ዋዜማ ራዲዮ- የብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞችን ከማንኛወም የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆንና በመሰል የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በቅስቀሳ ላይ መሳተፍ የሚከለክል አንቀጽ የተጨመረበት ረቅቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀረበ፡፡
የሚንስትሮች ምክርቤት መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ተወያይቶ ለፓርላማው የመራው የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።፡፡
ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም በፓርላማው ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ረቂቅ አዋጅ የተቋሙ ሰራተኞች የመረጃና ደህንነት ስራ ስምሪት የተለየ ዝግጁነትና የህይወት መስዋዕትነት የሚጠይቅ የሙሉ ጊዜ ስራና አገልግሎት በመሆኑና ሰራተኖች አገልግሎቱ በሚመድባቸው ማናቸውም ቦታና ጊዜ የተሰጣቸውን ግዳጅ የመወጣት ሃላፊነት የተጣለባቸው በመሆኑ ሰራተኞቹ በሌላ ገቢ በሚያስገኝ ስራ እንዳይሰማሩ ገደብ ይጥላል፡፡
በዚህም በየጊዜው ከሚፈጠር የኑሮ ውድነት አንጻር በተልዕኮ አፈጻጸም ላይ ጫና እንዳይፈጥር ለማድረግ፣ ሰራተኞችን ለማቆየትና ሌሎችም ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ ያስችላል የተባለውን የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚያስችል አሰራርን በአገልግሎቱ በኩል ተጠንቶ ለመንግስት በማቅረብ እንዲፈቀድ እንደሚያደርግ ረቂቁ ይደነግጋል፡፡
የአገልግሎቱ ሰራተኞች የስራ ስምሪት የፓራ ሚሊታሪ ባህሪ ያለው በመሆኑና የተለየ ዝግጁነት የሚያስፈልገው መሆኑ፣ ሰራተኞች ልዩ ስነ-ምግባርና እንደሚጠበቅባቸው፤ አዳዲስ በሚቀጠሩና በነበር ሰራተኞች ላይ በተለየ መልኩ የደህንነት ማጣራት እንደሚደረግባቸው፣ የምልመላና የቅጥር፣ የሙከራ ጊዜ፣የዝውውር እንዲሁም የተለየ የስንብት ስርዓት እንደሚኖር በረቂቁ ተብራርቷል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የአገልግሎቱ ሰራተኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በስራው አጋጣሚ ወይንም በስራ ስምሪቱ ያወቃቸውንና ያገኛቸውን ማንኛውም መረጃና ሰነድ ወይንም ሪከርድ የተደረገ መረጃ ምንጭ ያለአገልገሎቱ ዋና ዳይሬክተር እውቅ መግለጽ በህግ እንደሚያሰጠይቅ አዲስ አንቀጽ ተካቶበታል፡፡
የመንግስትን የፀጥታና የደህንነት ሪፎርም መሰረት በማድረግ እንደተዘጋጀ የተገለጸው ይህ ረቂቁ አዋጅ ብሄራዊ የደህንነት ስጋቶችን ወቅታዊና አፋጣኝ በሆነ መልኩ የተማከለ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ያግዛል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ የመረጃ ሚሰጥራዊነት ደረጃ ለማስቀመጥና እንደ አስፈላጊነቱ መረጃዎች ከሚስጥራዊነታቸው እንዲወጡ ይፈቅዳል፡፡
ምክርቤቱ ረቂቁን ተመልክቶ ለዝርዝር አይታ በዋናነት ለህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች መርቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]