሚነጠርበት አካባቢ ሚድሮክ ብቻ በምን መስፈርት ተለይቶ በበካይነት ፍቃዱ ታገደ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ አካል የለም።

     በአሁኑ ወቅት ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአከባቢ እና በሰው እንዲሁም በእንስሳት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ከአካባቢ ጥበቃ ከማዕድን ሚኒስቴርና ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ጥናትን እያጠና ነው። ቡድኑ መጀመርያ ላይ የገንዘብ እጥረት አጋጥሞት ስራ መስራት ባለመቻሉ የካናዳ መንግስት ባቀረበው የ15 ሚሊየን ብር ድጋፍ ነው ከስድስት ወር ጀምሮ የተጽእኖ ጥናት ግምገማን ማካሄድ የጀመረው። እስካሁንም ጥናቱ አላለቀም። 

በጥናቱ ወቅትም ግን ቡድኑ ችግር እንዳጋጠመው ዋዜማ ራዲዮ አረጋግጣለች። እሱም በሚድሮክ የወርቅ ማምረት ሂደት ምክንያት የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሎ በመገናኛ ብዙሀንና በመብት ተሟጋቾች ምስላቸው ሲቀርቡ ነበሩ ሰዎች አለመገኘታቸው ነው። ለጥናቱ ውጤታማነት ጉዳት ደርሶባቸዋል ከተባሉ ሰዎች የጸጉርን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት አካላት ቅንጣቶች (DNA)ችግሩ የደረሰባቸው በኬሚካል ለመሆኑ ማረጋገጫ ይጠቅማሉ። ነገር ግን የጥናት ቡድኑ እነዚህን ሰዎች ማግኘት አልቻለም። የሚድሮክ ወርቅ ኬሚካል ሰለባ ናቸው የተባሉ ሰዎች መጀመርያ ላይ የቀድሞ የ ማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ስፍራውን ሲጎበኙ ቀርበውላቸው ነበር። የጥናት ኮሚቴው ሲሄድ ግን እነዛው ሰዎች መጥፋታቸው ነገሩን ውስብስብ አድርጎታል።

 የነገሩን ፖለቲካዊ ውስብስብነት የኦሮምያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እንደተረዱትም መረጃ አለን። በሚድሮክ ወርቅ ላይ ሌሎች የጥቅም ፍላጎት እንዳላቸውም ነገሩን ፖለቲካዊ ገጽታ ማላበሱም የመነጨው ከዚህ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ።እርግጥ ሚድሮክ የወርቅ ማምረቻውን ከመንግስት የገዛበት መንገድ ብዙ የፍትሀዊነት ጥያቄ የሚነሳበት ነው። ስራውን ሲሰራ ትርፍና ኪሳራው ይፋ የሚሆንበት መንገድም እንዲሁ ድብቅ ነው። 

በማዕድን ማምረት ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ አደገኛ ኬሚካሎች አያያዝና አጠቃቀም፣ ከሁሉ አስቀድሞ ደግሞ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሚሰጥበት አሰራር ላይ ፍተሻ ማድረግ አሰፈላጊ ነው። የጥናት ውጤቱ ይፋ ሲሆን፣ ለሚድሮክ የኢንቨስትመንቱ ዕጣ ፈንታ ይለያል። ውዝግቡና ግብግቡ ግን ከአካባቢና ብክለት ተቆርቋሪነት ይልቅ ፖለቲካዊ ጥልፍልፉ እያገነገነ ነው። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]

https://youtu.be/wCyk6yeMD8Y