ዋዜማ- በሀገሪቱ ባለው የፀጥታ ችግርና የትራንስፖርት አቅርቦት መስተጓጎል ወትሮም የበረታ እጥረት የሚታይበት ነዳጅ አሁን በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ የበለጠ ተባብሷል። ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በበርካታ የሀገራችን ከተሞች እየተዘወተረ ነው። ዋዜማ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የነዳጅ አቅርቦትና ዋጋን በተመለከተ የሚከተለውን መረጃ አሰናድታለች።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመጋቢት ወር  የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርጓል። ከትላንት መጋቢት 1፣ 2018 ዓ፣ም ከስዓት በኋላ ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው ጭማሪ፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 139 ብር ከ48 ሳንቲም፣ ኬሮሲን 146. በር ከ14 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 137 ብር፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 133 ብር ከ45 ሳንቲም፣ ቤንዚን 132 ብር ከ18 ሳንቲም፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 145 ብር ከ23 ሳንቲም ሆኗል።

የዋጋ ጭማሪው በነጭ ናፍጣ ላይ 10 ብር፣ ኬሮሲን ላይ ሰባት ብር፣ ቤንዚን ላይ ሦስት ብር መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

መደበኛ የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ጭማሪ ከመደረጉ ቀደም ብሎ፣ በተለይ ካለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ሳምንት ወዲህ የሕገ ወጥ ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ንሯል።  በተለያዩ የክልል ከተሞች የተፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ፣ በሊትር እሰከ 500 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት ተረድታለች።

መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በተከሰተበት ትግራይ ክልል፣ አንድ ሊትር ናፍጣ እስከ 550 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ከክልሉ አሽከርካሪዎች ሰምተናል። መቀሌን ጨምሮ በትግራይ ክልል ከተሞች ቀደም ብሎ በሊትር እስከ 450 ብር ድረስ ሲሸጥ የነበረ ቢሆንም፣ ካለፈው ሳምንት ወዲህ 550 ብር እየተሸጠ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

ከመደበኛ ማደያዎች ነዳጅ ማግኘት አባድ መሆኑን የነገረን አንድ የአንቡላንስ ሹፌር፣ የወላድ እናቶችን ህይወት ለመታደግ ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች መግዛት ግዴታ መሆኑን ገልጧል። በአሁኑ ወቅት መቀሌ ከተማን ጨምሮ በትግራይ ክልል በየመንገዱ ጀሪካን ደርድሮ ነዳጅ መሸጥ መደበኛ የገበያ አማራጭ መሆኑንም ጠቁሟል።

ሌላኛው በቱሪዝም አገልግሎት ላይ የተሰማራ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት፣ አልፎ አልፎ ጎብኝዎች ሲያገኝ ነዳጅ የሚገዛው ከሕግ ወጥ ነጋዴዎች መሆኑን ተናግሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውድ ዋጋ የሚገዛው ነዳጅም እንደልብ እየተገኘ ባለመሆኑ፣ ለመቆም የተገደዱ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ያስረዳል።

በትግራይ ክልል የነዳጅ ግብይት በአመዛኙ ወደ ሕገ ወጥ አሰራር መሸጋገሩን ተከትሎ፣ የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ አዲስ የትራንስፖርት የታሪፍ ጭማሪ አድርጓል። ቢሮው የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን በምክንያትነት ጠቅሶ ባወጣው አዲስ የትራንስፖርት ታሪፍ፣ የ100 ፐርሰንት ጭማሪ ማድረጉን ዋዜማ የተመለከተችው ደብዳቤ ያመላክታል።

ምንም እንኳን ቢሮው የ100 ፐርሰንት ታሪፍ ጭማሪ ቢያደርግም፣ የትራንስፖርት እጥረት መኖሩን ምንጮች ገልጠዋል። ያለው ውስን የትራንስፖርት አገልግሎትም ቢሮው ካደረገው ጭማሪ በላይ በተጋነነ ዋጋ የሚገኝ ነው ተብሏል።

ቤኒሻንጉል ጉምዝ

ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የመንገድ መዘጋት ወትሮውንም፣ ሕገ ወጥ የነዳጅ አቅርቦት ስር በሰደደበት ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። በክልሉ ባለፈው ሳምንት፣ በሕገ ወጥ ገበያ ናፍጣ በሊትር እስከ 600 ብር ድረስ መሸጡን ኹለት የአሶሳ ከተማ ባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።

በክልሉ መዲና አሶሳ ከተማን ጨምሮ በየከተሞቹ ያሉ አብዛኞቹ ነዳጅ ማደያዎች መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ። በክልሉ ወትሮውንም ከመደበኛው ገበያ በላይ ነዳጅ የሚሸጥ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በዚህ ልክ የተጋነነ ዋጋ ታይቶ እንደማይታወቅ ምንጮች ጠቁመዋል።

በጋምቤላ

በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በከፍተኛ ደረጃ ደርቶ፣ አንድ ሊትር ናፍጣ እሰከ 370 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ለሕገ ወጥ ግብይት የተጋለጠ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተው ግጭት ሁኔታውን አባብሶታል ተብሏል።

አማራ

በአማራ ክልል በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ ከሰሞኑ በተከሰተው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት፣ በሕገ ወጥ መንገድ አንድ ሊትር ናፍጣ እሰከ 170 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። የሕግ ወጥ ነዳጅ ገበያ ዋጋው ክልሉን ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች በሊትር እሰከ 350 ብር ድረስ እንደሚሸጥ ዋዜማ ተረድታለች።

ደቡብ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ

ከጊዜ ወደ ጊዜ ተስፋፍቶ በቀጠለው ሕገ ወጥ የነዳጅ ገበያ በአንጻራዊነት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው አካባቢዎች አሉ። እንደ ደቡብ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች የሕግ ወጥ ገበያ ዋጋው ከሌሎች ክልሎች አንጻር እምብዛም የተጋነነ አይደለም።

እንደ ሲዳማ ክልል ባሉ ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች አንድ ሊትር ናፍጣ እስከ 200 ብር ድረስ በሕገ ወጥ ገበያ ይሸጣል። በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ ናፍጣ በሊትር እሰከ 175 ብር ድረስ እንደሚሸጥ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የመደበኛ ነዳጅ አቅርቦት እጥረት፣ በተመሳሳይ የሕገ ወጥ ገበያ ዋጋ ንረት ተከስቷል። ችግሩ በተለይ የግጭት ቀጠና በሆኑ የወለጋ አካባቢዎች የሚስተዋል ሲሆን፣ ናፍጣ በሊትር እሰከ 350 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው።

በተለያዩ ክልሎች የቅርቦት እጥረት በተመሳሳይ ጊዜ በተከሰተበት ባለፈው ሳምንት፣ አንዳንድ ማደያዎች ነዳጅ የለንም በሚል አገልግሎት እየሰጡ እንዳልነበር አሽከርካሪዎች ጠቁመዋል። አንዳንድ ማደያዎች አስቀድሞ ሲጠበቅ ከነበረው የመጋቢት ወር ዋጋ ጭማሪ፣ ተጨማሪ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ መደበቃቸውን እንደሚያውቁም ተናግረዋል።

ባለፉት ተከታታይ ቀናት ነዳጅ የለም በሚል ተዘግተው የነበሩ ነዳጅ ማደያዎች፣ ከጭማሪው በኋላ ትላንት ማክሰኞ ከስዓት በኋላ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ተብሏል።

የሕገ ወጥ ነዳጅ ግብይት ዋጋ መናር የተከሰተው፣ መንግሥት አዲስ የአቅርቦትና ስርጭት አሰራር ለመተግበር በተዘጋጀበት አጋጣሚ ነው።

የአቅርቦትና ስርጭት ችግሮችን ይቀርፉል በሚል ተዘጋጀው አዲስ አሰራር፣ የገበያ ድርሻ ድልድል ላይ የተመሰረተ ነው። በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው የተባለው አዲሱ አሰራር የሚተገበረው፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በሚያወጣው አካባቢዊ የድርሻ ድልድል ነው። [ዋዜማ]