ከስድስት አመታት በፊት ምዝገባው የተካሄደው የ40/60 የጋራ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት አሁን ለባለ ዕድለኞች የሚወጣበት ቀን ተቃርቧል። ይሁንና ጉዳዩ ይመለከተናል በሚሉ ሶስት የመንግስት ተቋማት መካከል በዕጣው ማን ይካተት በሚለው ጉዳይ ዙሪያ መግባባት አልተቻለም። የአዲስ አበባ መስተዳድር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በመካከላቸው የተፈጠረው ልዩነት ሊፈታ ባለመቻሉ ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት አምርቷል።

Senga Tera condos site

ዋዜማ ራዲዮ- በ2005 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን የቤት መኖሪያ የቤት ባለቤት አደርጋለሁ በሚል ከነደፋቸው የቤት ልማት መርሃ ግብሮች መካከል የ40/60 መኖሪ ቤት መርሀ ግብር አንዱ ነበር፡፡ ባለፉት 6 አመታት ውስጥ በተለይ በዚህ መርሃ ግብር በሰንጋ ተራ እና በክራውን አካባቢ ከወጡት ወደ 900 አካባቢ ቤቶች ውጪ ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይታየበት ይኸው 2011 ዓ.ም አጋማሽ አመት ላይ ደርሷል፡፡

በዚህ በጥር ወር እጣ ይወጣባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ቤቶች ላይ ግን ሶስት ተቋማት ማለትም በታከለ ኡማ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል አለመግባቶች መከሰታቸውን የዋዜማ ሬድዮ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የዚህ አለመግባባት መነሻ የሆነው ደግሞ በዚህ ወር ይወጣሉ ተብለው ለታሰቡት ቤቶች በእጣው ማን ይካተት ማንስ አይካተት የሚለው ሰፊ ክርክር እና በመጨረሻም ወደ አለመግባባት ያመራ መሆኑን ነው ምንጮቻቸንን የሚናገሩት፡፡ የውዝግቡ መነሻ እንደሚታወቀው የ40/60 የቤት ልማት መርሃ ግብር ምዝገባው በሚካሄድበት ወቅት የውል አስገቢ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቤት ፈላጊዎችን ውል ሲሰጥ ካስቀመጣቸው 9 የውል ነጥቦች መካከል በተራ ቁጥር 6 ላይ የተቀመጠው የውል አንቀፅ ስለመሆኑም ተሰምቷል፡፡

ይኸው በባንኩ ውል ላይ የተቀመጠው የውል አንቀፅ፡፡ “የቤት ድልድል ቅደም ተከተሉ በደንበኞች የቁጠባ ልክ በምዝገባ ግዜ እና በእጣ የሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ለብድር ብቁ የሆኑና ከፍተኛ ገንዘብ የቆጠቡ ቅድሚያ እድል ይኖራቸዋል” የሚለው ነው፡፡ የወቅቱ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ያዘጋጀው የዚህ የቤት ልማት መርሃ ግብርን በሚያብራራበት ጽሁፉም በተመሳሳይ ይልቁንም ሃሳቡን ይበልጥ አብራርቶ ተከታዩን አስፍሯል፡፡ “ የቤት ማስተላለፉ ሂደት የሚደረገው 40 እና ከ40 በመቶ በላይ በ5 አመት ያለማቋረጥ ቆጥበው ለጨረሱ ተጠቃሚዎች ሲሆን 100 ፐርሰንት የቆጠቡ ቅድሚያ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ሌሎች ቀጥሎ በተቀመጠው ቅደም ተከተል ያገኛሉ” ይላል፡፡

በወቅቱ ምዝገባው ሲካሄድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምዝገባውን ይከታተል የነበረው የባንኩ ባለሙያ እንደሚለውም የቤት ፈላጊዎቹ ከሌላ ባንክ የነበረውን ተቀማጭ ገንዘባቸውን ወደ ንግድ ባንክ ለማዞር የነበረውን ትርምስ ያታውሳል፡፡ ደቂቃ እና ሰከንድ እንኳን በእጣ የመካተት እና አለመካተትን ይወስናሉ ተብሎ ስለታመነ የነበረውን ሩጫ እንደማይረሳው ይናገራል፡፡ ለነገሩ በመጀመሪው ዙር እጣ እንዲወጣ የተደረገባቸው የሰንጋ ተራ እና የቃሊቲ ክራውን አካባቢ ሳይቶች በዚሁ አሰራር ቀድመው 100 ፐርሰንት የከፈሉትን እጣ ውስጥ በማስገባት እንዲተላለፍ መደረጉ የሚታወቅ ነው፡፡

አሁን በዚህ አሰራር መሰረት ግን በ3 ተቋማት መካከል አለመግባባቶቹ ከፍ ብለው ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደደረሰ ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ይናገራል፡፡ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና ካቢኔያቸው ከዚህ በኋላ ቤቶቹ ላይ እጣ ለማውጣት በእጣው 40 ፐርሰንት የቆጠቡትም ሆነ 100 ፐርሰንት የከፈሉት አንድ ላይ በእጣው መወዳደር አለባቸው የሚል አቋም ይዟል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ የ40/60 የቤት ውል አስገቢ የሆነው የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ይህን ሃሳብ አጥብቆ ስለመቃወሙ ምንጮቻችን ነግረውናል፡፡ የባንኩ ምክንያት ውል አስገቢ እኔ እንደመሆኔ በወቅቱ ውሉ ሲፈጸም አንዱ ነጥብ ቅድሚያ የከፈለ በእጣው ቅድሚያ መካተትን እድል እንደሚያገኝ በውሉ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ተግባዊ አልተደረገም ማለት የባንክ አሰራሬን እምነት ያሳጣብኛል፤ ለደንበኞችም ቢሆን ቃሉን የማይጠብቅ ተቋም የሚል ስም ያሰጠኛል ሲል የከተማውን አስተዳደር ሃሳብ መሞገቱና በሁኔታው አለመስማማቱ ነው የታወቀው፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በሀሳብ በመስማማት የቆመው በሚኒስትር ዣንጥራር አባይ የሚመራው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ እንደሚለው ደግሞ በዚህ ውል መሰረት በመተማመን ቀድመው 100 ፐርሰንት የከፈሉት የቤቶቹን ግንባታ ፋይናስ በማድረግ የማይናቅ አስተዋጽኦ አላቸው የሚል ነው፡፡ የቤቶቹ ግንባታ እዚህ ለመድረሱ ይህንን ገንዘብ ቀድመው በመክፈል የሚጠባበቁ ቤት ፈላጊዎች ገንዘባቸውን ለግንባታ ተጠቅመንበት አሁን በዚህ እጣ እንደማንኛውም ቆጣቢ ትስተናገዳላችሁ መባሉ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡

በዚህ መንገድ 3ቱ ተቋማት ከመግባባት ላይ መድረስ ስላቃታቸው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር አባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ውሳኔ እንዲሰጡበት ደብዳቤ መጻፋቸውን የዋዜማ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

እስከ ህዳር 2011 ዓ.ም ባለው ግዜ ውስጥ ለ3ቱም የቤቶች አይነት ማለትም ለባለ አንድ፤ ባለ ሁለትና ባለ ሶስት መኝታ ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ 100 ፐርሰንት ክፍለው የቤቶቹን እጣ መውጣት የሚጠባበቁ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 24 ሺህ ደርሷል፡፡ በተቀራኒው ደግሞ ግንባታቸው ተጠናቆ ለእጣ የተዘጋጁት ቤቶች ቁጥር17 ሺህ 737 ቤቶች መሆናቸውን መረጃ ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ክፍያቸውን መቶ በመቶ ላጠናቀቁት እንኳን ቤቶቹን ለማዳረስ ቢታሰብ አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ማድረግ እንደማይቻል ነው፡፡

በቅርብ ቀናትም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ ማናቸውንም መግለጫ የመሰጠት ለመገናኛ ብዙሁን የማስረዳትና መስል ስራዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በቀር ማንም እንዳይገባበት ከምክትል ከንቲባው ተነግሮናል ይላሉ ሌሎች ተቋማት።

ከሳምንት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ 6 ወር ስራ አፈጻጸማቸውን ያቀረቡት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ነበዚህ አመት ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ብለው በሪፖርታቸው ያቀረቡት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቁጥር 38 ሺህ 240 መሆኑን መጥቀሳቸው አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ቤቶች ለተጠቃሚዎቹ የሚተላለፉበት አግባብ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ግን ለማወቅ የግድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ የሚጠባበቅ ይሆናል፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ያድምጡ]

https://youtu.be/0A6ZQXxv1j4