ዋዜማ ራዲዮ- ከዕለታት አንድ ቀን ሪቻርድ ፓንክረስት በቸርችል ጎዳና ሲያዘግሙ አንዱን የሊሴ ተማሪ አስቁመው “ገብረማርያም ማን ነው?” አሉት፡፡ ልጁም አሰብ አርጎ “ምን አልባት ትምህርት ቤቱ ያረፈበት መሬት ባለቤት ይሆናል” አላቸው፡፡ ሪቻርድ በተማሪው መልስ ተገርመው አዲስ ትሪቡን መጽሔት ላይ አንድ መጣጥፍ ጻፉ፤ TheFrench Lycee; Who Was Geberemariam? የሚል፡፡ ይኼ የኾነው በፈረንጅ 2003 አካባቢ ነው፡፡ ሰሞኑን ተመሳሳይ ይዘት አንድ ባለ 205 ገጽ መጽሐፍ ተመረቋል። በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን ጨምሮ ብዙ ታዳሚዎች ተገኝተው ነበር፡፡
ሊሴ የአርበኛ የልጅ ልጆች ቤት ነው፤ ከድሮም ጀምሮ፡፡ አሁንም ድረስ ከሊሴ ተማሪ አንድ እጅ የሚኾነው በቅድመ አያቱ አርበኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለምሳሌ የቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ የልጅ ልጆችና መላው ቤተሰባቸው እዚያ እንደተማሩ አውቃለሁ፡፡ ይሄ ትምህርት ቤት የተቋቋመው በ 1936 ዓ.ም ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ የኢትዮ ፍራንሴ ወዳጅነት ማኅበር ሲጠናከር የትምህርት ቤቱ ስም ሊሴ ገብረማርያም ተባለ፡፡ ይሁንና ትምህርት ቤቱ በይፋ የተመረቀው በ1944 ነው፡፡ ንጉሱ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ተወካይ ሆነው ከመጡት የአንደኛው ዓለም ጦርነት ጀብደኛ ከሙሴ ረኔ ማየር ጋር በመሆን እነ አቴጌ መነን፣ እነ ልዑል አልጋ ወራሽ፣ እነ ልዑል መኮንን በተገኙበት መርቀው ከፈቱት፡፡
ሊሴ ሳይከፈት በፊት ንጉሱ ተማሪዎቻቸውን ወደ እስክንድሪያ እየላኩ ያስተምሩ ነበር፡፡ እዚያ ሊሴ ፍራንኮ የሚባል ትምህርት ቤት አለ፡፡ ከዚያ የተማሩ አገራቸው እየተመለሱ ይሾሙ፤ ወይም ለሌላ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ሦስተኛ አገር ይላኩ ነበር፡፡ የሊሴ ገብረማርያም መከፈት ይህን ሂደት በከፊል አስቀረ፡፡ ተማሪ ቤቱ እንደተከፈተ በእንግሊዝኛ ነበር ትምህርት የሚሰጠው፡፡ በ1939 በንጉሡ በጎ ፍቃድ ወዳጅነትን ለማጠናከር ለፈረንሳዮች ተላልፎ ሲሰጥ ግን በፈረንሳይኛ ቋንቋ ማስተማር ቀጠለ፡፡
ገብረማሪያም ጋሪ ጎዳና
ሙሉ ስማቸው ነው፤ እስከነአያት፡፡ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ጎዳና፡፡ በሐረር ከተማም በስማቸው ጎዳና ተሰይሞላቸዋል፡፡ ጠላትን በፈረስ ሲያርበደብዱ የኖሩ አርበኛ ስለሆኑ አባ ንጠቅ ገብሬ በሚለው ስም ነው ይበልጥ የሚታወቁት፡፡ አባታቸው አቶ ጋሪ ጎዳናና እናታቸው ወይዘሮ ሌሎ ጉቴ ያወጡላቸው ስም ደግሞ ገሜሳ የሚል ነው፡፡
የእኚህን ድንቅ አርበኛ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ነው በሊሴ የተመረቀው፡፡ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት በስማቸው የመኾኑ ሚስጥርም ይኸው ነው፡፡ መሬት የሚያርድ አርበኛ መኾናቸው፡፡
ጣሊያንን በ22 ዓመታቸው አድዋ ላይ ገጠሙት፡፡ ከ40 ዓመት በኋላ የመርዝ ጋዝ ይዞ ሲመጣ ደግሞ በ62 ዓመታቸው ሲዳሞ ላይ ጠበቁት፡፡ እዚያ ከራስ ደስታ ዳምጠው ጋር አብረው አርበደበዱት፡፡ ጣልያን ገድሎ ከቀበራቸው ከ11 ወራት በኋላ እንኳ በሕልሙ እየመጡ ያባነኑት ይመስል ሬሳቸውን አስቆፍሮ አስወጥቶ በደንብ በሚያውቋቸው ባንዳዎች እርሳቸው ስለመሆናቸው አስመስክሮ ማረጋገጫ ለማግኘት መሞከሩም ይነገራል፡፡ የእኚህን ስመጥር አርበኛ ታሪክ ከሚዘክረው ከዚሁ መጽሐፍ ንባባችን በጥቂቱ እናጫውታችሁ።
የእምዬ ምንሊክ ምርኮኛ
ለወላጆቻቸው 13ኛው ልጅ የኾኑት ገብረማርያም አገምጃ በሚባል አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ የባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) አገር ነው፡፡ ደጃዝማች ባልቻና የደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪ የአንድ ቀዬ ልጆች ናቸው፡፡ ሁለቱም በአጼ ምንሊክ ጦር የተማረኩና ለከፍተኛ ማዕርግ የደረሱ ሰዎች ነበሩ ፡፡
ገብረማርያም እድላቸው ኾኖ ዘመንፈስ ቅዱስ በሚባሉ የምንሊክ የጦር መሪ በምርኮ ተይዘው በቀጥታ በመቆርቆር ላይ ወደነበረችው አዲሳባ ወደ የምትባል ከተማ ተወሰዱ፡፡ ከአዲሳባ ቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ተሻገሩ፡፡ እዚያ ገሜሳ የሚለው ስማቸው ገብረማርያም በሚባል የክርስትና ስም ተቀይሮ ወደ ምንሊክ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ገቡ፡፡ ከዚያም ለአገራቸው ሰው ለባልቻ ሳፎ ተሰጡ፡፡ ያኔ አባ ነፍሶ የምንሊክ በጅሮንድ ነበሩ፡፡ ዛሬ የባንክ ገዥ እንደምንለው ማለት ነው፡፡
አባነፍሶ ገብረማርያምን የቤተመንግሥት ሥርዓት በማስተማር ቆፍጣና ወታደርና ብቁ አስተዳዳሪ አደረጓቸው፡፡ የጦርና የአስተዳደር ጥበባቸውን ሳይሰስቱ መገቧቸው፡፡
ገብረማርያም በ22 ዓመታቸው ከባልቻ ጋር አድዋ ዘመቱ፡፡ 25ሺ ሰው በአንድ ጀምበር ባለቀበት ውጊያ ገብረማርያም ብቃታቸውን አስመሰከሩ፡፡ በአድዋ ድል ማግስት ለፊታውራሪነት በቁ፡፡ የያኔው ጄኔራል ደጃዝማች ባልቻ የሲዳሞ ገዢ ኾነው ሲሾሙ ፊታውራሪ ገብረማርያም አብረዋቸው ወደዚያው ተጓዙ፤ ልዩ ረዳታቸውም ኾኑ፡፡ ለ11 ዓመታት ሲዳሞ በቆዩበት ወቅት አስተዳደሩን በመንግሥታዊ መዋቅር መልክ ማስያዝ የግዛቱን ሰላም ማረጋገጥ ዋነኛ ተግባራቸው ነበር፡፡ ደቡብ ላይ ስማቸው ገነነ፡፡ ከዚያም በኋላ ደጃዝማች ባልቻ ወደ ሐረርጌ ሲዛወሩም ቢኾን ፊታውራሪ ገብረማርያም አልተለዩዋቸውም፡፡
ተፈሪ ልዑል አልጋ ወራሽ ኾነው ሲገኑ በአጋፋሪነት ወደ ቤተመንግሥት ተመለሱ፡፡ ተፈሪ በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር ራስ ሆነው አልጋ ወራሽ ከተደረጉ በኋላ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ቢሆንም የሐረር ገዢነታቸውን አልለቁም ነበር፡፡ እንደራሴ በመወከል ያስገዙ ነበር፡፡ በእንደራሴነት ከተመደቡ የወቅቱ መኳንንትም መካከል አንዱ ገብረማርያም ነበሩ። በ1922 ዓ.ም ፊታውራሪ ገብረ ማርያም ጋሪ ጎዳናን በደጃዝማችነት ማዕረግ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ አድርገው ሾሟቸው፡፡
የብዙዎች ውለታ በተረሳበት አገር ገብረማርያም ጋሪ የሚዘክራቸውን በማግኘት ታድለዋል መለት ይቻላል፡፡ ቸርችል ያለው ሊሴ ገብረማርያም በስማቸው ነው፡፡ ሐረርም በስማቸው የተሰየመ ጎዳና አለ፡፡ የዛሬን አያድርገውና ቀብሪደሐር የሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል በእርሳቸው ስም ተሰይሞም ነበር፡፡ ንጉሱ ናቸው ከስደት ሲመለሱ ይህን ለግራዚያኒ ማረፊያ ጣሊያን ገንብቶት የነበረውን ትልቅ ቤት ሆስፒታል አድርገው በደጃዝማች ገብረማርያም የሰየሙት፡፡ ስሙ አሁን ከስሞ እንዲሁ ቀብሪ ደሀር ሆስፒታል ይባላል፡፡
ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የኢትዮጵያ ወጣቶች የጀግንነት ማኅበር፣ የኢትየጵያ ሕዝብ የአገር ፍቅር ማኅበርን እንዲሁም የኢትዮጵያን ቀይ መስቀል ማኅበር በኢትዮጵያ ዉስጥ በመመሥረት ሂደት ዉስጥ አይነተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የወልወል ጦስ
የአድዋ ጦርነት ሲነሳ የዉጫሌ ስምምነት እንደሚነሳው የሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ሲነሳ የወልወል ግጭት አይረሳም፡፡ የያኔው የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ከጣሊያን ጋር ሲደራደሩ የወራሪዎቹ ተወካይ ሲኞር መምቤሌ ለድርድር ካቀረባቸው 3 ነጥቦች የመጀመርያው የሐረሩ ገዢ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ወልወል ምሽግ ሄደው በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የጣሊያንን ጦር አዛዥ ይቅርታ ይለምኑ የሚል ነበር፡፡ ጣሊያን ወልወልን የኔ ግዛት ነው ማለቱ ነበር፡፡ ገብረማርያም ተቆጡ፡፡ ያኔውኑ ጦር መስበቅ አማራቸው፡፡ንጉሡ ለማይቀረው ጦርነት እቅድ ሲነድፉ ከጀርመን መሳርያ ግዢ በምስጢር ፈጽመዋል፡፡ ይህን ያስፈጸሙትም ገብረማርያም ናቸው፡፡
አባ ንጠቅ ገብረማርያም በዘመናቸው መጨረሻ ያደረጉት ታላቅ ጀብድ ጣሊያንን መፋለም ነበር፡፡ ከሲዳሞ የጀመሩ በሔበኖ የጨበጣ ዉጊያ አድርገዋል፡፡ በዋደራ፣ ነገሌ ቦረና፣ ይርጋለም፣ ዶሎ፣ በተፈሪ ኬላ ወንዶና ዲላ መካከል የሞት ሽረት ትንቅንቅ አድርገዋል፡፡ የፍሰሐ ገነት ጦርነትም የሚዘነጋ አልነበረም፡፡ በዚህ ሁሉ ጦርነት ሻቃ በቀለ ዋያና ራስ ደስታ ዳምጠው አብረዋቸው ነበሩ፡፡
በቃል ያለ ይረሳል…
እንዲህ ትውልድ የዘነጋውን አርበኛ መዘከር ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ መረጃን ማጠናቀር እንዴት አድካሚ እንደሆነ የገባበት ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ የደጃዝማች ገብረማርያምን ታሪክ በማሰባሰብ ሂደቱ ቀላል ነው ባይባልም የኚህን ትልቅ አርበኛ ታሪክ በመጽሐፍ እስከዛሬ አለመኖር የማይታመን ነው፡፡
መጽሐፉ ሙዳየ ቃላት ተሰናድቶለት የንጉሡን ዘመን የማዕረግ ስሞች ለማብራራት የተደረገው ጥረት ለብዙ አንባቢዎች ትልቅ ርዳታ ነው። በፊታውራሪና በቢትወደድ፣ በነጋድራስና በበጅሮንድ፣ በቀኝ እዝማችና በደጃዝማች መሐል ያለውን የትርጉምና የግብር ልዩነት የሚረዳው አንባቢ በጣም ጥቂት ነው። የመጽሐፉ አዘጋጆች አቶ አረጋ ኃይለሚካኤል በ1960 ዓ. ም. ለኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ባችለር ዲግሪ ማሟያ ባቀረቡት ጥናት ውስጥ የሚገኘውን የቃላት መፍቻ በመጽሐፉ ቀዳሚ ገጾች ላይ ማስቀመጣቸ ያስመሰግናቸዋል።
መጽሐፉ በሁለት ዋና ምዕራፍ ተዋቅሯል፡፡ አንዱ የሕይወት ታሪካቸውን ይተርካል፤ ሌላኛው ደግሞ ከቤተሰባቸው የተገኙ አስገራሚ ታሪካዊ ሰነዶችን አባሪ አድርጓል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ የተነሱ ፎቶዎች ውድ የታሪክ ቅርሶች ናቸው፡፡ ከቤተሰብ ሳጥን ወጥተው በዚህ መጽሐፍ ታትመዋል፡፡ የታሪክ ሰነዶች በሚለው ምዕራፍ አባሪ የተደረጉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ማኅተም ያረፈባቸው፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ቪዛ የተመታባቸው፣ የእቴጌ መነን የደብዳቤ ራስ (ሄደር) የተረገጠባቸው፣ የጸሐፊ ትእዛዝ ወልደ መስቀል የመጀመርያ ቲተር የታተመባቸው፤ የንጉሠ ነገሥቱ ቅንጡ ፊርማ ወዘተ በራሱ ታሪክ ይተርካል፡፡ ጦማሮቹ የደጃዝማች ገብረማርያም ብቻ አይደሉም፡፡ ከፈረንሳይ ሌጋሲዮን ጋር በተደረገ ወዳጅነት በጅቡቲ ላይ የኢትዮጵያ ቆንስል ኾነው የተሾሙት የልጃቸው ልጅ ተፈራ ገብረማርያም ደብዳቤዎችም አሉበት፡፡ ልጃቸውም የድሬዳዋ ገዢ ነበሩ፡፡
ከመጽሐፉ አስደናቂ ነገሮች አንዱ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሕይወት ከነበሩ ሕያው ምስክሮች የተገኙ መረጃዎችን ማካተቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ሻምበል ጌታቸው ኃይለሚካኤል የደጃዝማች ገብረማርያም የእህት ልጅ ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1919 ሲሆን ጣሊያን ሲገባ የ8 ዓመት ልጅ ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ደጃዝማችን ተከትለው በየዱሩ ተንከራተዋል፤ ፡፡ በተአምር ከዚያ ጦርነት ተረፉ፡፡ የመጽሐፉ ዝግጅት እየተደረገ በ2003 ነሐሴ ላይ አረፉ፡፡ ለመጽሐፉ ግብአት በርካታ የቃል መረጃ የተገኘውም ከርሳቸው ነበር፡፡ ለአብነት ሻምበሉ በማስታወሻቸው ካሰፈሩትና መጽሐፉ ዉስጥ ከተካተተው መሐል ይህን እንየው ፡፡ የዱር የገደሉን የአርበኝነት ሕይወት በተለይም አርበኞቹ ሕጻናት ልጆቻቸውን ሳይቀር ይዘው በየዱሩ የሚንከራተቱበትን ምክንያት እንዲህ አድርገው ገልጸውታል፡፡
ጣሊያን አርበኛን ይወጋል፤ ባንዳው ደግሞ የአርበኛውን ቤተሰብ ይወጋል፡፡ የአርበኛውን ቤተሰብ የወጋ ባንዳ ጣሊያን አዛዦች ዘንድ መቅረቢያ ይሆነዋል፡፡ እንደ አርበኛው ትልቅነትም ቤተሰቡ ግዳይ ተጥሎ ይፎከርበታል፡፡ ጣሊያን ደግሞ የአርበኛን ቅስም የሚሰብረው ቤተሰቡን እያሳደደ እጁ ሲገባም እያሰቃየ ነው፡፡ ..የአርበኛ ቤተሰብ የበረሀውን ሐሩር፣ የሌቱን ቁር፣ መርዛማ እባቦችንና ጊንጦችን ተቋቁሞ፣እንደ ወታደር ደግሞ የጠላት አውሮፕላን ቦንብና መርዙን መድፉንና ታንኩን ተጋግሎ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡
አዛውንቱ እንደሚናገሩት የራስ ደስታ ዳምጠው ቤተሰቦች በሙሉ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ ባህርማዶ በመውጣታቸው ራስ ደስታ በአርበኝነት ዘመን የቤተሰብ ጭንቀት አልነበረባቸውም፡፡ በአንጻሩ ደጃዝማች በየነ መርዕድ ባለቤታቸውን ልእልት ሮማነ ወርቅ ኃይለሥላሴን (የንጉሠ ነገሥቱ ልጅ) እና ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አውደ ውጊያ ገብተው ሲፋለሙ ኖረዋል፡፡ ደጃዝማች በየነ ከተገደሉ በኋላ ባንዳው ቤተሰቦቻቸውን አንገላቶ በቀጥታ ለጣሊያን አሳልፎ ሰጠባቸው፡፡ በባንዳዎች ከፍተኛ መጉላላት የደረሰባቸው ልዕልት ሮማነ ወርቅ ኃይለሥላሴ ሕይወታቸው ሮም በኢጣሊያን እስር ቤት ዉስጥ አልፏል፡፡
ስለዚህ አርበኛ ቤተሰቡን የት አድርጎ ነው ላገሩ ክብር የሚፋለም፡፡ መንደሩን ሁሉ የባንዳ ዐይን ገብቶታል፡፡ ያ ክፉ ቀን እስቲወጣ ቀን የጨለመው ለኢትዮጵያ ክብር ዱሩን ቤቱ ላደረገው አርበኛ ብቻ አልነበረም፤ ኢትዮጵያን በቅጡ ለማያውቋት የአርበኛ ልጆች እና እናቶቻቸውም ጭምር እንጂ፡፡
በየመንደሩ እየተለቀሙ ለጣሊያኖች እየተሠጡ ካለቁት እና በየበረሃው የቦንብ እና የመርዝ ጋዝ ሰለባ ከሆኑት መካከል በአምላክ ቸርነት በሕይወት ተርፈን ታሪኩን ለቀሪው ትውልድ ለማስተላለፍ የበቃነው ጥቂቶች ነን፡፡
ይላሉ ሻምበል ጌታቸው።
“የምትጣፍጥ ሞት መጣች”
ደጃዝማች ደቡብ ላይ ሲፋለሙ ቆይተው ከብዙ ፍልሚያ በኋላ ቆሰሉ፡፡ ቆስለውም አላረፉም፡፡ ከደቡብ የተነሱ ተንፏቀው እስከ ትውልድ አገራቸው አገምጃ ድረስ ዘለቁ፡፡ የጣልያን ጦር ሲከባቸውና ጦርነቱ የመጨረሻቸው እንደሆነ ሲያውቁ እንዲህ ተናገሩ፣
ዛሬ ሰርጌ ነው፡፡ለዉድ አገሬ ለሰንደቅ ዓላመው ግዳጄን ፈጽሜ ሕይወቴን አሳልፋለሁ፡፡ ከዚህ እልፍ አልልም፡፡ የመጨረሻ ትግሌ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል፡፡ ጠላት እጄን አይጨብጥም፡፡ የምትጣፍጥ ሞት መጥታለች፡፡
ከዚህ ንግግር በኋላ የወንድማቸውን ልጅ ሻቃ በቀለ ዋያን መርቀው ካሰናበቱ በኋላ ባካሄዱት ከፍተኛ ፍልሚያ ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ፡፡ የካቲት 18፣ 1929፡፡