Hossana City

ዋዜማ- ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፣ሐድያ ዞን፣ ሾኔ ሆስፒታል ሰራተኞች የደሞዝ አቤቱታቸውን ለማሰማት ወደ ሆሳዕና ሲያመሩ የፀጥታ ኀይሎች ደብድበው ከመለሷቸው በኋላ የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ሾኔ ሆስፒታል የሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች ከደምወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ሐምሌ 11 ቀን ከሰዓት በኋላ በሦስት መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና ተሳፍረው ችግሩን ለማስረዳትና መፍትሄ እንዲሰጣቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት መቀመጫ ወደ ሆነችው ሆሳዕና ከተማ መጓዛቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም መረጃው ቀድሞ የደረሳቸው የሃዲያ ከተማ ፖሊሶች መኪኖቹን ተከታትለው ዱራሜ ከተማ ላይ አስቁመው ማለፍ አትችሉም ብለው እንደከለከሏቸው ለዋዜማ አስረድተዋል።

ከዱራሜ ከተማ በሌላ መኪና ተሳፍረው ወደ ሆሳዕና እቅንተው የነበረ ቢሆንም፣ ሆሳዕና ከተማ መግቢያ ላይ የከተማዋ ፖሊስ ተሽከርካሪዎቹን በማስቆም ማለፍ እንደማይችሉ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

የሕክምና ባለሙያዎቹ ማለፍ አለብን በማለት በተነሳ እሰጥአገባና የፀጥታ ኃይሎቹ በወሰዱት የኃይል እርምጃ፣ አንዲት ሴትን ጨምሮ አራት ያህል ሰዎች ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት መድረሱን ለዋዜማ ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በየመሃሉ ያልተከፈላቸውን የትርፍ ጊዜ ክፍያ፣ እንዲሁም የ2016 ዓ.ም የግንቦትና ሰኔ ወር ደመወዝ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተከፈላቸው አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ በስሩ ከ 4 መቶ በላይ የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች እንዳሉት የገለጹት ሰራተኞቹ፣ ጉዳዩን ለሆስፒታሉ አስተዳደር በተደጋጋሚ ቢያስረዱም መፍትሄ ሊሰጣቸው አለመቻሉን ገልጸዋል።

የሃድያ ዞን የፋይናንስ መምሪያ ሆስፒታሉ ለሰራተኞቹ ሳይከፍል የቆየውን ደምወዝ እንዲከፍላቸው በተደጋጋሚ በደብዳቤ ያዘዘ ቢሆንም ክፍያው አልተፈጸመም ሲሉም ያብራራሉ።

ከዚህ ቀደም ከክልሉ የብልጽግና ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ክፍያው ይከፈላችኋል ብለው እንደነበርም አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል የሆስፒታሉ አስተዳደር ወቅቱ የበጀት መዝጊያ በመሆኑ የሰኔ ወር ደምወዝ እንድንከፍላችሁ ወስደናል ብለችሁ ፔሮል ላይ ፈርሙ ብሎ እንዳስገደዳቸውና ባለሙያዎቹ ግን ብሩን ሳንወስድ አንፈርምም ብለው ድርጊቱን መቃወማቸውን ለዋዜማ ገልጸዋል።

የሕክምና ባለሙያዎቹ እንዳሉት ከሆነ የሆስፒታሉ የአስተዳደር ሥራ የሚሰሩ ሰራተኞች ደመወዛቸው ሳይቋረጥ እየተከፈላቸው ነው።

ከአሥተዳደር ሰራተኞች ውጪ የሕክምና ባለሙያዎቹ አሁን ሙሉ ለሙሉ የሥራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን ነግረውናል።

የሆስፒታሉ አሥተዳደርም የሕክምና ባለሙያዎቹ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ በቃልና በደብዳቤ በተደጋጋሚ እንዳሳወቃቸው የገለጹት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ደምወዛችን ካልተከፈለን ወደ ሥራ አንመለስም ብለዋል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን አብረሃም ሎምቤን ያነጋገረች ሲሆን ችግሩ በዋናነት የጥሬ ገንዘብ ወይም የካሽ እጥረት መሆኑን አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሃዲያ ዞን ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ (የካሽ) እጥረት አለ ሲሉ ሥራ አስኪያጁ አክለዋል።

ወቅቱ የበጀት መዝጊያ እንደመሆኑ በመንግሥት አሰራር መሰረት በጀት ለመዝጋት ከግንቦት በቀር የሰኔ ወር ደምወዘቻው ተከፍሏቸዋል ሲሉ ለዋዜማ አስረድተዋል።

አሁን ላይ በሆስፒታሉ የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ ቢኖሩም፣ ደምወዛችን ይከፈለን ብለው እየጠየቁ ጎን ለጎን ሥራቸውን ባግባቡ እየሰሩ ያሉ ሰራተኞች መኖራቸውንም አብረሃም ጠቁመዋል።

የሆስፒታሉ አስተዳደር ቀሪውን የሰራተኞች ደምወዝ ከፍሎ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንንም ሥራ አሥኪያጁ ለዋዜማ ተናግረዋል። [ዋዜማ]