Daniel Kibret- PHOTO Credit EBS

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሀይማኖት መምህርነቱና በሚሰጣቸው ማህበራዊ ሂሶች ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመጪው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በግሉ እንደሚወዳደር ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

ዳንኤል ክብረት ምርጫውን የሚወዳደረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ለማግኘት ሲሆን ፣ የሚወዳደረውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ባለ የምርጫ ክልል መሆኑን ለመረዳት ችለናል።


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀይማኖት መምህርነቱ በስፋት የሚታወቀው ዳንኤል በርካታ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሂሶችንና ታሪኮችን የያዙ መጻህፍትን ለአንባቢያን ያደረሰ ነው። አንደበተ ርቱዕና በአማኒያን ዘንድም ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነው።


በኢትዮጵያ በ2010 አ.ም መጋቢት ወር የፖለቲካ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ዳንኤል ክብረት ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ከመሆኑም ባለፈ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሆኖም እያገለገለ ይገኛል። ከዚህ በመነሳትም ምርጫ የሚወዳደረው ብልጽግና ፓርቲን ወክሎ ነው በሚል ብዙዎች ቢገምቱም በግሉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወዳደር ነው ዋዜማ ራዲዮ የሰማችው።

ዳንኤል ክብረት መንግስትን አሁን ላይም እያገለገለ ያለው ከፓርቲ ነጻ ሆኖ በፈቃደኝነት ስለሆነ ምርጫውን በግሉ መወዳደር የፈለገው ከዚህ መነሻ መሆኑንም ነው የሰማነው።

ዳንኤል ክብረት በተለይ ከመንግስት ጋር በቅርበት መስራት ከጀመረ ወዲህ የብዙ ውዝግቦች መነሻ ሆኗል። ዳንኤልን በቀደመ የሀይማኖት ስብከቶቹና አሁንም በየመድረኩ በሚያንጸባርቀው አቋሙ “ጸረ ብዝሀነትን ያራምዳል : የቀደመ ስርአትን ይናፍቃል : ጸረ ፌደራሊዝም” ነው እያሉ የሚተቹት አሉ።

ባለፈው አመት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባልነት እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት እጩ ሆኖ ሲቀርብም በምክር ቤቱ አባላት ተመሳሳይ ትችት ሲቀርብበት ተሰምቷል።

ከትችቱ ባሻገር ዲያቆን ዳንኤል የጠቅላይ ሚንስትሩ የቅርብ ሰውና በኣአደባባይ ሙግት ስማቸው ከሚጠራ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ ነው።

ብልጽግና ታዋቂዎችን ለእጩነት ለማቅረብ እየሰራ ነው

ብልጽግና ፓርቲም ለዚህኛው አመት ምርጫ ታዋቂ ግለሰቦችን እጩ አድርጎ ለማቅረብም እየሰራ ነው።ከነዚህም ውስጥ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ይገኝበታል። ኡስታዝ አቡበከር በአዲስ አበባ ቤተል አካባቢ ብልጽግና ፓርቲን ወክሎ እንዲወዳደር በፓርቲው እንደሚፈለግ በተደጋጋሚ እንደተገለጸለት ከታማኝ ምንጮቻችን የሰማን ሲሆን ከአቡበከር በኩል ግን ለብልጽግና ፓርቲም ምላሽ አልሰጠም።

አቡበከር መሀመድ በህወሀት መራሹ የኢህአዴግ አስተዳደር ጊዜ የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ መግባት በመቃወሙ ለአመታት መታሰሩ የሚታወስ ነው።

ከጋዜጠኞችም በፋና ቴሌቭዥን የምትሰራው ሰላማዊት ካሳም ብልጽግና ፓርቲን ወክላ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት እንደምትወዳደርም ሰምተናል።

ብልፅግና ህዝብ ሊቀበላቸው ይችላሉ ያላቸውን ባለሀብቶችን ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች በማግባባት ዕጩ አድርጎ ለማቅረብ ሰፊ ዘመቻ መጀመሩንም ተረድተናል። [ዋዜማ ራዲዮ]