Bekele Gerba

ዋዜማ ራዲዮ- በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራሮች የረሀብ አድማ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ መታመማቸው እና ላንድማርክ በተባለ የግል ሆስፒታል ለመታከም መጠየቃቸው ይታወሳል።


በመንግስት ሆስፒታል ነው መታከም ያለባቸው በማለት ይህን ጥያቄ እና የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ይሁንታ የተቃወመው ጠቅላይ አቃቤህግ ለጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኝ ብሎ ነበር።
ይህን ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት የካቲት 16 ቀን 2013ዓም የላንድማርክ ሆስፒታል ፍቃደኝነትን እና ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የህክምና ሞያው በሚፈቅደው ደምብ መሰረት የሀኪሞች ቡድን በማደራጀት ተከሳሾች ባሉበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሄዶ ሙሉ ህክምና እንዲሰጥ ወስኖ ነበር።


ይሁን እንጂ ላንድማርክ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎቼን ነቅዬ ማረሚያ ቤት ድረስ ሄጄ አላክምም በማለት ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል።


የተከሳሾች ጠበቆችም ደምበኞቻቸው ወደ ሆስፒታሉ ተወስደው ለመታከም እንዲፈቀድላቸው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ (አርብ) የይግባኝ አቤቱታ አስገብተዋል።[ዋዜማ ራዲዮ]