FILE

ዋዜማ- የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አንቶኒ ብሊንከን ቅዳሜ ዕለት የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድን በስልክ ያነጋገሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል እየተካረረ ያለው ውዝግብ መርገብ እንዳለበት አሜሪካ ፍላጎቷ መሆኑን ገልፀዋል።


ዋዜማ ከአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት ምንጮች እንደሰማችው ሶማሊያ የኢትዮጵያን ሰራዊት ከሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማስወጣት መወሰኗን ዋሽንግተን በበጎ አልተመለከተችውም።


ብሊንከን ለፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሀመድ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣትም ሆነ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚኖር መካረር አጠቃላይ ቀጠናውን ወደከፋ አለመረጋጋት ይወስደዋል የሚል ስጋት አላቸው።


የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያ ቆይታ በሶማሊያ መንግስት ይሁንታ የሚወሰን ቢሆንም ፣ በአሜሪካ በኩል የኢትዮጵያ መውጣትን ተከትሎ አልሸባብ ሊያንሰራራና የሶማሊያ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት አለ።


ብሊንከን ፕሬዝዳንት ሐሰንን ከማነጋገራቸው ሰዓታት በፊት የፕሬዝዳንቱ የፀጥታ አማካሪ ከመጪው ታህሳስ ወር በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ጠቅሎ እንዲወጣና በቀጣይ ተልዕኮም እንዳይካተት እንደምትፈልግ ይፋ አድርገው ነበር።

ብሊንከንና ፕሬዝዳንቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖለቲካ ጉዳዮች የመስክ ቢሮ በሶማሊያ የሚቀጥልበትንም መንገድ ተወያይተዋል። ሶማሊያ ከሳምንታት በፊት የተመድ የፖለቲካ ቢሮንም ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ መጠየቋ ይታወሳል።


ብሊንከን ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙበት የባህር በር የመግባባቢያ ስምምነት ያለሞቃዲሾ ፈቃድ ተግባራዊ እንዳይሆን አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማግባባትና ጫና ለማድረግ እንደምትሞክር መናገራቸውንም ሰምተናል።


ሐሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባህር በር ስምምነቱን ከተወችው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነቷን ለማደስ ፈቃደኛ መሆኗን አስታውቀዋል ተብሏል።


አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከትግራይ ጦርነት ወዲህ ቢሻሻልም በቅርብ ወራት ዳግም በተፈጠሩ አለመግባባቶች መቀዛቀዙን ብሉም ከመጋረጃ ጀርባ የበረታ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ መኖሩን ዋዜማ ባለፉት ሳምንታት ከተለያዩ መንግስታዊና ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች ሰምታለች።


አሜሪካ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችበትን የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ያለ ሶማሊያ መንግስት ፈቃድ ተግባራዊ መሆን የለበትም የሚል አቋም ያላት ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ቻይናና ሌሎች በርካታ ሀገራት ስምምነቱን ተቃውመውታል። የአፍሪቃ ህብረት በበኩሉ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ እንዲመካከሩና ህጋዊ መንገድን ብቻ እንዲከተሉ መክሯል። [ዋዜማ]