METEC -EPEI
METEC -EPEI

ዋዜማ ራዲዮ- በሙስናና በብቃት ማነስ ለከፍተኛ የሀብት ብክነት ስበብ የሆነው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ሲቪል ሰራተኞቹን በግዳጅ እረፍት እያስወጣ ነው። ድርጅቱ በአዲስ መልክ ሊዋቀር እንደሆነም ተሰምቷል።

በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የተሰየሙ ሶስት የጥናት ቡድኖች ባቀረቡት ሀሳብ ላይ በመንተራስ ሜቴክ ወታደራዊና ሲቪል ምህንድስናና አምራች ክፍሎቹ እንደ አዲስ ይዋቀራሉ። በመልሶ ማዋቀሩ ተቋሙ ብቃት ሳይኖረው የገባባቸውን የስራ ዘርፎች የሚያጥፍና አዳዲስ አደረጃጀቶችንም የሚከተል ነው። ይህን አዲስ አደረጃጀት ለመተግባር ሜቴክ ሲቪል ሰራተኞቹን ግዳጅ እረፍት እያስወጣ መሆኑንም ባደረግነው ማጣራት አረጋግጠናል።

የኮንትራት ውሎቹን እየተነጠቀ ያለው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን  (ሜቴክ) ሲቪል ሰራተኞቹን የረጅም ጊዜ ፍቃድ እያስወጣ ነው።የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ባልተለመደ ሁኔታ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን  ለአንድ ወር ፍቃድ አስሞልቶ እያስወጣቸው መሆኑን ሠራተኞቹ ለዋዜማ ራዲዮ ተናግረዋል።

መረጃውን ያደረሡን የሜካኒካል ምህንድስና ባለሙያዎች ኮርፖሬሽኑ በገፍ ሠራተኞቹን ፍቃድ እያስወጣ ያለው የተለያዩ ውሎቹን በተለይም የመንግስት ፕሮጀክቶች ከእጁ እየወጡ በመሆኑ በኮርፖሬሽኑ ስር ባሉ የተለያዩ ማምረቻ ፋብሪካዎች የስራ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ነው ብለውናል።

ሜቴክ አጠቃላይ ሀያ ሺህ ያህል ስራተኞች አሉት።

ሜቴክ ኦሞ ኩራዝ : ጣና በለስ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት የተሰኙ ሶስት የስኳር ፕሮጀክቶቹ እንዲነጠቁ መደረጉን ተከትሎ በፕሮጀክቶቹ ይሠሩ የነበሩ የሜቴክ ተቀጣሪዎች  ሆነው አዲስ አበባ ወዳለው መስሪያ ቤት መምጣታቸው ተሠምቷል።ሠራተኞቹ ለዋዜማ ራዲዮ እንዳሉት ከሆነ ይህን ተከትሎ በሠራተኞች ዘንድ የስራ ዋስትና ማጣት ስጋትን ተከትሎ የየክፍል አለቆች ሰብስበዋቸው ሊያረጋጓቸው ሞክረዋል።

ሜቴክ ሶስቱን የስኳር ፕሮጀክቶች እጅግ ማጓተቱን ተከትሎ መንግስት ፕሮጀክቶቹን ነጥቆታል።እያንዳንዳቸው ስኳር ፕሮጀክቶች ከ235 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጭ ወጥቶባቸው በ18 ወራት እንዲጠናቀቁ በ2004 አ ም ወደ ግንባታ ቢገቡም ፕሮጀክቶቹ ስድስት አመት አልፏቸውም ወደ ስራ አልገቡም።

ኦሞ ኩራዝ 95 በመቶ ጣና በለስ ቁጥር አንድ 78.75 በመቶ ጣና በለስ ቁጥር ሁለት ደግሞ 25 በመቶ ላይ ነው ያሉት።ይህ መጓተታቸውን የሚያሳይ ሲሆን ከውል በላይ አመታት ተጓተውም ምርት ባለመጀመራቸው ሜቴክ ፕሮጀክቶቹን ተነጥቋል።በዚህም የተነሳ ሰራተኞቹን ካለ ስራ አስቀምጧል።

በሌላ በኩል በሜቴክ ስር ባለው የፓወር ኢንጂነሪንግ ፋብሪካዎች ውስጥ ስራ በእጅጉ በመቀዛቀዙ ሰራተኞቹ በተመሳሳይ የአንድ ወር ፍቃድ ሞልተው እየወጡ ነው።የሜቴክ ፓወር ዘርፍ አምራች ፋብሪካዎች ከ2000 በላይ ሰራተኞች በተለያዩ ቅርንጫፎች አሉት።ለታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋተር ኢንቴክ የተባለውን አካል ጨምሮ የተለያዩ የብረት አካላትን የሚያመርተው የአዲስ አበባው ፋብሪካም ስራው ተቀዛቅዟል።

ሜቴክ በተለያየ መስሪያ ቤት ያሉ ሰራተኞቹን በግፊት ፍቃድ እያስወጣ መሆኑ ሰራተኞች ላይ ስጋትን ጭሯል።በሌላ በኩል ጠቅለይ ሚኒስት አብይ አህመድ በተለያዩ መድረኮች ሜቴክን ሸንቆጥ የሚያደርግ ንግግር ማድረጋቸው ኮርፖሬሽኑ እንደቀድሞው ደንበኞችን አስገድዶም ጭምር አዳዲስ ስራዎችን እንዳያገኝ እያደረገው ነው።ከውጭ ያስገባ የነበረው ጥሬ እቃም “መቋረጥ” ሊባል በሚችል ደረጃ ተቀዛቅዟል። ሜቴክን የተመለከተ ተጨማሪ ዘገባ እዚህ ያንብቡ  CLICK