Facebook Logo
Facebook Logo

ፌስቡክና ጉግል በመጪው የፈረንጆች ዓመት የኢንተርኔት አገልግሎት ለደሃ አገራት በነጻ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን እቅድ እያስተዋወቁ ነው። እነኚህ ትልልቅ የኢንተርኔቱ ዓለም ድርጅቶች የሚያስተዋውቁት በነፃ ኢንተርኔት የማቅረብ እቅዳቸው በአንድ በኩል 2/3ኛ የሚኾነውን ኢንተርኔት ያልደረሰበትን የዓለም ክፍል ከቀረው ዓለም ጋር የማገናኘት ትልቅ ሙከራ ተደርጎ ቢቆጠርም በሌላ በኩል ግን ከትችት አላመለጠም።

የፌስቡክ ፈጣሪና ዋና ስራ አስኪያጅ ማርክ ዙከርበርግ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ ድርጅቱ ሲያዘጋጀው የቆየውን ይህንን ኢንተርኔትን በነፃ የማዳረስ እቅድ ይፋ ሲያደርግ በድኅነት የሚማቅቀው ዝቅተኛው የዓለም ሕዝብ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚኾን ገልጾ ነበር። ዓለም የበለጠ በመረጃ ሲተሳሰር የተሻለ ዓለም ይኖረናል በሚል እሳቤ ላይ እንደተመሰረተ የሚነገርለት የፌስቡክ እቅድ አቀራረቡ ሰብዓዊ ርዳታን ለ3ኛው ዓለም አገራት ማድረስን የመሰለና ለትርፍ ያልተጀመረ ፕሮጀክት አስመስሎታል።

(መዝገቡ ሀይሉ ዝርዘር ዘገባ በድምፅ አሰናድቷል፡ አድምጡት)

አሁን አፍሪካ ላይ ትኩረት ያደረገው የኢንተርኔት አቅርቦት ዩቴልሳት ከሚባለው ፈረንሳዊ የቴልኮም ኩባንያ ጋር በጋራ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው። ለዚሁም አገልግሎት ሲባል ፌስቡክና ዩቴልሳት AMOS 6 የተባለ ሳተላይት ወደኅዋ ያመጥቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ፌስቡክ ከዚሁ አግልግሎት ሲባል የሰራውን ግዙፍ ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮን ለመረጃው ፍሰት አቀባባይ አድርጎ የመጠቀምም እቅድ አለው።

ይህ የፌስቡክ ኢንተርኔትን በነፃ የማዳረስ ውጥን Internet.org ተብሎ የተሰየመው አዲሱ የድርጅቱ እቅድ አንድ አካል ነው። እስካሁንም ድረስ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያና በጥቂት የአፍሪካ አገሮች አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ነበር። ይሁንና እስካሁን በነበረው የሙከራ ጊዜ ከብዙ የኢንተርኔቱ ተጠቃሚዎች በተለይም ከሕንድ የገጠመው ተቃውሞ ጠንከር ያለ ነበር።
የተቃውሞው ምክንያት ሁለት መሰረታዊ ጉዳይዕች ላይ ያተኮረ ነው። የመጀመሪያው መሰረታዊ ጉዳይ በቅርቡ በብዙ አገራት ተቀባይነት እያገኘ የጸደቀው Net Neutrality ወይም የበይነ መረብ ገለልተኝነት ሕግ ነው። በሕንድ 800 ሺህ ሕዝብ በጻፈው የአቤቱታ ማመልከቻ እና 68 የመናገር ነጻነት መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባቀረቡት ግልጽ ደብዳቤ መሰረት ይህ የኢንተርኔት ዶት ኦርግ ፕሮጀክት የበይነ መረብ ገለልተኝነት ሕግን የማያከብር ባህርይ አለው ተብሎ ተከሷል።
ይህ የፌስቡክ አዲስ ፕሮጀክት ይጥሰዋል ተብሎ የሚነቀፍበት የበይነ መረብ ገለልተኝነት የሚባለው ሕግ ዋነኛው ድንጋጌ ከንግግርና ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ የሰብአዊ መብቶች ጋር ተዛማችነት ያለው ነው። በሕጉ መሰረት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የኢንተርኔት መረጃን ለደምበኞቻው ሲያቀርቡ በምንም መልኩ መድልዖ እንዳያድርጉ ያግዳል። ክፍያ በሚደረግባቸው እና በማይደረግባቸው የኢንተርኔት መረጃዎች እንዲሁም የኢንተርኔት የመረጃው ምንጭ የኾኑ አገሮች ወይም የጂኦግራፊ ክልል ሳይመረጥ ሁሉም የኢንተርኔት ፍሰት ወይም ትራፊክ በእኩልነት እንዲስተናገድ ያስገድዳል።

አሁን ፌስቡክ የጀመረው የኢንተርኔት አቅርቦት ግን በብዙ መልኩ የተገደበ መረጃ ነው። አቅርቦቱ የሚይዘው ፌስቡክንና ከፌስቡክ ጋር ስምምነት የፈጠሩ ጥቂት የመረጃ ምንጮች ብቻ በነፃ እንዲሰራጩ መደረጉ እና የኢንተርኔት አገልግሎቱን የሚያሰራጩት የቴሌኮም ኩባንያዎች የሚፈልጉትን የመረጃ አይነት ብቻ የማሰራጨት ወይም የማይፈልጉትን የመገደብ መብት የሚሰጥ ባህርይ እንዳለው ተጠቁሞ ትችት ቀርቦበታል።

በሁለተኛ ደረጃ ለትችት ያጋለጠው ጉዳይ፤ ከዚህ በፊት ፌስቡክ ይከሰስበት የነበረውን የደምበኞቹን መረጃ አሳልፎ የመስጠት ችግር ነው። ኢንተርኔት ባልደረሰባቸው በድኅነት በተጠቁ አካባቢዎች የሚደርሰው ይህ የፌስቡክ ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት፤ በዚህ በአዲሱ የኢንተርኔት ዶት ኦርግ መድረክ ውስጥ እንዲካተቱ የሚፈቀድላቸው የመረጃ ምንጮች ለፌስቡክ የመረጃ ስብሰባ ግብአት እንዲኾኑ ያስገድዳል። ከዚህም አልፎ ፌስቡክ የሚሰበስባቸውን መረጃዎች አብረውት ለሚሰሩ የቴሌኮም ኩባንያዎች እና መንግስታት አሳልፎ የመስጠት ነፃነትንም ይሰጠዋል።

ይህ የዚህን የፌስቡክ ፕሮጀክት መጀመር ለሰብአዊ መብትንና ለዲሞክራሲ አጋር ይኾናል የሚለውን የብዙዎች ምኞት የሚቃረን ኾኖ እንዲታይም አድርጎታል። የዜጎቻቸውን የኢንተርኔት የመረጃ ልውውጥ ለሚሰልሉና ለሚቆጣጠሩ አምባገነን መንግስታት ተጭማሪ ርዳታን የሚሰጥ እንዳይኾንም ተሰግቷል።

ከዚሁ የፌስቡክ የኢንተርኔት አቅርቦት ጋር የሚመሳሰለው የጉግል ፕሮጀክት ጉግል ሉን ይባላል። በብዙ መልኩ ከፌስቡኩ ፕሮጀክት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢኾንም የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ ግን የተለየ ነው። እንደፌስቡክ ሁሉ ጉግል ሉንም በመጪው የፈረንጆች ዓመት በብዙ የዓለም ክፍሎች በስራ ላይ እንደሚውልም ይጠበቃል።
ጉግል ሉን ኢንተርኔቱን የሚያሰራጨው እንደ ፌስቡክ ሳተላይት በማምጠቅ አይደለም። ሳተላይት ከማምጠቅ የተለየ ርካሽ እና አዲስ ፈጠራ ለዓለም ያስተዋውቃል ተብሎ ይጠበቃል። የጉግል የኢንተርኔት ስርጭት የሚደረገው ከምድር ከባቢ አየር ከፍ ብለው በሚለቀቁ በርካታ ባሉኖች አማካኝነት ነው። ጉግል ዝግጅቱን አጠናቋል። በውጥን ፕሮጀክትነት ሙከራ በተደረገባቸውም በኒውዚላንድና በአሜሪካ ጥሩ ውጤትን አሳይቷል።

እንደፌስ ቡክ ሁሉ ይህም የጉግል ፕሮጀክት ዒላማው ያደረገው ኢንተርኔት ላልደረሰው 2/3ኛ ለሚኾነው የዓለም ሕዝብ ኢንተርኔት ማድረስ ነው። ይህም ፕሮጀክት ስኬታማ ከኾነ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት በሁሉም የዓለም ክፍሎች በነፃ እንዲገኝ ያደርጋል።

በጉግል ሉን ባሉኖች የሚሰራጨው ኢንተርኔት ተጠቃሚዎቹ ጋር ለመድረስ እንደፌስቡክ ሁሉ በየአገሩ ካሉ መንግስታት ጋር ስምምነት ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም ጉግልን እንደፌስቡክ ሁሉ ትችት እንዲቀርብበት እና በጥርጣሬም እንዲታይ አድርጎታል። ጉግል የዚህን አገልግሎት ዓላማ ሲያስተዋውቅ መረጃና እውቀት ላልደረሳቸው በቢሊዮን ለምሚቆጠሩ የዓለም ሕዝብ መረጃን ማድረስ ብቻ ሳይኾን በመረጃ መገደብና ብብዙ አገሮች በሚደረገው ቁጥጥር ምክንያት የሚባባሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የሚያግዝ ርዳታም እንደሚኾን ተጠብቆ ነበር። ይሁንና ይህም ይጉግል አገልግሎት ከኢንተርኔትና መረጃ የራቁትን ሕዝብ ለማግኘት በየአገሩ ያሉትን መንግስታት እና የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ይኹንታ ማግኘት ይጠበቅበታል።

እንዲህ ያለ መረጃ ያለገደብ ለሕዝባቸው መድረሱን የማይወዱት እንደ ኢትዮጵያ ያሉት መንግስታት ይህን አይነት ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያለ ነፃ የመረጃ አቅርቦት እንዲመጣባቸው የሚፈቅዱ አይመስልም። ጉግል ይኹንታውን ማግኘት ቢችል እንኳን እነኚህኑ ጨቋኝ መንግስታት የሚያግዝ ተጨማሪ መሳሪያ ኾኖ እንዳያገለግል ያለው ስጋትም በተቺዎቹ ዘንድ እየተንጸባረቀ ነው።