በ19 መቶ ስድሳ ዓ.ም በአርበኛ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ተጽፎ ለንባብ በቅቶ የነበረው የአርበኞችን ታሪክ ያቀፈው ‹‹ቀሪን ገረመው›› የተሰኘው መጽሐፍ ከ48 ዓመታት በኋላ ለንባብ በቅቷል፡፡ 450 ገጾች ያሉትና በኢትዮጵያ የአርበኞች ታሪክ ዙርያ በዋቢነት ከሚጠቀሱ መጻሕፍት አንዱ የሆነው ይህ ሥራ በደራሲው ወራሾች ሙሉ ፈቃድ ተገኝቶ በሊትማን ቡክስ አማካኝነት የታተመ ነው፡፡
ደራሲው በ1895 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፣ በ1919 ወደ ግብጽ ሄደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከተመረጡ ሃያ አንድ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት እስክንድሪያ ከተማ ሊሴ ፍራንሴስ ትምህትርት ቤት ገብተው በኋላም ወደ ፈረንሳይ አገር ተሻግረው የቴሌኮሚኒኬሽን ልዩ ትምህርት ሲማሩ ቆዩ፡፡ ኾኖም በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የፋሺስት ወረራ ስለደረሰ የክተቱን አዋጅ በወዶዘማችነት በመቀበል ከፓሪስ ወደ ማይጨው መዝመታቸው ተዘግቧል፡፡
መጽሐፉ በዋናነት በአምስቱ የመከራ ዘመን ግዳጃቸውን ክብር ባለው ተጋድሎ ስለፈጸሙት የሸዋ አርበኞች የሚያተኩር ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ለጠላት የእግር እሳት ሆነው የቆዩ የቤጌምድር፣ የሰሜን ጎጃም፣ የትግሬ፣ የሐረርና የቦረና ጠቅላይ ግዛቶች አርበኞች ታሪክ በዚህ መጽሐፍ በግርድፉ ብቻ እንደተካተተ ተገልጧል፡፡ ‹‹የሸዋን ክፍል ከሞላ ጎደል የጻፍኩት በአምስቱ የመከራና የጨለማ ዘመን በዚሁ በሸዋ የጽዋው ተካፋይ በመሆኔና ብዙዎቹን አርበኞች በመዋቄ፣ ታሪኩንም እስከተቻለ ድረስ በመከታተሌና ጠይቄም በመረዳቴ የሸዋን አርበኞች ታሪክ ለመጻፍ ቻልኩ›› ሲሉ በአንድ አካባቢ ይበልጥ ለምን እንዳተኮሩ ደራሲው በመግቢያቸው አብራርተዋል፡፡
ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ከጠላት ጋር በማበር በአገራቸው ላይ ተነስተው ስለነበሩ ባንዳዎች ስምና ዝርዝር ታሪክ የዘገቡ ሲሆን በአንጻሩ በታላቅ ጀግናነት ጀብድ ሲፈጽሙ ስለነበሩት ልጅ ኃይለማርያም ማሞ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ የደጃዝማች በቀለ ወያ፣ የነእብረሃም ደቦጭና የሞገስ አስገዶም የጀብድ ሥራዎች በዝርዝርና በእማኝነት ዘግበውታል፡፡
መጽሐፉ በፋርኢስት ትሬዲንግ አታሚነት፣ በሊትማን ቡክስ አሳታሚነት ሦስት ሺ ቅጂዎች ታትመው በ182.50 ብር ዋጋ ለአንባቢ ቀርቧል፡፡ ‹‹ቀሪን ገረመው›› በአርበኝነት ገድሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ በነበራቸው ዜጎች ከተጻፉ ጥቂት መጽሐፍት አንዱ ነው፡፡