ዋዜማ ራዲዮ- በፋና ቴሌቭዥን እና በዩቲዩብ ለተወሰኑ ወራት ቀርቦ በውዝግብ የተቋረጠው “ምን ልታዘዝ” ድራማ ተዋናዮች ደራሲና አዘጋጅ በአዲስ ድራማ ወደ ተመልካች ለመድረስ እየተሰናዱ መሆኑን ዋዜማ ከቡድኑ አባላት ስምታለች።
“አስኳላ” የተሰኘ አዲስ ሲት ኮም ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማን እየቀረፁ ሲሆን በቅርብ ወደ ተመልካች መድረስ ይጀምራል።
በኋይሉ ዋሴ የድራማው አዘጋጅና ፀሀፊ ሲሆን ይህ ተከታታይ ድራማ በዲኤስ ቲቪ የአማርኛ ቋንቋ ቻናል በኩል እንደሚቀርብ ለዋዜማ ተናግሯል።
በኋይሉ ዋሴ ከማዝናናት በዘለለ የፊልሙ ኢንደስትሪ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሎም በማህበራዊ ችግሮቻችን ዙሪያ የሕዝቡ ድምፅ መሆን አለበት ብሎ ያምናል።
“ምን ልታዘዝ” ድራማ በአደባባይ መቅረብ ያልቻሉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትችቶችን አዝናኝ በሆነ መልክ በማቅረብ በህዝብ የተወደደ የነበረ ቢሆንም ድራማውን በሚያዘጋጁት ባለሙያዎችና በፋና ብሮድካስት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት መቋረጡ ይታወሳል።
ፋና ቴሌቭዥን ድራማው በማስታወቂያ ዕጥረት መቋረጡን ገልጾ ውዝግብ አለ መባሉን አስተባብሎ ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]