ዋዜማ- በግዢ ሒደት ላይ ከሚገኙ 6 የጭነት  መርከቦች ሁለቱ በተያዘው ዓመት ስራ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ  የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ለዋዜማ ተናግረዋል።

የሚገዙት መረከቦች  ኮንቴነሮችን፣ ብትን ጭነቶችን እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ (multipurpose) መርከቦች መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

የወደብ ይዞታዎችን የማልማት፣ ማስተዳደር እና አገልግሎት የመስጠት ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ፤ በሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን አራት ድርጅቶች ውህደት ፈጽመው የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።

እነዚህ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማህበር፣ የባህርና ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት፣ የደረቅ ወደብ አግልግሎት ድርጅቶች እና ኮሜት ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ናቸው።

ተቋሙ የሀገሪቱን ከ 90 በመቶ በላይ የወጭ እና ገቢ ንግድ የሚያስተናግድ መሆኑን የገለጹት አቶ ደምሰው፤ከዚህ ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያ በራሷ መርከቦች የምታስተናግድ ሲሆን ቀሪውን ደግሞ በኪራይ መረከቦች እንደምታጓጉዝ አብራርተዋል።

በባለፈው የጥቅምት ወር  የሚኒስትሮች ምክር ቤት  የመቶ ቀናት ግምገማውን ባደረገበት ወቅት፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ  አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ያሏት መርከቦች 10 ብቻ መሆናቸውን የወጭ እና የገቢ ንግድ “ሙሉ በሙሉ” የማያስተናግዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህ ሳቢያ ሀገሪቱ ከሌሎች ድርጅቶች መረከብ በመከራየት የወጭ እና የገቢ ንግዷን እንደምታከናውን አብራርተዋል።

ለኢትዮጵያ የመርከብ አገልግሎት ከሚያቀርቡት ዓለም አቀፍ የመርከብ ድርጅቶች ውስጥ “ሜዲትራኒያን ሺፒንግ ካምፓኒ”፣ “መረስክ”፣ “ሃፓክ ሊዮይድ” የተሰኙት ይገኙበታል። 

“የኢትዮጵያን ገቢ እና ወጪ ንግድ የሚያጓጉዘው የኢትዮጵያ መርከብ ብቻ አይደለም። በቂ ስላልሆነ ማለት ነው። ኢትዮጵያ ያላት መርከቦች በጣም ትንሽ ናቸው 10 ናቸው። ኢትዮጵያን የምታክል ሀገር ገቢ እና ወጪ ንግድ ሙሉ ለሙሉ የሚያስተናግዱ አይደለም። የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ  ከሌሎች ድርጅቶች መርከብ እየተከራየ ነው የሚጭነው” በማለት ሚኒስትሩ ያለውን የጭነት መርከብ ቁጥር ማነስ አስረድተዋል።

ሀገሪቱ ካሏት “ብትን ጭነት አገልግሎት” የሚሰጡ 10 መርከቦች ውስጥ ዘጠኙ 27 ሺህ ቶን የሚጭኑ ናቸው። “ዓባይ ሁለት” የተሰኘችው እና በ2015 ዓ.ም ስራ የጀመረችው መርከብ ከ 63 ሺህ ቶን በላይ የመጫን አቅም ያላት መሆኑን ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ  የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው ገልጸዋል።

ግዙፍ የጭነት መርከቧ የተገዛችው፤ “ባህርዳር” እና “ሐዋሳ” በተሰኙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ምትክ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁለቱ መርከቦች “የመጫን አቅማቸው አነስተኛ” እና “አትራፊ መሆን ያልቻሉ” መርከቦች በመሆናቸው ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ አሁን ካሉት መርከቦች “ተጨማሪ እንዲገዙ ታዝዘው በሂደት ላይ ነው ያለው” ሲሉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ በዘንድሮ ዓመት 6 የተለያዩ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ መርከቦች እንደሚገዙ የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው ገልጸዋል። ከነዚህ የጭነት መርከቦች ውስጥ ሁለቱ በዚህ ዓመት ስራ እንደሚጀምሩ ለዋዜማ ነግረዋታል። 

“የመርከብ ግንባታ በባህሪው ከ 2 እስከ 3 ዓመት ስለሚወስድ 2 መርከቦች በተያዘው የበጀት ዓመት ግዥ ተፈጽሞ ወደ ስራ የሚገቡ ሲሆን ሌሎቹ ሂደታቸውን ጠብቀው የሚገቡ ይሆናል” በማለት አስረድተዋል። የሚገዙት አዲስ መርከቦች የመጫን አቅማቸው ከ 63 ሺህ ቶን በላይ እንደሆነም ገልጸዋል። [ዋዜማ]