ዋዜማ- ከትራፊክ ፖሊስ ክስ ቅጣት ጋር ለኦሮሚያ ሚሊሻ መዋቅር ድጋፍ በሚል ተጨማሪ 5 መቶ ብር በግዳጅ እንድንከፍል እየተገደድን ነው ሲሉ የተለያዩ አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ወይም ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ አገራት የሚጓዙ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የክሱ መጠን ምንም ያህል ቢሆን ለሚሊሻ ጽ/ቤት ድጋፍ በሚል ተጨማሪ 5 መቶ ብር መክፈል ግድ እንደሆነ ለዋዜማ አስረድተዋል።

የክሱን ገንዘብ በሚሰጣቸው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ካስገቡ በኋላ፣ ያስገቡበትን ደረሰኝ ይዘው የመንጃ ፈቃዳቸውን ለመውሰድ ወደ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት በሚያቀኑበት ወቅት፣ ድጋሚ ለሚሊሻ ድጋፍ ከፍላችሁ ተመለሱ እንባላለን ሲሉ የአከፋፈል ሂደቱን ይናገራሉ።

የሚሊሻ ጽ/ቤት ድጋፍ የተባለው ይኸው ክፍያ በሲንቄ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ብቻ የሚከፈል መሆኑን የሚጠቅሱት አሽከርካሪዎቹ፣ ክፍያውን ፈጽመው ደረሰኙን ለመንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት ሲያስረክቡ ብቻ የመንጃ ፈቃዳቸውን መውሰድ እንደሚችሉ ያወሳሉ።

የተባለውን የሚሊሻ ድጋፍ 5 መቶ ብር ከፍለው ደረሰኙን ለጽ/ቤቱ ከሰጡ በኋላ ግን ጽ/ቤቱ ምንም አይነት የገቢ ደረሰኝ ለአሽከርካሪዎቹ እንደማይሰጥ ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት መረዳት ችላለች።

ይህንኑ ጉዳይ ለማስፈጸም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀናት ከሥራ ገበታቸው ውጪ እንደሚሆኑና ሂደቱን ለመጨረስ ያለው መጉላላት አስልቺ እንደሆነ በብሶት ያነሳሉ።

በሌላ በኩል በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በየኬላው ላይ በሚቆሙ የጸጥታ ኃይሎች “የኮቴ” በሚል 5 መቶ ብር ለመክፈል መገደዳቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ለአብነትም ከአማራ ክልል ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ የሚያቀና አንድ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ ያሰበበት እስኪደርስ ስድስት የፍተሻ ኬላዎች ቢኖሩ 3 ሺሕ ብር የመክፈል ግዴታ አለበት ሲሉ አብራርተዋል።

ዋዜማ ከቀናት በፊት በኦሮሚያ ክልል ከእርሻ መሬት ዓመታዊ ግብር ጋር ተዳብለው በሚመጡ ሌሎች ክፍያዎች ከአቅም በላይ ለሆነ ወጪ መዳረጋቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን አነጋግራ አንድ ዘገባ ማስነበቧ ይታወሳል

አርሶ አደሮቹ መደበኛ ዓመታዊ የእርሻ መሬት ግብር 1 መቶ ብር እንደሆነ፣ ሆኖም አብረው ከሚመጡ ሃያ በላይ ክፍያዎች ጋር ሲደመር ግን 6 ሺሕ ብር አካባቢ የሚጠጋ ገንዘብ ለመክፈል መገደዳቸውን ለዋዜማ አስረድተው ነበር።

ከእርሻ መሬት ዓመታዊ የግብር ክፍያ ጋር አብረው ተዳብለው የሚመጡት እነዚሁ ከሃያ በላይ ክፍያዎች በተለያዩ ስሞች የታተሙ የክፍያ ደረሰኞች ሲሆን ከእነዚሁ ክፍያዎች አንዱ ይኸው ለሚሊሻ ጽ/ቤት ድጋፍ የሚለው ተጠቃሽ እንደሆነ ዋዜማ ከቀናት በፊት አስነብባ እንደነበር ይታወሳል። [ዋዜማ]