Jule 3ዋዜማ ራዲዮ- ስድስት ኪሎ የሚገኘው ‹‹ገተ-ጀርመን የባሕል ማዕከል›› በዚህ ሰሞን ቤተ-መንግሥታዊ ጥበቃ ሳያስፈልገው አልቀረም፡፡ ይህ ማዕከል ለአንድ ወር ይዞት የሚቆየው ንብረት ከማዕከሉ ማዶ ከሚገኘው የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ከሚገኝ የገንዘብ ክምችት የማይተናነስ ሊሆን ይችላል፡፡ በማዕከሉ ለአንድ ወር የሚቆዩት 17ቱ የጁሊ ምህረቱ የሥዕል ሥራዎች ወደ ገንዘብ ብንቀይራቸው በትንሹ ከአምስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ልንመነዝራቸው እንችላለን፡፡

በድምፅ የተሰናዳውን ዘገባ መዝገቡ ሀይሉ ያቀርበዋል አድምጡት፣ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

በአሜሪካ የፋይናንስ ቀውስ ጋር ተያይዞ ስሙ በበጎ የማይነሳው የ‹‹ጎልድመን ሰክስ›› የፋይናንስ ተቋም በሥሩ 32ሺ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ግዙፍ የንዋይ ኩባንያ ነው፡፡ ኒውዮርክ የሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ዋና መግቢያ ላይ ግዙፍ የሥዕል ሥራ ለማሠራት ሲያቅድ የመጀመርያ ምርጫው ጁሊ ነበረች፡፡ እርሷ ሥራውን ሠርቶ ለማስረከብ 2 ዓመታትን ወስዶባታል፡፡ ‹‹ሚዉራል››የተሰኘው ይህ ሥራዋ ለግዙፍ ኩባንያ እንደመሠራቱ፣ እንደ ሥዕሉ ግዝፈት ሁሉ ግዙፍ ክፍያን አስገኝቶላታል፡፡ 6 ሜትር በ26 ሜትር የሚሆን መጠን ያለው ‹‹ሚወራል›› አንድ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወደ ጁሊ ኪስ አስገብቷል፡፡

ያም ሆኖ ጁሊ ነጋዴ አርቲስት የምትባል አይደለችም፡፡ ጥሎባት ግን ሥራዎቿ ከፍተኛ ሲሳይን የሚያመጡ ናቸው፡፡ በዓለም ስመጥር ሚዩዚየሞች እንዲሁም የሥዕል ስብስብ በማከማቸት የሚተዳደሩ ደላሎች የጁሊን ሥራዎች አድነው ይገዛሉ፡፡ ይህ እውነታ ጁሊን የዚህ ዘመን የዓለማችን 7ኛዋ ከፍተኛ የሥዕል ሻጭ አርቲስት ያደርጋታል፡ ፡
የጁሊ የሥዕል ሥራዎች ወትሮም በግዝፈታቸው ይታወቃሉ፡፡ በቁመናቸው ከአደባባይ ትልልቅ የማስታወቂያ ቢልቦርዶች የማይተናነሱ ናቸው፡፡ ለርሷ ሥራዎች የሚመጥኑ የሥዕል አውደ ርዕይ ማሳያዎች የሌሏት አዲስ አበባ አብዛኛዎቿን የጁሊ ሥራዎች ለማሳየት የተንገታገተችውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በሚዩዚየሞቻችን በሮች የቁመት ማነስ ምክንያት ወደ አገር ቤት እንዳይመጡ የተደረጉ የጁሊ ሥራዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

ግዝፈታቸው ብቻም አይደለም፡፡ የዋጋ ተመናቸውም የትየሌሌ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የጁሊን ሥዕሎች የማጓጓዣ ዋጋ አንሮታል፡፡ 17 ሥራዎቿን በአውሮፕላን ካርጎ ለማጓጓዝ የነበረው ፈተናም ቀላል አልነበረም፡፡ እነዚህን ቅቦች ከነበሩበት ቤልጅየም ወደ አገር ቤት ለማድረስ 1.5 ሚሊዮን ብር መፍጀቱ ተነግሯል፡፡ ይህ ለአገር ቤት አንዳንድ የሥነ-ጥበብ ማዕከላት የዓመት በጀት ሊሆን የሚችል የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ መረዳቷም የማጓጓዣ ወጪውን ከኪሷ ለመክፈል ሳያስገድዳት አልቀረም፡፡ ሥራዎቿን በአገሯ ለማሳየት የነበራትን ጉጉት ከፍ ያለ መሆኑን የምንረዳው ደግሞ ለሥራዎቿ የመድን ሽፋን ሰጪ አለማቀፍ ተቋማት ከሚጠይቁት አነስተኛ ቅድመ ሁኔታ ባልተሟላበት መልኩ ሥዕሎቹ ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ያደረገችው ድፍረትና ጥረት ነው፡፡ ለሥዕሎቿ የተሰጠው የመድን ሽፋን 132 ሚሊዮን ብር የሚገመት እንደሆነ ተነግሯል፡፡

 

Julie Mihretu
Julie Mihretu

የጁሊን ሥራዎች መረዳት
በ1960ዎቹ ገብረክርስቶስ ደስታ ከጀርመን መሠረታዊ የሥዕል ጥበብን ተምሮ ሲመለስ በወቅቱ ጥበቡን የሚረዳለት ዜጋ ማጣቱ ይነገራል፡፡ ከረቂቅ ሥነ-ሥዕል ዘውግ የሚመደቡት ሥራዎቹ ለአገር ቤት ተደራሲ ትርጉም አልባ በመሆናቸው በወቅቱ የነበሩ ሀያሲዎች ‹‹አታጭበርብረን›› እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡

ይህ ሁኔታ ዛሬም ብዙ የተቀየረ አይመስልም፡፡ በገብረክርስቶ ደስታ ማዕከል ሥራዎቿን ያቀረበቸው ጁሊ ምህረቱ የገብረክርስቶስ እጣ ፈንታን ለማስተናገድ ትገደዳለች፡፡ ሥዕሎቿን በቅጡ የሚያብላላ፣ አብላልቶ የሚያገናዝብ፣ አገናዝቦ የሚረዳና የራሱን ትርጓሜ ለማግኘት የሚሞክር ለሥነ ሥዕል ባዕድ ያልሆነ፣ የሥነ-ሥዕል ጥበብን ፊደል የቆጠረ (Art Litrate) ተመልካች የማግኘት ዕድሏ ሰፊ እንደማይሆን ከወዲሁ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ለዚህ ድምዳሜ መነሻ የሆኑ አያሌ አጋጣሚዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ከ2003 ጀምሮ በሸራተን አዲስ በየዓመቱ የሚዘጋጀው የደቦ ሥዕል አውደ ርዕይ የአገሪቱ ትልቁ የጥበብ ገበታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሟቹ ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስውር ረቂቅ (Abstraction) ሥራዎቸውን ባቀረቡበት አንድ ዝግጅት ወጣት ተመልካቾች ግራ በመጋባት ያንሾካሽኩ ነበር፡፡ ሥዕሎቹን ዘለግ ላለ ደቂቃዎች እንኳ ለመመልከት ጊዜ ሳይወስዱ ከርሳቸው ጋር ፎቶ ለመነሳት ረዥም ጊዜን ያጠፉ እንደነበር የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ አይዘነጋውም፡፡ ወጣቶቹ አርቲስቱ ከሣሏቸው ሥዕሎች ይልቅ ሚዲያው ስለእርሳቸው የሣለው ምስል ገዝፎባቸው ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነበር፡፡

በነዚህ ዓመታዊ የሸራተን የሥዕል አውደ ርዕዮች የብዙዎች ቀልብ የሚስቡት የመዝገቡ ተሰማ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ከሜተር አርቲስት አፈወርቅ ጋር ፎቶ የተነሡ ወጣቶች ወደ መዝገቡ ተሰማ ሥራዎች በረው በመሄድ ዘለግ ያለ ጊዜን በአድናቆት ያሳልፉ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ በመጠኑም ቢኾን የሚነግረን ዕውነታ ከስውር ረቂቅ የሥዕል ዘውግ ይልቅ ለእውናዊው የሥዕል ዘይቤ በእጅጉ የቀረበ ተመልካች ያለን መሆኑን ነው፡፡

መሠረታዊ የቀለም፣ የቅርጽና የመስመር ስሜትና ትርጉም በአንደኛ ደረጃ ትምህርትና በጠቅላላው የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት አለመካተቱ ለዚህ ክፍተት እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ተመልካቹ በእውን የሚያውቀው ነገር በፎቶ ገጭ ብሎ እስካላየ ድረስ አንድን የሥነ-ሥዕል ሥራ ለማድነቅ እንዲቸገር የራሱን አስተዋጽኦ ሳያደርግ አልቀረም፡፡

የጁሊ ወጥ ሥራዎች መለያ ቀለም ሥነ-ሕንጻን፣ ታሪክንና ፖለቲካን በሥዕል ዉስጥ አዋህዶ መተረክ ላይ ነው፡፡ የብዙዎቹ ሥራዎቿ አሻራ እነዚህን በድርብርብ ነጠብጣቦች፣ በተረጩ ዉህድ ቀለማትና በአያሌ መስመሮች ዉስጥ ፈጥሮ ስሜትን መቆጣጠር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነጋገሪያ ያደረጋትን ‹‹ካይሮ›› የተሰኘውን ሥራዋን እንደ አብነት ብንመለከት የግብጽን አብዮት መነሻ ያደረገና የካይሮን ጥንታዊውንና ዘመናዊውን ሥነ-ሕንጻ፣ የማኅበረሰቡን ፖለቲካዊ ጥያቄና አኗኗር ከቅኝ ገዢዎች ዘመን ጀምሮ የሚተርክ ነው፡፡ ‹‹ካይሮ›› የተሰኘውን ሥራ በመመልከት ብቻ በግብጽ አብዮት ስሜት መናጥ ይቻላል፡፡ በአንድ ሥዕል ይህን ሁሉ መተረክና ይህን ሁሉ ስሜት በተመልካች ላይ ማጋባት ታላቅነት ይጠይቃል፡፡ ጁሊን ታላቅ የሚደርጋትም ይህ አቅሟ ነው፡፡

Julie Mihretu
Julie Mihretu

ጁሊ ‹‹ጆሊዋ የቦሌ ልጅ››
ጁሊ ምህረቱ የኦሎምፒያ ልጅ ናት፡፡ ልጅነቷን ያሳለፈችው ቦሌ ‹‹በፒተር ፓን›› መዋዕለ ሕጻናት ነበር፡፡ ከዛሬ 38 ዓመታት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደርግ ሥልጣን ሲቆጣጠር እነ ጁሊ ከአገር ወጡ፡፡ መጀመርያ ወደ ሴኔጋል፣ በኋላም ወደ አሜሪካ፡፡

ያኔ አባቷ አቶ አሰፋ ምህረቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦግራፊ መምህር ነበሩ፡፡ እናቷም አሜሪካዊት መምህርት ናቸው፡፡ ለአንድ ዓመት ሴኔጋል ሼካንታዲዮፕ ኮሌጅ ዉስጥ ተምራለች፡፡ ከዚያም ሚቺጋን ካለመዙ ኮሌጅ ገባች፡፡ መሠረታዊ ሥነ-ሥዕልን የቀሰመችው ከሥመ ጥሩ የሮድ አይላንድ ስኩል ኦፍ ዲዛይን ‹‹ሪዝድ›› የአርት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በአሜሪካ ከኛው የአርት ስኩል መልከ አቻ ነው፡፡

ከትምህርት ቤት እንደወጣች ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውላታል ማለት ይቻላል፡፡ ለአርቲስቶች መጠለያ በማቅረብ የሥነ-ጥበብ ሕልማቸውን እንዲኖሩ የሚያስችሉ ‹‹አርት ሬሲደንሲዎች›› ዋና ዋናዎቹ ለጁሊ በራቸውን ከፍተውላታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው ሀርለም ዉስጥ የሚገኘውና ‹‹ስቱዲዮ ሙዚየም›› የሚባለው ሲሆን ይህ ስቱዲዮ በተለይም ለብዙ ጥቁር አርቲስቶች ታላቅነት ሚናው የጎላ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ጁሊ ልቅም ያለች የቦሌ ልጅ መሆኗ በዛሬ አለባበሷም የሚጎላ ነው፡፡ ቅልል ያሉ ሸሚዞችን በጂንስ ሱሪ ታዘወትራለች፡፡ ፀጉሯን በአጭሩ ትከረከመዋዋለች፡፡ ቶሎ ተግባቢ ናት፡፡ ለሚያይዋት ሁሉ ያልተቆጠበ ፈገግታን ትለግሳለች፡፡ 46 ዓመቷን የደፈነችው ጁሊ የዕድሜዋን ግማሽ ብትመስል ነው፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ወደ ትውልድ አገሯ በተለይም ወደ አክሱም ተመላልሳለች፡፡ ሥራዎቿን ይዛ ስትመጣ ግን ይህ የመጀመርያዋ ነው፡፡

የጁሊ ስኬቶች ጣሪያ
‹‹ጁሊ በዚህ ወቅት በምድራችን ከሚገኙ 5 ድንቅ ሴት አርቲስቶች አንዷ ናት›› ይላል የዚህ አውደ ርዕይ መሪ ዶክተር ዳግማዊ ዉብሸት፡፡ አላጋነነም፡፡ የዓለማችን ታላላቅ የሥነ-ጥበብ ሽልማቶች አንዱም አልቀራትም፡፡ የ2007 የበርሊን ሽልማት ከአሜሪካ አካዳሚ ኦፍ በርሊን ተቀብላለች፡፡ የ2005 ጂኒየስ አዋርድ አሸናፊ አርሷው ናት፡፡ ይህ ሽልማት አሜሪካኖች በሥነ ጥበብ ጫፍ ለደረሱና ለከበዱ አርቲስቶች የሚሰጡት ገናና ሽልማት ነው፡፡ ሽልማቱን የሚመራውም የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ነው፡፡ ሥራዎቿ በዋና ዋና ዓለማቀፍ ሙዝየሞች ዉስጥ ተካተውላታል፡፡ የአውሮፓ ከተሞችንና ዋና ዋና ሙዝየሞችን ብናካልል ጁሊ ተወክላለች፡፡
አሜሪካ ዉስጥ በየሁለት ዓመቱ በጉጉት ከሚጠበቁ የሥዕል አውደ ርዕዮች ዋናው ‹‹ዊትኒ ቢየናሊ›› ትልቁ የዘመናዊ አርት ማሳያ መድረክ ነው፡፡ ታላላቅ አርቲስቶች በደቦ ሥራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በዚህ መድረክ መጋበዝ የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ጁሊ አንዷ ነበረች፡፡ በብራዚል፣ በፈረንሳይና በሲድኒ ገናና የደቦ አውደርዕይ መድረኮች ጁሊ ገናባቸዋለች፡፡

ጁሊ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በበጎ ከሚያስጠሩ ከዋክብት አንዷ ትሁን እንጂ የአገር ቤት ሚዲያም ሕዝብም ‹‹የኛ ልጅ›› የሚላት አይነት ጀግና ሆና አታውቅም፡፡ አገር ቤት ለጆሮም ለአይንም ባዳ ናት፡፡ በፋሽን ሊያ ከበደ፣ በሳይንስ ቅጣው እጅጉ፣ በሙዚቃ አቤል ተስፋዬ እንደምንለው እንኳ ጁሊ ምህረቱ በአገር ቤት ሚዲያ የሥዕል ጌታ ሆና አታውቅም፣ ለተቀረው ዓለም ካልሆነ፡፡ ይህ የሆነው የአገር ቤት ሚዲያው ስለማያውቃት ነው፡፡ ይህ መድረክ ይህንን ገዢ ስሜት ይቀይረዋል ይላሉ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች፡፡

አንዱ ዓላማችን አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፍ የሥዕል አድናቂዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለከቱ ማስቻል ነው ይላል የዉብሸት ወርቃለማሁ ልጅ ዶክተር ዳጊ፡፡ ጁሊን ተከትለው አለማቀፍ ሚዲያዎች መምጣታቸው ተነግሯል፡፡ መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉት የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የጁሊ ተቀዳሚ ተደራሲዎች ሆነው በመክፈቻው ዕለት ልዩ ዝግ ዕይታ ተሰናድቶላቸው ነበር፡፡ በቀጣዩ ቀናትም ከአገሬው ይልቅ የሌላው አገር እንግዶች የጁሊ ተቀዳሚ ታዳሚዎች እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡

በአኗኗር ዘዬዋ፣ በሥራዎቿ፣ በግል ሕይወቷ፣ በፍቅር ጓደኛ ምርጫዋ ሳይቀር የአገሬውን ባሕል ልታስደነግጠው የምትችለው ጁሊ ምህረቱ በሥዕል ሥራዎቿም የምዕራባውያን ልብ ታሸፍት እንደሁ እንጂ የአገሬውን ትኩረት ለማግኘት የምትችልበት ዘመን የቀረበ አይመስልም፡፡