ዋዜማ ራዲዮ- በወለጋይቱ ጩታ መንደር የተወለደው ገጣሚ ፣ሀያሲ፣ ተመራማሪ ፣ ፈላስፋ ፣ መምህር ባጠቃላይ ገጸ ብዙው ኢትዮጵያዊ ሰለሞን ደሬሳ የእድሜውን እኩሌታ የኖረባት የአሜሪካ ግዛት የሆነችው ሚንሶታ ባሳለፍነው ሳምንት (ጃንዋሪ 26,2018) አርብ ምሽት በስራዋቹ ስታከብረው አምሽታለች።
ሰለሞን ደሬሳ በህዳር ወር 2017 በአካል ቢለይም ትቶ ባሳለፋቸው ስራዋቹ እና ትዝታዋቹ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል። ብእርና ዜማ በሚል ስያሜ የተሰባሰቡና በሚኒሶታ ግዛት የሚገኙ ወጣቶች ከ University of Minnesota, Interdisciplinary Center for the Study of Global Change (ICGC) እና ከዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ጋር በመተባበር ምሽቱን ያዘጋጁት።
የዋዜማ ሬድዮ ባልደረባ በቦታው ተገኝታ እንደዘገበችው በእለቱ የሰለሞን ደሬሳ ወንድም አምባሳደር ብርሃነ ደሬሳ እና ፕሮፌሰር ማርያ ዴመን (ከፕራት ኢንስትትዩት – ኒውዬርክ) በክብር እንግድነት በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይ ታድመዋል። ወዳጅና አድናቂዋቹ ዶ/ር አስቴር ገ/ማርያም፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ (ከኢትዮጵያ)፣ ፕሮፌሰር በረከት ሀብተስላሴ (ከኖርዝ ካሮላይና) የፅሁፍ ምስክርነት እና ግጥሞች በመላክ፣ እንዲሁም ሶማልያዊው ፕሮፌሰር አሊ ጀማል አህመድ (ከኩዊንስ ኮሌጅ – ኒውዬርክ) እና ፕሮፌሰር ዳግማዊ ውብሸት (ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፔንሲልቬኒያ) ምስክርነታቸውን በቪድዮ አቅርበዋል። ዳዊት ወርቁ ከፍኖተ ጥበብ የስነ-ጽሁፍ ማህበር በአካል በመገፕት ትዝታዎቹን አካፍልዋል። በእለቱ ዶክመንተሪ ፊልም፣ የፎቶ እግዚቪሽን የሰለሞን ደሬሳ የምርምር፣ የጋዜጠኝነትና የኪነ ጥበብ ህትመቶች ለእይታ ቀርበዋል። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ከታች ያገኙታል]