IMG_0814

መስፍን ነጋሽ (ዋዜማ ራዲዮ)

ከአንዳንድ ሰዎች ጋራ የሆነ ቀጠሮ ያላችሁ ይመስላችኋል። ቀኑና ሰዓቱ የማይታወቅ ቀጠሮ። ሰሎሞን ዴሬሳ ለእኔ ከእዚያ ብጤ ሰዎች ቁንጮው ነበር። ባገኘው የምነግረው የሆነ ልዩ ነገር ኖሮኝ፣ አለያም እርሱ ብቻ የሚመልሰው ጥያቄ ገጥሞኝ አይደለም። ብቻ እንዲሁ በድጋሚ የማየው የማገኘው ይመስለኝ ነበር። ደሞ ኮ ያልተቆረጠ ቀጠሮም ሰጥቶን ነበር። “ተጨማሪ ጥያቄ ካለ፣ ለብስለት መገኘት ዋዜማ እንቃጠርና…” ብሎ ነበር የ“ዘበት እልፊቱ”ን መግቢያ ሲያሳርግ። ከዚህ ወዲያ የገጣሚ ቀጠሮ ከየት ይመጣል?! ለብስለት መገኝት ዋዜማ! ሰሎሞን መብሰሉ አሌ አይባልም። ምናልባት እኔ ከመብሰል ዋዜማ ሳልደርስ ቀርቼ ይሆን ያልተገናኘነው? ምናልባት። ወይስ ቀጠሮው የአካል አልነበረም? ምናልባት።

ሰሎሞን ብስለት የሚለውን ጭብጥ በተለያየ ቦታ ያነሳዋል። “አንዳፍታ” በሚለው ግጥሙ

እውንና እውቀት ከሆኑ አንዳፍታ
ውበትና ሞት ሃላፊ እንደ ሽታ፣
ከምስጢር ጓሮ ጉድጓድ ቆፍሩላት
ፍቅርን አግዘናል መስከን ትመልሳት።

“ብስለት” የሚል ርእስ የተሰጠው ሌላው ግጥሙ ደሞ እንዲህ ይላል።

ባዶ ሆዴ ስፋቱ
የንዳዴ ነዲድ ጥማቱ
ጭንቅላቴ ባዶነቱ ልቤ ቅንነቱ!
ጨግጎ
ሊበትን እንፋሎቱ
እኔን ብሎ ብስለትን ማንሳቱ።

የሰሎሞን ቀጠሮ ስንት ዕድሜ፣ ስንት ሕይወት ይፍልግ ይሆን?

እጅግ ከሚመስጡኝ የሰሎሞን ንሸጣዎች አንዱ በዕድሜና በሕይወት መካከል ያለውን ግንኙንት የሚጠይቅበት ነው። አንድ ዕድሜ እና አንድ ሕይወት አቻ ናቸውን የሚል ሐሰሳ ይመስላል። ዘበት እልፊቱ ውስጥ ካልተሳሳትኩ ሁለት ጊዜ አንስቶታል።

ርእሱ ጥያቄ ምልክት (?) ብቻ በሆነው ግጥሙ፥

“?
በልግ ክረምት ጸደይ በጋ
አንድ ዕድሜ ላንድ ሕይወት ላይበቃ?” ሲል ይጠይቃል።”

አንባቢ አንድ ዕድሜ ስንት ነው? አንድ ሕይወትስ ምን ያህል ነው ብሎ መጠይቁ አይቀርም። መልሱ ገጣሚው ዘንድ የለም።

“አንቺን” በተሰኘው ግጥም ደግሞ ይህንኑ ጉዳይ በሌላ መቼት ያነሳዋል።

አንቺን ላየ አንድ ዕድሜ ላይበቃ
ያቃጠለኝ ጥማት ባረቄ ላይረካ
ፋኖ ልምታሽ ፋኖ ማታ
ልጣበቅሽ እስክነቃ።

IMG_0815አንድ ዕድሜ ለአንድ ሕይወት ይበቃል ወይ ማለትን ምን አመጣው? የሚል የሰሎሞን ብጤ “ተንኮለኛ ወለጌ” መሆን አለበት። በሰሎሞን ግጥሞች ውስጥ የምመለከታት ሕይወት “ለጊዜያዊ ትግል ስፍራንን የመመጠን” ትግል አድርጌ ነው፤ እርሱው ራሱ በ“ልጅነት” “እሽቅድምድም” (መግቢያ) ውስጥ ስለግጥም ቅርጽ እንደሚለው።

“ህጻን ለቲንስ እጁ እንኳ መጠለያ የማትሆን፣ ቡችላ ገፍቶ የሚጥላት፤ ካፊያ አጥቦ የሚወስዳትን ቤት ካልቦካ ጭቃ የሚሰራው ለጊዜያዊ ትግሉ ስፍራን ለመመጠን ሳይሆን አይቀርም።” (ልጅነት)
ሰሎሞን የሕይወትን እና የግጥምን ተፈጥሮ ተቀራራቢ አድርጎ የሚመለከት ይመስላል። ለምሳሌ በዚሁ የ“ልጅነት” መግቢያው ላይ ሕይወት እና ግጥምን ተለዋዋጭ ቃላት አድርጎ የተጠቀመበትን አንድ ቁልፍ ኅይለ ቃል መጥቀስ ይቻላል። “ህይወት (ግጥም) እንዳንዳንድ ጥያቄ በየትውልዱ ብቻ ሳይሆን በየተወላጁ ተመላላሽ ናት” ይላል።

ሰሎሞን፣ ስለግጥም ቅርጽ ሲከራከር ቄንጠኛ የብስክሌት አንዳድን በምሳሌነት ባመጣበት መንገድ፣ ሕይወትም እንደዚያው በራሷ ግብ ሆና “ለውበቷ” የሚጨነቁላት ነገር ሆና ትታየው ይሆን? ይመስለኛል። ወይም፣ እኔ ሕይወትን እንዲዚያ እንደመለከታት ጋብዞኛል። የተቀበልኩት ግብዣ ነው።

ከግጥሞች ተነስቶ የሰሎሞንን ሕይወትና አስተሳሰብ እረዳለሁ ብሎ ማሰብ ወደ ስሕተት ሊመራ እንደሚችል የመጽሐፎቹን መግቢያዎች ያነበበ ሁሉ የሚገነዘበው ነው። የእኔም ሙክራ በሰሎሞን ግጥሞች ውስጥ የራሴን ሐሰሳ ማድረግ እንጂ ደራሲውን መበየን አይደለም። ለዚያውም መሞቱን ስሰማ በጫጫርኩት በዚህ የስንብት ማስታወሻ።

ሰሎሞን የሚጋብዛቸው ጥያቄዎች ማለቂያ የላቸውም። በሐሳብ ለመወሰድ አንድ ሐረግ ወይም ስንኝ ለሚበቃቸው ብጤዎቼ፣ ሰሎሞን ከገጣሚነቱ ባልተናነሰ፣ በራሱ ቋንቋ፣ ነሻጭነቱ የትም የማይገኝ ነው። አንድ የግሌና የቅርቤን ምሳሌ ልስጥ። “ዘበት እልፊቱ ወለሎታት” ምስጋና ባቀረበበት “እጅ መንሻ”ው ላይ ልጁን ሲያመሰግናት “በባእድ አገር ላሳድጋት ስፍጨረጨር ላሳደገችኝ ልጄ፥ ለገላኔ ዴሬሳ” ይልላታል። ዕጹብ እንጂ ምን ይባላል?! ልጅ ሲያሳድጉ አብሮ የማደግ ውለታን አስታውሶ መኖር ድንቅ ነው። እኔም እንዳቅሜ ልጄን በየቀኑ ሳገኛት በልቤ ይህን ምስጋና ሳልሰጣት የዘለልኩበት ቀን የለም፤ ዕድሜ ለሶሎሞን።

ለሰሎሞን ስንት ዕድሜ ይበቃው ነበር? ሰማንያ። ይኸው ነው።

በቀረውስ፤ በሰሎሞን ዴሬሳ አገላለጽ “ጊዜን ላንዳፍታ ቆም ማድረግን፥ ለማስተዋል፥ ለመሳቅ፥ ለመተከዝ ፋታ ማግኘትን የማይመኝ ማን አለ? አንዲት ደቂቃ ባታልፍኮ ዘላለም ትሆናለች።”

አንድ ዕድሜ ላንድ ሕይወት ላይበቃ?