Alamoundi
Al Amoudi

በኢትዮጵያ እና ስዊድን ቁጥር አንድ የውጭ ባለሃብት የሆኑት ቱጃሩ ሼክ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲን በሞሮኮ የሚገኘው ነዳጅ ማጣያቸው ለወራት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ተቀማጭነቱን ስዊድን ባደረገው የሚድሮክ እህት ኩባንያ በሆነው ኮራል የነዳጅ ኩባንያቸው ስር የሚገኘው ሳሚር የተባለው ነዳጅ ማጣሪያቸው በኪሳራ ሳቢያ ስራ ካቆመ አራት ወራት አልፈዋል፡፡

ሳሚር በአሁኑ ጊዜ ለሞሮኮ መንግስት ያልከፈለው የተጠራቀመ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የታክስ ዕዳ አለበት፡፡ በተጨማሪም 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የባንክ እዳ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ኩባንያው የገባበት ቀውስ ብድር ያበደሩትን የሞሮኮ ባንኮች ጭምር ችግር ላይ ጥሏቸዋል፡፡ ሳሚር በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በሞሮኮዋ ካዛብላንካ አክሲዮን ገበያ 50 በመቶ ዋጋውን አጥቷል፡፡ ከ1,200 በላይ ለሆኑት ሰራተኞቹም ደመወዝ መክፈል ተስኖታል፡፡

አላሙዲ ግን ኩባንያቸው ቀውስ ውስጥ ከገባ ጀምሮ ድምፃቸውን ያጠፉ ሲሆን አልፎ አልፎ መግለጫ የሚሰጡትም በፅሁፍ ብቻ ሆኗል፡፡ ኮራል ኩባንያ ሳሚርን ከገዛ ጀምሮ አላሙዲን ከግል ገንዘባቸው አምስት ሳንቲምም ለኩባንያው እንዳላወጡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይገልፃሉ፡፡
ቻላቸው ታደስ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክቶታል

አላሙዲንም በኩባንያቸው ስራ ማቆም ሳቢያ ከሞሮኮ መንግስት ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውን በርካታ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡ በሞሮኮ መንግስት ባለስልጣናት እና በሳሚር ቦርድ መካከል ጋር የተደረጉት ውይይቶችም ውጤት አላስገኙም፡፡ የኩባንያው ሃላፊዎች በነሃሴ አጋማሽ ኩባንያውን ከኪሳራ ለማውጣት 150 ሚሊዮን ዶላር ለማፍሰስ እየተዘጋጁ እያሉ ነበር የሞሮኮ መንግስት ኩባንያው በባንክ አካውንቱ ተቀማጭ ያደረገውን ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ያገደው፡፡ በካዛብላንካ ያለው የሳሚር አክሲዮን ሽያጭም እንዲሁ በመንግስት ታግዷል፡፡

አላሙዲን ወደ ሞሮኮ ነዳጅ ኢንዱስትሪ የገቡት ኮራል ፔትሮሊዬም እኤአ በ1997 ዓ.ም ሳሚር የነዳጅ ማጣሪያን ከሞሮኮ መንግስት ከገዛ በኋላ ነበር፡፡ ኮራል ፔትሮሊዬም በሳሚር ላይ የ67 በመቶ ባለቤትነት ድርሻ አለው፡፡ ሳሚር 65 በመቶ የሚሆነውን የሞሮኮ የተጣራ ነዳጅ ገበያ ይቆጣጠራል፡፡ በቀን ሶስት መቶ ሺህ በርሜል ነዳጅ ፍጆታ ያላት ሞሮኮ በፍጆታዋ በአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ኩባንያው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረበት ዕዳ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እንደነበር ከራሱ ከኩባንያው የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በነዳጅ ዓለም ኣቀፍ ዋጋ ማሽቆልቆል ሳቢያ ሳሚር የአምናውን በጀት ዓመት ያጠናቀቀው በ340 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በያዝነው የፈንጆች ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ 233 ሚሊዮን ዶላር እንደከሰረ ኩባንያው ራሱ አስታውቋል፡፡ ቬንቸር አፍሪካ የተሰኘው ድረ ገፅ እንደሚለው ከሆነ ሳሚር በወርቃማ ዘመኑ በዓመት 57 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ያካብት ነበር፡፡

ኪሳራውን ተከትሎም በየካቲት ከዓለም ዓቀፉ እስላማዊ የገንዘብና ንግድ ኮርፖሬሽን (International Islamic Trade Finance Corporation) 235 ሚሊዮን ዶላር ተበድሯል፡፡

አላሙዲን ኩባንያቸው በኪሳራ ከተዘጋ በኋላ በነሃሴ ወር አጋማሽ ላይ ከሞሮኮ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን በርካታ የሞሮኮ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን የሞሮኮ መንግስት ግን በውይይቱ ማግስት ኩባንያው ያለበትን እዳ በሙሉ እንዲከፍል ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል፡፡ አረብ ዊክሊ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው አላሙዲ ኩባንያቸውን ከውድቀት ለመታደግ 150 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መመድብ እንደሚፈልጉ ቢገልፁም የሞሮኮ ባለስልጣናት ግን እሳቸው ካቀረቡት አስር ዕጥፍ የሚልቅ ገንዘብ መመደብ እንዳለባቸው ነገረዋቸው ነበር፡፡

የሞሮኮ መንግስት ባለስልጣናት ቱጃሩ ሳሚር ብቸኛው የነዳጅ ዘይት ኩባንያ መሆኑን ስለሚያውቁ የኩባንያቸውን ቀውስ ከራሳቸው ትክሻ አውርደው የሞሮኮ መንግስት ድጎማ በማድረግ ቀውሱን እንዲፈታው የመፈለግ አዝማሚያ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን መንግስት ለኩባንያቸው ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለው እና ራሳቸው ሊወጡት እንደሚገባ ግልፅ እንዳደረገላቸው ዓረብ ዊክሊ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የመንግስት አቋምም ቱጃሩን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡

አላሙዲን ከባለስልጣናት ጋር ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎም የሳሚር ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ጥቅምት ወር ተሰብስቦ ኩባንያውን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰበሰብ ወስኖ እንደነበር ከሳሚር የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ አብዛኛውን አክሲዮን ድርሻ የያዙት አላሙዲን 670 ሚሊዮን ዶላሩን እንዲያዋጡ፤ ቀሪውን ሌሎች ባለ ድርሻዎች መሸፈን ካልቻሉም ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመድቡ ወስኖባቸው ነበር፡፡ አላሙዲን ግን እስካሁንም ውሳኔውን ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ ታዛቢዎች ግን የወቅቱ ነዳጅ ገበያ ሁኔታ ለነዳጅ ኢንዱስትሪ ገንዘብ ለማሰባሰብ አመቺ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳ የገንዘቡ መጠን ከግዙፉ ኮራል ኩባንያ አቅም በላይ ይሆናል ብለው ባያምኑም፡፡

ቱጃሩ አላሙዲን የሳዑዲ ዓረቢያ ዜጋ በመሆናቸው የሳሚር ቦርድ የሳዑዲ ዓረቢያው ንጉስ ሳልማን ነሃሴ ላይ በሞሮኮ ያደረገትን ጉብኝት እንደ ሽፋን በመጠቀም ቀውሱን የሁለቱ ሀገሮች ፖለቲካዊ ጉዳይ ለማስመሰል ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ታዛቢዎች ይገልፃሉ፡፡

አሁን ያለው ጥያቄ የአላሙዲን ኩባንያ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆናል? የሚለው ሆኗል፡፡ አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሞሮኮ መንግስት ባለስልጣናት ሁለት አማራጮች አሏቸው፤ አንድም ኩባንያውን ለሞሮኳዊ ባለሃብቶች በማስተላለፍ በቶሎ ስራውን እንዲጀምር ማድረግ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለሞሮኮ መንግስትና ባንኮች ካለበት ግዙፍ ዕዳ አንፃር መንግስት ሙሉ በሙሉ ሊወርሰውም ይችላል፡፡ ምናልባት ሁኔታዎች ባሉበት ከቀጠሉ የዓለም ነዳጅ ዋጋ እንደቀነሰ ከመቀጠሉ ጋር ተዳምሮ ዕጣ ፋንታው ከእንዚህ አማራጮች ላያልፍ ይችላል፡፡
ከሳሚር 50 በመቶውን ነዳጅ አቅርቦቱን ያገኝ የነበረው ነዳጅ አከፋፋዩ ኦይል ሊቢያም የኩባንያውን ኪሳራ ተከትሎ ክፍተት ስለተፈጠረ በመጭዎቹ ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ለመጀመር ማቀዱን በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም ዕቅዶች ዋነኛው በሞሮኮ የወደብ ከተማ “አጋድር” ግዙፍ ነዳጅ ማጠራቀሚያ በመገንባት ከሊቢያ የተጣራ ነዳጅ ማስገባት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

Al Amoudi

በዓለም ላይ እኤአ ከ2014 ጀምሮ የነዳጅ አቅርቦት ከፍላጎት በመብለጡ ዋጋው እጅጉን ወርዷል፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት እንደዘገበው የነዳጅ ዋጋ ሰኔ 2014 ላይ በበርሜል 115 ዶላር የነበረ ቢሆንም በዓመቱ መጨረሻ ግን ወደ 70 ዶላር ወርዶ ነበር፡፡ በ2014 የተመዘገበው የዋጋ ቅናሽ ለአምስት ኣመታት የዘለቀውን የተረጋጋ ዋጋ አዛብቶታል፡፡ በያዝነው ሳምንት ደግሞ አንድ በርሜል እስከ 37 ዶላር ድረስ ቀንሷል፡፡

ለዋጋው መቀነስ አስተዋፅዖ ያደረጉት የዓለም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቀሴ መቀዛቀዝ፣ ቆጣቢ ዘመናዊ አጠቃቀም እና የሌሎች ኢነርጂ ምንጮች መስፋፋት እንደሆኑ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል አሜሪካ ዋነኛዋ የዓለማችን ነዳጅ አምራች ሆና ብቅ ማለቷም ተጠቃሽ ነው፡፡ የአሜሪካ ነዳጅ ምርት በ2014 ዓ.ም ቀደም ሲል ከነበረው ምርት መጠን ጋር ሲነፃፀር የ16 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በተጨማሪም ሳዑዲ ዓረቢያና የባህረ ሰላጤው ሀገሮች ዋጋውን ከፍ ለማድረግ ሲሉ ብቻ ምርታቸውን ቢቀንሱ ተቀናቃኛቸው ኢራን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ስለምታገኝ ምርታቸውን መቀነስ አለመፈለጋቸውም አንዱ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ሳዑዲ ከሌሎች አንፃር ነዳጅ ለማውጣት የምታወጣው ወጭ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ዝቅተኛ ዋጋ እምብዛም አይጎዳትም፡፡

በዓለም ነዳጅ ገበያ የ40 በመቶ ድርሻ ያለው የነዳጅ አምራቾች ማህበር “ኦፔክ” አባላት በቅርቡ ተሰብስበው ምርት ለመቀነስ መስማማት አለመቻላቸውም ዋጋውን የበለጠ እያወረደው እንደሆነ የእንግሊዙ ቴሌግራፍ ሰሞኑን ዘግቧል፡፡

በነዳጅ ዋጋ መቀነስ በጣም የተጎዱት ዋጋው ይጨምራል በሚል ተስፋ ብዙ ገንዘብ በሚጠይቁ የነዳጅ ፍለጋ እና ምርት ዘርፎች የተሰማሩት እና ለቀውስ ተጋላጭ የሆኑት ነዳጅ አምራቾች እና ገንዘብ ያበደሩ ባንኮች ናቸው፡፡ የአላሙዲን ሳሚር ኩባንያም በቀላሉ ለቀውስ ተጋላጭ ከሆኑት አምራቾች ስለሚመደብ ነው አጣብቂኝ ውስጥ የገባው፡፡