ዋዜማ ራዲዮ- የገዥው ፓርቲ ንብረቶች የሆኑት ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት (ራዲዮ ፋናና ፋና ቴሌቭዥን)፣ ዋልታ ( ዋልታ ቴሌቭዥን) እንዲሁም በሁለቱ ድርጅቶች ጥምረት የተመሰረተው ዋፋ ፕሮሞሽን የተባለው የማስታወቂያ ድርጅት ከኢሕአዴግ ጉባዔ ተከትሎ የህዝብ ንብረት እንዲሆኑ ዕቅድ ቀረበ። የፓርቲ አባል የሆኑ የድርጅቶቹ አመራሮችም በቦታቸው እንደማይቀጥሉ ተነግሯል።

ኢህአዴግ በመስከረም ወር መጨረሻ ከሚያደርገው ስብሰባ በሁዋላ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት: ዋልታ እና ዋፋ ፕሮሞሽን ለውጡ ከሚነካቸው ውስጥ እንደሚሆኑ ዋዜማ ሬዲዮ ከቅርብ ምንጮቿ አረጋግጣለች።

እነዚህ ሶስት ተቋማት በተለይ ፋና እና ዋልታ ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት በከባድ የጸጥታ ችግር ውስጥ ባለችባቸው ጊዜያት; የሀገሪቱ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ችግር ምንጭ ነው ከሚባለው ሕወሐት ጋር በማበር በሰሯቸው የፕሮፓጋንዳ ስራዎች ትችት ይቀርብባቸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢህአዴግ ሊቀመንበር  አብይ አህመድ የሚመራው የገዥው ፓርቲ፣ በፓርቲው ባለቤትነት ስር ያሉ መገናኛ ብዙሀንን ወደ ህዝብ ድርጅትነት የማሸጋገሩ አሰራር ዝርዝር አፈፃፀሙ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ከመታዘዙ ውጪ ዝርዝሩ አልተገለጠም።

ዋልታና ፋና የአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል 25 በመቶ ድርሻ ይኑርባቸው እንጂ በሚሰሯቸው ዘገባዎች የህውሀት በጉልህ ተጽእኖ በከፍተኛ ደረጃ ያርፍባቸው ነበር።ይህ ደግሞ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ታይቷል።

በዘገባዎቻቸው  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራውን ኦህዴድ በውጭ ሀገራት ከነበሩና በወቅቱም በአሸባሪነት ተፈርጀው የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው ከነበሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ይሰሩ እንደነበር የሚያሳዩ ዘገባዎችን ሲሰሩ እንደነበር ይታወሳል።

አብይ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግን የሚዲያ ተቋማቱ በግዴታም ቢሆን የለውጥ አንቀሳቃሽ የሚባለውን አካል የሚደግፉ ዘገባዎችን ለመስራት ተገደዋል። አሁንም ቢሆን የሚዲያ ተቋማቱ ከሙያ መመዘኛ አንጻር ብዙ እንደሚቀራቸው የድርጅቶቹ ሰራተኞች ያስረዳሉ። ለዚህም ሲባል ከተቋማቱ ባለቤትነት ጀምሮ የአመራሮች ማስተካከያ እንዲደረግ ሀሳብ ቀርቧል።

ከጥቂት ወራት በፊት የዋልታ ምክትል ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ወይዘሮ አልማዝ በየነ(ሕወሐት) ከስራቸው መነሳታቸው ይታወቃል።ወይዘሮ አልማዝ በዋልታ ውስጥ ምክትል ስራ አስፈጻሚ የነበሩ ቢሆንም ከዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተተካ በቀለ (ብአዴን) በበለጠ ሁኔታ ተጽእኖ በማሳረፍና ዋልታን የህውሀት አጀንዳ ማስፈጸሚያ አድርገውት እንደነበርም ይታወቃል።ወይዘሮ አልማዝ ከዋልታ ምክትል ስራ አስፈጻሚነት ከተነሱ በሁዋላ ተቋሙ የለውጥ ሀይል እየተባለ ለሚጠራው የሀገሪቱ ፖሊቲከኞች ያዳላ ዘገባን በመስራት ተጠምዷል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ለረጅም አመታት በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ወልዱ ይመስልም   ከብሄራዊ ድርጅታቸው ሕወሐት አባልነት መታገዳቸው ተሰምቷል።የታገዱበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

በርካታ የሕወሐት አመራሮች አቶ ወልዱ በያዙት ሀላፊነት እናት ድርጅታቸውን አልረዱም እንዳውም ለለውጥ ሀይሉ ጋር የማጎብደድ አዝማሚያ ታይቶባቸዋል በሚል ያብጠለጥሏቸዋል። ፋናን ለረጅም አመታት የመሩትና ድርጅቱን ባማሳደግ ቁልፍ ሚና ያላቸው አቶ ወልዱ ቀለም ጠገብ የህግ ባለሙያ ናቸው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ፋና የሕወሐት አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዲሆን በማድረግ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አቶ ወልዱ ተቋማቸው የተቃዋሚ ፖርቲ አባላት አሸባሪ ናቸው በሚያስብል ደረጃ የሚያብጠለጥሉ ዘገባዎችን ሲሰራ ነበር በሚል ይተቻል።በሀገሪቱ ባለፉት አመታት የነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን የሁከትና የአሸባሪነት ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ፍላጎት ተደርጎ እንዲዘገብ አቶ ወልዱ የሚመሩት ጣብያ በእጅጉ ሰርቷል። አቶ ወልዱ በ2007 አም ምርጫ ወቅት አንድነት ፓርቲ ላይ ያነጣጠረ አፍራሽ ዘገባ እንዲሰራ በማድረጋቸውም ስማቸው ይነሳል ።

ዋፋ ፕሮሞሽን የፋናና የዋልታ ስብጥር የሆነ በበርካታ የማስታወቂያ፣ የንግድ ትርዒት እንዲሁም ሁነት በማዘጋጀት የሚሰራ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ተቋም ነው።