METEC former boss Gen. Kinfe Dagnew

ዋዜማ ራዲዮ- የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በማዘግየትና በምዝበራ ስሙ ተደጋግሞ ሲነሳ ስምታችኋል። ሌላ ያልሰማችሁትን የሜቴክ ረጅም እጅ ከሀገር ውጪ ጭምር ህገ ወጥ ተግባር የተፈፀመበትን ጉዳይ እንነግራችኋለን። ሜቴክ ሁለት የኢትዮጵያ ግዙፍ መርከቦችን ከብዙ ኪሳራ ጋር ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሽጧቸዋል።

ነገሩ ከዛሬ ስድስት አመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2012 በሀበሻ አቆጣጠር ይጀምራል። በወቅቱ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት የአሁኑ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት በባለቤትነት ሲያንቀሳቅሳቸው ከነበሩ መርከቦች መካከል አብዮትና አባይ ወንዝ የሚባሉት መርከቦች ከ27 አመት በላይ የሆናቸውና ያረጁ በመሆናቸው እንዲወገዱ ይወሰናል።ሁለቱ መርከቦች እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያላቸው ናቸው።በእርጅና ምክንያት እንዲወገዱ ሲወሰንም የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ብረታቸውን አቅልጬ ልጠቀም በሚል መርከቦቹን ይገዛቸዋል።

አግባብነት የሌለው አሰራሩ የጀመረው እዚህ ጋር ነው።ሜቴክ መርከቦቹን የገዛበት መንገድ ግልጽ ያልሆነና ሌሎች ብረት ፈላጊዎችን አግላይ ነበር።በወቅቱ አብዮትና አባይ ወንዝ የተሰኙት መርከቦች ለሜቴክ እንዲሸጡ የወቅቱ የመርከብ ድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበርና የቀድሞ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር መኩሪያ ሀይሌ : የቦርድ አባሉ አምባሳደር ዶክተር አዲሳለም ባሌማ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ዋዜማ ራዲዮ ተረድታለች።

ሜቴክ ብረቱን አቅልጬ ለሌላ አገልግሎት እጠቀምባቸዋለሁ ያላቸውን መርከቦች ለታሰበው አላማ አላዋላቸውም።በመጀመርያ መርከቦቹ ለስምንት ወራት በጅቡቲ ወደብ ቆመው ነበር።ለዚህም በቀን ለእያንዳንዳቸው 4000 የአሜሪካን ዶላር የወደብ ኪራይ ይከፈል ነበር።የሚገርመው በዚህ ጊዜ መርከቦቹ በሜቴክ ይገዙ እንጂ የኪራዩ ወጭ የተሸፈነው በባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ነበር።ከዚህ ሁሉ ህገ ወጥ ድርጊት በሁዋላም ሜቴክ መርከቦቹን እንዳለው ብረታቸውን አቅልጦ ከመጠቀም ይልቅ የተባበሩት ኤምሬቶች :ዱባይ: ወስዶ ያሳድሳቸዋል። ሜቴክ ለሁለቱ መርከቦች ግዥና ጥገና በጥቅሉ 10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር አውጥቷል።የመርከቦቹንም ዋጋ ለንግድ መርከብ ድርጅቱ መክፈሉን አውቀናል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስሪት ባልታየ ሁኔታ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል ሁኔታ ሜቴክ መርከቦችን የማንቀሳቀስ ፍቃድ ሳይኖረው በአለም አቀፍ የውሀ አካላት ላይ የመርከብ ባለቤት ሆኖ ነበር። በኢትዮጵያ ይህን አይነት ፍቃድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣንም ቢሆን ለሜቴክ ስራ ምንም አይነት ፍቃድ እንዳልሰጠ ታውቋል።ሌላው ቢቀር ሜቴክ ሁለቱን መርከቦች የንግድ ስራ ሲጠቀምባቸው ማሟላት ያለበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ፣ የደህንነት ደረጃ ፣ የባለሙያ ደረጃዎችን ሁሉ ሳያሟላና እጅግ አደገኛ በሆነና ህገ ወጥ በሆነ መልኩ ነው።

ለስራውም ከንግድ መርከብ ጡረታ የወጡና ውላቸው የተቋረጡ ሰዎችን እንዲሁም የውጭ ዜጎችን ይጠቀም ነበር።ሜቴክ መርከቦቹን ይጠቀምበት የነበረው ህገወጥ ተግባር  ነው በሚል የተለያዩ ከበድ ያሉ ውንጀላዎች ይቀርብበታል። በዚህ ወቅት መርከቡን ለመጠቀም ከሆነ ከአንድ የመንግስት የልማት ድርጅት ወደሌላው ማሸጋገር ለምን አስፈለገ?  በሚል ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር።ይሁን እንጂ ሜቴክንም ሆነ ህገ ወጥ ውሳኔ ያስወሰኑ የመንግስት ባለስልጣናትን በህግ የጠየቀ አልነበረም።

ሜቴክ መርከቦቹን በሀገር ውስጥ አከናውናለሁ ለሚላቸው ፕሮጀክቶች ግብአት ማመላለሻነት በቅጡ ቢጠቀምበት ምንም አልነበረም ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጮቻችን። ሜቴክ ለዚህ ፍላጎቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አገልግሎትን እየተጠቀመ እስከ 400 ሚሊዮን ብር የአገልግሎት ውዝፍ እየመጣበት በከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ውትወታ ነበር ክፍያ የሚፈጽመው።

የሁለቱ መርከቦች አጠቃቀሙም አክሳሪ ነበር።ከሚሰሩበት ወደብ ላይ ቆመው በውጭ ምንዛሬ እለታዊ ክራይ ይከፈልባቸው ነበር።በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሱሌይማን ደደፎ ሁኔታው አሳስቧቸው ነገሩን መላ እንዲሉት ለቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም የጻፉት ደብዳቤ አፈትልኮ የማህበራዊ ድረ ገጽ መነጋገርያ ሆኖ ነበር።

ከዚህ ሁሉ የብክነት ጉዞ በሁዋላ ሜቴክ ሁለቱን መርከቦች  ዱባይ ወስዶ ሽጧቸዋል።ለማን? ስንት ሸጣቸው?  የሽያጬ ገንዘብስ የት ገባ? እስካሁን አልታወቀም ።በጉዳዩ ላይ መንግስት ምርመራ መጀመሩን ስምተናል።

ሜቴክ የፈጠረውን ተደጋጋሚ ችግር ታሳቢ በማድረግ ድርጅቱ ወታደራዊና ሲቪል ስራዎች በሚል ለሁለት መከፈሉን በቅርቡ አስታውቋል። በሀገሪቱ ላይ ለደረሰው እጅግ ከፍተኛ ኪሳራ እስካሁን ሀላፊነት የሚወስድ አልተገኘም።

ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/XOUw3ILxuLo