ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት በብርቱ የኢኮኖሚና የፀጥታ ፈተና ውስጥ ሆኖ ከሁለት ወር በኋላ ለሚጀምረው አዲሱ የበጀት ዓመት 780 ቢሊየን ብር በጀት ማዘጋጀቱን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ስምታለች።
አዲሱ በጀት ከዘንድሮው በጀት ጋር ሲነፃፀር የአንድ መቶ ቢሊያን ብር ያህል ብልጫ አለው። የ 2014 ዓ.ም በጀት የአጋማሽ አመቱ ጭማሬ ተዳምሮ 680 ቢሊየን ብር ነበር። ዘንድሮን በበርካታ መሰናክሎች ያሳለፈው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቀጣዩ ዓመት የበለጠ ፈተና የሚጠብቀው ሲሆን መንግስት አሁን ያሰናዳው 780 ቢሊየን ብር በጀት ከፍ ያለ ጉድለት ሊገጥመው እንደሚችል በበጀት ዝግጅቱ ወቅት በተደረጉ ምክክሮች ላይ መነሳቱን ስምተናል።
ለ2015 ዓ.ም የተያዘው በጀት ከ 2014 ዓ.ም የ100 ቢሊየን ብር ጭማሬ ይኑረው እንጂ በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሲሰላ ብዙም ለውጥ የሚታይበት አይሆንም።
የአጠቃላይ የበጀት ድልድሉን የተመለከተ መረጃ ገና ይፋ ባይሆንም ለቀጣይ አመት የተያዘው በጀት እድገት ግን ተፈጥሯዊ ሊባል የሚችል መሆኑን ነው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የምጣኔ ሀብት ምሁር ለዋዜማ ራዲዮ የገለጹት። ከዛ ይልቅ አሳሳቢ ሆኖ ያየሁት በጀቱ የሚሟላበት መንገድ የዋጋ ንረት ፈጣሪ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ሊሆን መቻሉ ነው ይላሉ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ።
መንግስት በ 2014 ዓ.ም ይኖብርኛል ብሎ የያዘው የበጀት ጉድለት ከ180 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን በጦርነትና ገቢ አሰባሰብ መዳከም እንዲሁም በብድርና እርዳታ መቀዛቀዝ ሳቢያ የነበረው የበጀት ጉድለት ከዚህ እንደበለጠ ግልፅ ነው። ይህም መንግስትን ከብሄራዊ ባንክ እንዲበደርና ለዋጋ ንረት የሚዳርግ የብር ህትመት እንዲኖር እንዳስገደደው መረጃዎች ያሳያሉ።
በተያያዘ መንግስት የብር ህትመት ሳያስፈልገው የበጀት ጉድለትን የሚሞላበት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ላለፉት ወራት መቀዛቀዝ ታይቶበል። በሚያዝያ ወር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ 21 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው ሰነድ ለገበያ አቅርቦ የ12 ቢሊየን ብር ሰነድ ነው የሸጠው።በመጋቢት ወርም እንዲሁ የ21 ቢሊየን ብር ሰነድ ለገበያ አቅርቦ 10 ቢሊየን ብቻ ነው የሸጠው።
ከሁለት አመት በፊት የግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ እንደ አዲስ ሲጀመር መንግስት ዳጎስ ያለ ብድርን ከገበያው እያገኘ የመጣ ቢሆንም የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ፣ የገበያው ዋና ተሳታፊ እየሆኑ የመጡትን ባንኮች ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ እያደረጋቸው በመሆኑ መንግስት ከሰነድ ሽያጭ ያሰበውን ያክል እንዳያገኝ አድርጎታል።
በገቢ አሰባሰብ እና በሰነድ ገበያ ላይ ያሉ መቀዛቀዞች እንዲሁም ከጸጥታ ጋር ያለው ሁኔታ በአስተማማኝ ካልተፈታ የቀጣይ ዓመት በጀት የሚሞላበትን መንገድ የዋጋ ንረትን ሊያባባስ የሚችል እንደሚሆን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ስጋታቸውን ይናገራሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]