Chaka housing project design

ዋዜማ- የብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት ሊያካሂድ ሰላቀዳቸው የመሰረተልማትም ይሁን ሌሎች ፕሮጀክቶች አስቀድሞ ለህዝብ የማሳወቅ ልማድ የለውም። ይልቁንም አንዳንድ ፕሮጀክቶች ሚስጥራዊነት ይታይባቸዋል። ዋዜማ መንግስት በቅርቡ ለመጀመር ያቀዳቸውን  ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተዘረዘሩበትን ሰነድ አግኝታ ተመልክታለች። አንብቡት

የተመለከትነው ሰነድ መንግስት ለመጀመር አቅዷቸው “እጅ ስላጠረኝ አለማቀፍ ባለሀብቶች በሽርክና አብራችሁኝ ስሩ ፣ ከትርፉም ተካፈሉ” በሚል ያሰናዳው ዝርዝር ነው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በመሆን ለአልሚዎች ይፋ ያደረጉት የእነዚህ ፕሮጀክቶች ዝርዝር እንደሚያሳየው መንግሥትና የውጭ የግል ባለሀብት በጋራ (Public Private Partnership) ቢያለሙ አዋጭ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ መንግሥት መሬትና የተለያዩ ድጋፍ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ባለሀብቱ ደግሞ በማልማት፣ ከዚያም ከ20 እስከ 30 ዓመታት ውስጥ ፕሮጀክቱን እያስተዳደረ ትርፉንና ዋናውን ከመለሰ በኋላ ፕሮጀክቱን ለመንግሥት አስረክቦ ይወጣል፡፡

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የጫካ ቤቶች ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህም 51.5 ቢሊዮን ብር ይፈልጋል፡፡ በዓመት 486,000 ዘመናዊ ቤቶችን መገንባት እጅግ አንገብጋቢ መሆኑንና አቅርቦቱ ግን 165 ሺሕ ብቻ ነው ይላል ሰነዱ፡፡ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክትም ለብቻው 120 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል፡፡ 

ለታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈለጉ ፕሮጀክቶች ተዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ወራንሶ ሶላር ፕሮጀክት (አፋር)፣ ጋድ ሶላር (ሶማሌ ክልል)፣ አይሻ ንፋስ ኃይል (ሶማሌ)፣ ደብረ ብርሃን ንፋስ ማመንጫ (አማራ ክልል) ይገኙበታል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገነባ የካንሰር ሆስፒታል፣ በወላይታ ሊገነባ የታሰበ የካሳቫ ስታርች ፋብሪካ፣ የአዋሽ ሪዞርት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ቱሉ ቦሎ ከዚያም ጅማ ድረስ የሚዘረጋ የፍጥነት መንገድ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 

ከአዲስ አበባ 26 ኪሎሜትር ቢሾፍቱ ላይ ሊገነባ የታቀደው እንዶድ የተቀናጀ የደረቅ ወደብ አገልግሎት ሌላው መንግስት 2 ቢሊየን ዶላር የያዘለት ፕሮጀክት ነው።

በፈረንጆች 2030 የመንግሥት መኪኖች በሙሉ ወደ የኤሌክትሪክ ለመቀየር በመታቀዱና በአገሪቱ የሚኖሩ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቁጥር አሁን ካለበት 100 ሺሕ አካባቢ በፍጥነት እንደሚያድግ በመታሰቡ በዚህ ዘርፍም ብዙ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዷል፡፡ 

በአጠቃላይ በምግብ ዘይት፣ በባቡር፣ በድንጋይ ከሰል፣ በወርቅ፣ በሊትዬም፣ በመስኖ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች በPPP መሠረት ለማልማት ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የአውሮፓ ሕብረትና ግራንት ቶርንቶን በጋራ ያወጡት ሰነድ ያሳያል፡፡ [ዋዜማ]