ዋዜማ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሠራተኞቹ ዛሬ ሊሰጠው አቅዶ የነበረው አወዛጋቢው የመጀመሪያ ዙር የብቃት መመዘኛ ፈተና መሰረዙን ዋዜማ ሰምታለች።
ለፈተና የተመረጡት ሠራተኞቹ በአውቶቡስ ወደ ፈተና ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ሲጠባበቁ እንደነበር ለዋዜማ ተናግረዋል።
ዳግማዊ ሚኒልክ ት/ቤት የፈተና ጣቢያ ሊፈተኑ የነበሩ አንድ ሰራተኛ የተወሰኑ ሰራተኞች ስም ዝርዝር ብቻ በመፈተኛ ክፍሎች እንደተለጠፈ ለዋዜማ ገልጸዋል። ፈተናው ሊሰጥባቸው በነበሩ ሌሎች ሶስት ቦታዎችም መሰረዙን ከተፈታኞች ስምተናል።
በቦታው ፖሊሶች ብቻ ስለነበሩ ለምን እንደተሰረዘ የሚናገር አካል እንዳልነበርም ተናግረዋል።
አርብ ማምሻውን የአዲስ አበባ አስተዳደር ባወጣው መግለጫየምዘና ፈተናውን ለመስጠት የተመረጡት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ኮተቤ ዩኒቨርስቲ፣ የብቃት ምዘናውን ያልሰጠነው የቴክኒክ ችግር ስላጋጠመን ነው ማለታቸውን አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ፣ የብቃት መመዘኛ ፈተናውን የሚሰጠው አዲስ የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት ባደረጉት የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች እንደሆነ ገልፆ ነበር። ስለምዘናው ዝርዝር መረጃ በዚህ ማስፈንጠሪያ ያገኛሉ
በትናትናው ዕለት ተቃዋሚው እናት ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ሠራተኞች ሊሰጠው ያቀደው ምዘና እንዲኹም በምዘናው የሚሰጠው የሠራተኞች ምደባ ባስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።
ፓርቲው፣ ፈተናና ምዘናው መንግሥት የማይፈልጋቸውን ሠራተኞች በማስወገድ የሚፈልጋቸውን ለመተካት ኾን ብሎ ያዘጋጀው ስልት መኾኑን ለመገመት አያዳግትም ብሏል። ከፈተናው በፊት የፈተናው መልስ በየትምህርት ቤቶች አስቀድሞ ተለጥፎ መገኘቱን ከመረጃ ምንጮቹ መረዳቱን የጠቀሰው ፓርቲው፣ ይህን ተከትሎ ፈተናው ለጊዜው መቋረጡን እንደደረሰበት ገልጧል።
ፓርቲው፣ በአዲስ አበባ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እየሠሩ የሚገኙ ሠራተኞች የብሄር ማንነታቸውን እንዲሞሉ የሚያስገድደው ቅጽ ባስቸኳይ እንዲቆምም ፓርቲው ጠይቋል። በዚኹ መግለጫው፣ የከተማዋ አስተዳደር ሠራተኞች የፈተና አሰጣጡን፣ ምደባውንና “ብሄር” የሚጠይቀውን ቅጽ በሰላማዊ መንገድ እንዲቃወሙ ፓርቲው ጥሪ አድርጓል። [ዋዜማ]
To reach Wazema editors, you can write to wazemaradio@gmail.com