Book Cover-Blaten Geta Hiruy

መጽሐፉ ለኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ የመጀመርያ ሥራ ነው ተብሏል

ዋዜማ ራዲዮ- ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በአውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉትን ጉዞ በስፋት የሚቃኘው ይህ መጽሐፍ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ርዕሱም ‹‹የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ (1903 ዓ.ም)›› የሚል ነው፡፡ በሽፋኑ ከንቲባ ገብሩ፣ ነጋድራስ አስቤ፣ ደጃዝማች ካሳ እና ቀኛዝማች ብስራቴ ተደርድረው የሚታዩበትን ታሪካዊ ፎቶን የያዘ ነው፡፡ የመጠቁም ቅጠሎቹን ጨምሮ 302 ገጾች ያሉት ይህ ዓይነግቡ መጽሐፍ ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት የተባዛ ነው፡፡ ዋጋውም በአንድ መቶ ሐምሳ ብር ተተምኗል፡፡

በጀርባ የሽፋን ገጽ ላይ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለና ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ በመጽሐፉ ዙርያ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን አሰናጁ ባሕሩ ዘውዴ በበኩላቸው ‹‹የኅሩይ ወልደ ሥላሴን የጉዞ ትረካ ዝርዝር ሁኔታን በሚያስገርም ምልአትና ጥንቃቄ የዘገበ›› ሲሉ ያሞካሹታል፡፡

የታሪክ ኢምሬትስ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ በበኩላቸው ስለ መጽሐፉ በሰጡት አስተያየት ‹‹ከመቶ ዓመት በላይ ሳይታወቅ የቆየን ሰነድ አርትኦት ተደርጎበት፣ በምርምር ላይ የተመሰረተ የግርጌ ማሰብራሪያ ዳብሮ፣ ታሪካዊ አውዱን የሚገልጽ ሰፊ መግቢያ ታክሎበት…›› በዚህ መንገድ ለአንባቢ መቅረቡን አሞካሽተዋል፡፡ የዚያ ዘመን ኢትዮጵያዊያን አውሮፓን እንዴት እንዳዩት የምንረዳትበት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ክብርና ሉአላዊነት ላይ በወቅቱ የነበረን አስተሳሰብ ለመገንዘብም ኾነ ዘመናዊነትን ለማጥናት መነሻ የሚኾን ጥሩ ሰነድ ነው ሲሉም መጽሐፉን ገልጠውታል፡፡

የመጽሐፉ አሰናጅ ባሕሩ ዘውዴ ለመጀመርያ ጊዜ የረቂቁ ቅጂ ያገኙት ከታሪኩ መሪ ተዋናይ ከነበሩት የደጃዝማች ካሳ የልጅ ልጅ ከዶክተር አስፋ ወሰን ዐሥራተ ካሣ ዘንድ እንደነበር በመግቢያቸው አስታውሰዋል፡፡ ይህም በ1994 ዓ.ም ፕሮፌሰር ባሕሩ ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ በነበሩበት ወቅት የኾነ ነው፡፡

ኾኖም የሰነዱን ኦሪጅናል ቅጂ ማግኘት የቻሉት ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የልጅ ልጅ ከወይዘሮ እምዩ ተክለማርያም እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ “…ተግዳሮቶችን ተቋቁሜ ያገሩን ታሪክ ለማወቅ ከፍ ያ ጉጉት እያደረበት ለመጣው ኢትዮጵያዊ  ይህን የመሰለ ታሪካዊ ሰነድ ሳላቅርብለት ቢቀር ሕሊናዬ ይወቅሰኛል›› ሲሉ መጽሐፉን ያሰናዱበትን አግባብና አነሳስ አብራርተዋል፣ ፕሮፌሰር ባሕሩ፡፡

መጽሐፉ በዘጠኝ ክፍሎች የተሸነሸነ ሲኾን ከጉዞ ዝግጅት ጀምሮ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ፣ ከጅቡቲ እስከ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ግብጽ፣ እየሩሳሌምን ካሰሰ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመልስ ጉዞን ያደርጋል፡፡ ከቋንቋ አንጻር ዶክተር ፈቃደ አዘዘ የድሮ ቃላትን ተመጣጣኝ ፍቺ በማቅረብ እገዛ ማድረጋቸው በምስጋና ገጽ ተመልክቷል፡፡ በመጽሐፉ የኋላ ገጽም የቃላት ፍቺ የዋቢ ምንጮች ዝርዝርን ቀድሞ ተቀምጧል፡፡

ቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ዳይሬክተር የነበሩት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ የሚመሩት የኢትዮጰያ ሳይንስ አካዳሚ ከዚህ በኋላ በርካታ ፋይዳ ያላቸው ኅትመቶችን እያሰናዳ ለአንባቢ የሚያቀርብ የፕሬስ ክንፍ ማቋቋሙና ይህን ክፍል በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በማደራጀት ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡ የፕሬስ ክፍሉ በጊዝያዊነት ደራሲ እንዳለጌታ ከበደን ጨምሮ የመጻሕፍት አርታኦት ሥራ ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ደቦጭን ያካተተ ነው፡፡