Gemshu Beyene- Photo Reporter
Gemshu Beyene- Photo Reporter

(ለዋዜማ ራዲዮ)

ጤና ይስጥልኝ፣ ጌታዬ!

ገረመው ነኝ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ፡፡ ምስጉን ጉዳይገዳይ ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባ ኩማም ያውቃል፡፡

ዉሎዬ ብሔራዊ፣ አመሻሼአብዮታዊሄሄሄ…(ምን ማለቴ እንደሆነ ይገባዎታል መቼስ!)

ላየን ባር ቤቴ፣ ቴሌ ባር ግዛቴ

ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ!! ድሮስ የፊንፊኔ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!?

እርስዎ ግን እንዴት ከርመዋል? ኸረ ለመሆኑ! ከታሳሪ ወገን ነዎት ወይስ ከአሳሪ?

አለምክንያት አልጠየቅክዎትም፡፡ ሰሞኑን ከታሳሪ ወገን የሚመደቡ ዋና ዋና ደንበኞቼ በሆነ ባልሆነው እየደነገጡብኝ ብቸገር ጊዜ ነው፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው በነዘራቸው ቁጥር ይንጰረጰራሉ፡፡ ቦርጫቸው ሳይቀር ነው የሚንዘረዘር፡፡ ይህን ጊዜ ያን የታፈነ የደላላ ሳቄን እለቀዋለሁ፡፡ ‹‹ገረመው! ምን አለ በለን ማዕበሉ ላንተም አይመለስም›› ይሉኛል፡፡ ይበልጥ እስቃለሁ፡፡ ‹‹እኔኮ የመንግሥትን አሠራር ተከትዮ ነው የምደልለው›› እያልኩ አሾፋለሁ፡፡ ‹‹ለአገልግሎቴ ቫት የምቆርጥ ብቸኛው የፊንፊኔ ደላላ ነኝ?›› እያልኩ እፎልላለሁ፣ እቀደልዳለሁ፡፡ ኾኖም አይስቁልኝም፡፡ እውነቱን ልንገርዎ አይደል? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሳቅ ያቆሙ ደንበኞቼ በዝተዋል፡፡ ከነዚህ መሐል ጋሽ ገምሹ በየነ ቦቴ አንዱ ነው፡፡

ከወር በፊት ኦፊስ ባር ተገናኝተን ነበር፡፡ የእኔ ነገር ሆኖበት እንጂ እሱ መቼ በጄ ይልና፡፡ ቢራም በግድ ነው፡፡ በዚያ ላይ ማምሸት አይወድ፡፡ ሕይወቱ ባለ አንዲት ቀጥታ መስመር ናት፡፡ ከቢሮ ቤት፣ ከቤት ቢሮ፡፡ ከካዛንቺስ መገናኛ፣ ከመገናኛ ካዛንቺስ፤ ከኢሊሌ ዘርፍሽዋል፣ ከዘርፈሸዋል ኢሌሌ፡፡ ይኸው ነው የገምሹ ሕይወቱ፡፡ መገናኛ ዘርፈሽዋል ጀርባ የገነት ቁራጭ የመሠለ ቪላ ሠርቶ፣ ዛፍ ተክሎ፣ በወፍ ዝማሬ ታጅቦ ይኖራል፡፡

ምን ዋጋ አለው ታዲያ! ሰሞኑን የወፍ ሳይሆን የፀረ ሙስና ጫጫታ እየረበሸው ቢቸገር ጊዜ ገለል ሳይል አልቀረም፡፡

የሚገርም እኮ ነው ጌታዬ?

ገምሹ 2 ካሬ ላይ በተንጣለለ በዚህ መኖርያ ቤቱ፣ 9 መኝታ ቤት፣ ሦስት ሳሎን፣ አምስት መታጠቢያ ቤት፣ አንድ ባር፣ አንድ ካፌ፣ ዘመናዊ ላውንደሪና አንድ ቤተ መጻሕፍት ይገኛል፡፡ በዚህ ገነተ ልዑልን በሚያስንቅ ቪላው ታዲያ ካንድ ልጁ ጋር ነው የሚኖረው፡፡ ቢሊዮን በተሻገረ ሀብቱ አንዲት እምቦቀቅላ ነው ማፍራት የቻለው፡፡ ይቺን ውድ የስለት ልጁን ‹‹ኢሊሌ›› ሲል ሰይሟታል፡፡ ‹‹ውብ ጨረቃ›› እንደማለት ነው ባፋን ኦሮሞ፡፡ ገና ድክ ድክ የምትል ድምቡሽዬ ሕጻን እኮ ናት፡፡

መገናኛ ዘርፈሽዋል ጀርባ ከሚገኘው ከዚሁ መኖርያ ቤቱ ማዶ ‹‹ላዮን ሀርት›› በሚባል አካዳሚ ፊደል ትቆጥራለች፡፡ እሱ ዶላር ይቆጥራል፣ እሷ ፊደል ትቆጥራለች፡፡ እሱ በስሟ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ይገነባል፣ እሷን በኮከብ አልባ ትምህርት ቤት ያስተምራታል፡፡ ገምሹ ሌንጨወለጋ እንዲህ ነው እንግዲህ!

ሕጻን ኢሊሌ ብቸኛ የአካሉ ክፋይ ትሁን እንጂ እንደ ልጅ የሚያሳድገው ሌላ ጎረምሳም አለው፡፡ የባለቤቱ የወይዘሮ ፀሐይ የወንድም ልጅ ነው፡፡ 11 ክፍል ደርሷል፡፡ ወይዘሮ ፀሐይ ወልደሰንበት እንዴት ያለች ሩህሩህ ሴት መሰለችዎ! ‹‹ፊንጫ ፋፏቴ›› የተሰኘውን ግዙፉን የትራንስፖርት ኩባንያ ቀጥ አርጋ ያቆመችው እርሷው ናት፡፡

እግረ መንገዴን ጋሽ ገምሹ በየነና ወይዘሮ ፀሐይ ወልደሰንበት….እንዴት እንደተገናኙ ነግሬዎት ልለፍ፣ ጌታዬ!

የዛሬ 13 ዓመት ግድም ነው፡፡ እርሷ ያምቦ ልጅ ናት፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ብላ ተሸቀርቅራ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ መሄድ፡፡ ጋሽ ገምሹ ለጥምቀት በዓል ከፊንፊኔ ወደ ትውልድ መንደሩ አምቦ ሎሚ በኪሱ ይዞ መሄድ፡፡ ግጥምጥሞሹ አይገርምም?

ገምሹ ከዚያ በፊት ደንግጦ የሚያውቀው ለቆንጆ ሴት ሳይሆን ፒስታ መንገድ ሲያይ ብቻ ነው፡፡ እሱም የአስፋልት ጨረታው ስለሚታሰበውልማት ስለሚያጓጓው ነው፡፡ ያን ቀን ግን ወይዘሪት ፀሐይን ሲመለከት ደነገጠ፡፡ በዚያች የጥምቀት ዕለት እህል ዉሀ አገናኛቸው፡፡ ገምሹ ሎሚውን የደስ ደስ ባላት ወይዘሪት ፀሐይ ደረት ላይ ወረወረ፡፡ ‹‹በሬዱ አምቦ›› ወይዘሪት ፀሐይ ተሽኮረመመች፡፡በሬዱኪያ›› አሏት ጋሽ ገምሹ፡፡ ያኔውኑ ፍቀር ተለኮሰፍቅር ተቀጣጠለፍቅር ጎመራ፡፡

ጌታዬ! ምን ዋጋ አለው ታዲያ! ትዳር የሚባረከው በልጅ ነው፡፡ ልጅ እምቢ አላቸው፡፡ እንግዲህ እሱ ሲፈቅድ አይደል ሁሉ የሚሆን? መታገስ ነበረባቸው፡፡ ከስንት ዓመታት ሕክምናና ፀሎት በኋላ ባረካቸው፡፡ ኢሊሌ ተወለደች፡፡

እርስዎ ግን እንዴት ነዎት ጌታዬ! ከአሳሪው ወገን ነዎት ወይስ ከታሳሪው?

ያለምክንያት አልጠየቅክዎትም፡፡ ሰሞኑን ውስኪ ቤቱ ሁሉ ከል ለብሶ ባይ ጊዜ ነው፡፡ ሂልተን ሎቢ ጭርታው ያስፈራል፡፡ ኦፊስ ባር የማይዳሰስ ድንኳን ሳይተከል አልቀረም፡፡ አገጩን በእጁ ደግፎ መለኪያ ያልጨበጠ አንድም ሀብታም አላየሁም፡፡ የኔም ሥራ ከመደለል ወደ ማባበል፣ ከማዝናናት ወደ ማጽጽናናት ወርዷል፡፡ እውነቴን እኮ ነው የምነግርዎ!

እኔምልዎ ጌታዬ! ገንዘብ ግን ከፍርሃት ነጻ ካላወጣ ምኑ ላይ ነው ትርፉ?

እርስዎም እንደሚያውቁት እኔ ገረመው ፕሮፌሽናል ደላላ ነኝ፡፡ እኔ የሰው ስም በከንቱ አላነሳም፡፡ ስለገምሹ የምነግርዎ በመረጃና በማስረጃ ተደግፌ ነው፡፡

ገምሹ የዛሬ ወዳጄ እንዳይመስልዎ! ገና ድሮ የከረከሰ የግንባታ ማሽን ሲያከራይ ነው የማውቀው፡፡ ገና ድሮ የበሰበሰች ኤንትሬ ሲነዳ ነው የማስታውሰው፡፡ ገና ድሮ የኑግ ሲራራ ነጋዴ እያለ ነው ጓደኞቼ የሚያውቁት፡፡ ያኔም እንዲሁ ነበር ታዲያ፡፡ ባተሌ፡፡ ጠዋት ማልዶ የወጣ ማታ አምሽቶ ቤት የሚገባ ባተሌ፡፡ አንድ ለመንገድ ማለትን እንኳ አያውቅም፡፡ የርሱ ግሮሰሪ ያቺው በቀይ ቀለም ያበደች ቢሮው ናት፡፡

ጓደኛ አያበዛም፡፡ ‹‹የኔ ወዳጅ እየሱሴ ነው!›› የሚለው ነገር አለ፡፡ ምናልባት አንድ ወዳጅ አለው ከተባለም ያው የተከበሩ አፈ ጉባኤው ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር ያባዱላና የገምሹ ፍቅር ይለያል፡፡ ማውራት ከጀመሩኮ ተሾመ ቶጋ ከነ መዶሻው ተመልሶ ከብራስልስ ቢመጣ እንኳ አያስቆማቸውም፡፡ እንደዕድሜ ዘመን ሚስጢረኛ አፍ ለአፍ ገጥመው ሹሹሹ…. ምን ይሆን የሚያወሩት?

ጌታዬ! ያው ለደላላ ወሬ ፌርማታ የለው…!የማውቀውን ልንገርዎና ልለፍ

ያባዱላ የቀድሞ ረዳት ኦቦ ኢብሳ አንዴ ምን አለኝ መሰልዎ…! .አባዱላን ፓርላማ ካጣኸው ወይ ገምሹ ዘንድ፣ ወይ ራስ ሆቴል ታገኘዋለህ አለኝ፡፡ ራስ ሆቴል ደግሞ ምን ይሠራል ብለው? ‘ጌታን የሚያመልከው ፓስተር ጃፒ ጋር እንደሆነ አታውቅምና ነው?’ ብሎ አሳቀኝ፡፡ ለካንስ ራስ ሆቴል ጀርባ ትልቁ አዳራሽ እውቅ ቸርች ሆኗል፡፡ አርብ አርብ ባባዱላ የሚባረክ ጸሎትና ስብከት ይካሄድበታል፡፡ገሬ! አንተ ዲዳውን ፓርላማ ነው የምታውቅ፣ ልሳን የሚናገር ፓርላማ በራስ ሆቴል ተከፍቶልሀልብሎ አሳቀኝ፣ ኦቦ ኢብሳ፡፡

ጌታዬ! አባዱላ ዘይደዋል እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ መጸለይ ካልሆነ ነጻ የሚያወጣ ማን ነው?!

ኦቦ ኢብሳ ዛሬ እንደኔው ከባድ ሚዛን ጉዳይ ገዳይ ከመሆኑ በፊት ካባዱላ ጋር የተለየ ቅርበት ነበረው፡፡አባዱላ እንዴት ነው ግን ሰሞኑን፣ ከታሳሪ ነው ከአሳሪ?’ ብዬው ነበር በጨዋታ በጨዋታ፡፡ ፈገግ ብሎ ቢጫ ጥርሱን ካሳየኝ በኋላ፣ ‹‹ገረመው! እሱ እኮ ከሙስና ከወጣ ዘመን የለውም፡፡ ለሁሉም ነገር እኮ ጊዜና ለከት አለው፡፡ ነባር ሙሰኞች አሁን ትተዋል፡፡ መተካካት ሲባል አልሰማህም? አሁን የምታያቸው አማተር ሙሰኞች ነው፡፡›› ብሎ አሳቀኝ፡፡ አባዱላን በሐብት ክምችት የገዛ አጃቢዎቹ እንደሚበልጡት ከዚህ በፊት ነግሮኝ ያውቃል፡፡ ‹‹አሁን ለኦሮሞ ልጆች የኢኮኖሚ እኩልነት መታገል ነው የያዘው›› አለኝ፡፡

ጌታዬ! አርስዎ ግን እንዴት ነዎት? የስጋት ንፋስ ሽው ይልብዎታል ወይስ እንደ ዋርዲያ እከ በሰላም ለሽ ይላሉ? ኸረ ለመሆኑ ከታሳሪ ወገን ነዎት ከአሳሪ?

እነዚህ ጥላቢሶች ወዳጄ ገምሹን ሲያስደነግጡብኝ ጊዜኮ ነው እንዲህ መጠየቄ!

ጋሽ ገምሹ በባህሪው ዛሬን እንጂ ነገን አይወድም፡፡ ነገ ተይዟል ይላል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ለዚህ ይመስለኛል ምስጉን የመንገድ ተቋራጭ ለመሆን የበቃው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ፕሮጀክቶቹን ከተቀመጠለት ቀን ቀድሞ የሚያስረክብ፡፡ እውነት ለመናገር ገምሹና ቻይና አንድም ዘግይተው ያስረከቡት መንገድ የለም፡፡ ይሄ እኔ ሳልሆን የመንገዶች ባለሥልጣን ውስጥ የተሰገሰገ ኮልኮሌ መሐንዲስ ሁሉ የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡

በሥራ አፈጻጸም አንደኛ፣ ገምሹ በየነ ኬኛ እያለ ያሾፍበት ነበር አቶ ዛይድ፣ የዛሬን አያርገውና፡፡

እርግጥ ነው ገምሹና ዛይድ ሽርክ ነበሩ፡፡ በስኳር ስለመሻረካቸው ግን አላውቅም፡፡

አሁን ጣጣ ውስጥ የከተታቸውን የማይጸብሪን መንገድ ዛይድ ያለጨረታ ለገምሹ የሰጠው ወዳጅ ስለነበሩ አይመስለኝም፡፡ ፕሮፌሽናል ደላላ ነኝ ብዬዎታለሁ፡፡ ነገርን ከሥር መሠረቱ ማስረዳት እወዳለሁ

ነፍሳቸውን ይማርና ታላቁ መሪ ያኔ ትግራይን በጎበኙበት ወቅት  ነዋሪውመንገድ ይሠራልንብሎ የሙጥኝ አለ፡፡ ታላቁ መሪ የአገር ሽማግሌ ሲያስጨንቃቸው ቃል ገቡ፡፡ ወደ አዲሳባ ሲመለሱ ለአቶ ዛይድእስቲ የተራረፈ በጀት ካለህ የምትችለውን አርግላቸውአሉት፡፡ ዛይድ ወዲያውኑ ገምሹ ጋር ደወለ፡፡ ገምሹ ያን ጊዜ በአጋጣሚ የማይጸብሪን የኮንክሪት መንገድ ጨረታ አሸንፎ በመሥራት ላይ ነበር፡፡ በቃ… “ማነህ ገምሹበነካ እጅህ አስፋልት አርገውአለው፡፡ ገምሹ ወዲያዉኑ ሬንጅ መቀባት ጀመረ፡፡ አሁን ይኸው ከስንት ዘመን በኋላ፣ ታላቁ መሪ በምስክርነት በማይቀርቡበት ሁኔታ ሁለቱም ጣጣ ውስጥ ገቡ፡፡

ጌታዬ ኢህአዴግ ፊት አይንሳዎ፤ ከነሳዎ አያድርስ ነው፡፡ እንደ መላኩ ፈንታ ቀይ ሆነው ገብተው እንደ ገብረዋሕድ ጠቁረው ከከርቸሌ ይወጣሉ፡፡ እውነቴን እኮ ነው የምነግርዎ…! ብቻ ኢህአዴግ ፊት አይንሳዎ…!

እንጂማ እንደ ገምሹ ለፓርቲው የቀረበ ጠንካራ የሥራ ሰው ነበረ እንዴ?

በፊንጫ ኑግ ነግዶ፣ በደብረማርቆስ ጂጋ ከተማ የቀን ሠራተኛ ሆኖ፣ ለአውራ ጎዳና መሥሪያ ቤት ከባድ መኪና ሾፍሮ ነው ዛሬ ቢሊየነር መሆን የቻለው፡፡ ገምሹ የኦህዴድን ዕድሜ ያህል በንግድ ዓለም ተፍጨርጭሯል፡፡ ኦህዴድ ከዚህ ሁሉ የትግል ዘመን በኋላም የኦሮሞ ሕዝብ ልብ ውስጥ አልሰረገም፡፡ ገምሹ ግን በከፊልም ቢኾን ተሳክቶለታል፡፡ ቢያንስ በርሱ የቢዝነስ ድርጅት ውስጥ ከሊሙዚን ነጂ እስከ ቡና ቀጂ ኢጆሌ ኦሮሞዎችን ነው የሚቀጥረው፡፡ ቢያንስ በርሱ የቢዝነስ ድርጅት የሥራ ቋንቋ ኦሮሚፋ ነው፡፡

የኦቦ በየነ ቦቴ ልጅ ገምሹ ሦስት ጊዜ በኢኮኖሚ ችግር ትምህርት አቁሞ ቀጥሏል፡፡ ዛሬ 12 ክፍልን ጥንቅቅ ማድረግ  የቻለው ባንድ ትንፋሽ አይምሰልዎ፡፡ ብዙዎቹ የአቡጊዳ ሽፍታ አድርገው የሚያስቡት ነገር ፍጹም የተሳሳተ ነው፡፡ ጂጋ ቋሪት 8 ክፍል አብሮት የተፈተነው አቶ አስቻለው እንደነገረኝ ገምሹ ሚኒስትሪ ለያውም በዚያ ዘመን 97 ነጥብ አምጥቶ ያለፈ የቀለም ቀንድ ነው፡፡

ኦቦ ገምሹ የተቃጠለ የኦሮሞ ብሔርተኛ ነው ብዬዎታለሁ፡፡ ካባዱላ የሚያቀራርባቸውም ይኸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ አልጋ ላንድ ምሽት በአምስት መቶ ዶላር ሲቸረችር እንኳን ቅድሚያ ለኦሮሞ ዲያስፖራ ሰጥቶ ነው፡፡ አገሩን መውደዱ ባልከፋ፡፡ ከኔም ሁሌም የሚያጋጨን ይሄን ብሔርተኛነቱን ሥራ ቦታ ሲያመጣው ነው፡፡ ‹‹ገምሹ! ሥራ በወንዝ ልጅነት አይሆንም፣ተው›› እለዋለሁ፡፡አንተ ነፍጠኛ ደላላ ስለሆንክ ነውእንደዚያ የምታስብ ይለኛል፡፡ እንስቃለን፡፡

ኦቦ ገምሹ የዋህ ነው፡፡ ከሱ ጎሳ ለሚመዘዙ ሠራተኞቹ ሁልጊዜም ሠርቶ በመለወጥ እንዲያምኑ ይመክራል፡፡እኔ ሥራ የጀመርኩት ሦስት መቶ ብር ተበድሬ ኑግ በመሸጥ ነው፡፡ በኋላ ቀንቶኝ ሾፌር ሆንኩ፡፡ አሁን እውነቱን ለመናገር ያሉኝን መኪኖች ቁጥር ማወቅ የማልችልበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ እባካችሁ ሥራ አትናቁእያለ ይመክራል፡፡

ታዲያ ነገር ሲያድር አይወድም፡፡ ይኸው ከአያት ሪልስቴቱ ጌታ ከአቶ አያሌው ተሰማ አምታቶ የወሰደባቸው ሺህ ሰባት መቶ ካሬ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ይሄን የካዛንቺስ ቁልፍ መሬት አቶ አያሌው በሊዝ አሸንፈው፣ መሰረቱን ቆፍረው ሲታሰሩ ግንባታውን ረሱት፡፡ ገምሹ ክፍለ ከተማ አመለከተ፡፡ በጊዜው ስላላለሙት ለኔ ይሰጠኝ ብሎ አቤቱታ አቀረበ፡፡ በከተማው ስንት ያለማ መሬት ተነጥቆ አያውቅም፡፡ ገምሹ ግን ካርታው እንዲመክን አድርጎ ከመቼው  ለኢሊሌ ማስፋፊያ እንደወሰደው ገምሹና ዋቃ ብቻ ነው የሚያውቁት፡፡  ካርታውን ገና በጁ ሳይገባ 22 ፎቅ የሚመዘዝ 8 ወለል የመኪና ማቆምያን ያካተተ ሕንጣ ሲያቆም ዓመት ተመንፈቅ እንኳ ፈጀበት እንዴ?

ገረመው! ይሄን ፎቄን ለምን አብልጬ እንደምወደው ታውቃለህ?” ይለኛል፣ በአንዳች አጋጣሚ ቤቱ ከጋበዘኝ፤ኸረ አላውቅም ጌታዬ!” እለዋለሁ፡፡ “…ከመኝታ ቤቴ ሆኜ፣ ለዚያውም ከአልጋዬ ሳልወርድ ስለሚታየኝ ነውይለኛል፡፡

እውነቱን ነው ለካስ፡፡ ከየትም የፊንፊኔ ጥግ ተኩኖ የሚታይ እንደ ሐረግ የተመዘዘ፣ እንደ እንጉዳይ የበቀለ ሕንጻ ነው ባንድ ጀንበር ያቆመው፡፡ በአፈጻጸም አንደኛ፣ ገምሹ በየነ ኬኛእለዋለሁ እኔም እንደ ዛይድ፡፡ ደስ ይለዋል፡፡ ያቺን የተመጠነች ፈገግታ ይሰጠኛል፡፡ ያቺን የአገጩን ጢም፣ ያቺን ድንቡሼ የሕጻን ልጅ የመሰለች ጉንጩን እወድለታለሁ፡፡

ለነገሩ ገምሹ ፈገግታ ላይ ብቻ ሳይሆን ብርም ላይ ቁጥብ ነው፡፡ ማስከፈል እንጂ መክፈል አይወድም ይሉታል ሠራተኞቹ፡፡ ያም ኾኖ በኦሮሞ ልጆች የሚጨክን አንጀት የለውም፡፡ እልል ያለ የአሮሞ ብሔርተኛ ነው፡፡ ከወለጋ ነቀምት ይልቅ በኢሊሌ ሆቴል ሎቢ አፋን ኦሮሞ ይነገራል፡፡ በቅርቡ ፕሮፌሰር ባሬንቶን የተኩት ፈረንጁ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ እንኳአካም፣ ነጉማ፣ ጋላቶማሲሉ አፋቸው እንዴት እንደሚጣፍጥ፡፡ ገምሹ ነው ያስተማራቸው ታዲያ፡፡ ገምሹ ቤት ለመሰንበት ለምን ፈረንጅ አይሆንም ኦሮምኛ መሞካከር አለበት፡፡

ጌታዬ! መረጃ አበዛሁብዎ አይደል? ያው እንደሚያውቁት የደላላ ወሬ ፌርማታ የለው

የኦሮሚያ ባንክ ገሚሱ ድርሻ የገምሹ ነው፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ ገሚሱ የገምሹ ነው፡፡ በፊንፊኔ አንድ ደርዘን የሚሆን ቤት አለው፡፡ ለየኤንባሲው አከራይቶታል፡፡ ቦሌ ዎርቤክ አካባቢ ለሞሪሽየስ ኤምባሲ ያከራየው አንዱ ነው፡፡ ቦቦጋያ 7 ካሬ ያረፈ፣ እንኳን ሰው ሄሊኮፍተር የሚሳርፍ ባለ 5 ኮከብ ሪዞርት ሙሉው የርሱ ነው፡፡ ከዓመት በፊት ጀምሮት ነበር፤ ምን እንዳደረሰው እንጃ እንጂ፡፡ እዚህ ቡራዩም ጎልፍ የሚያጫውት፣ በምድር በሰማይ የተፈጠረ እንሰሳ ሁሉ የሚገኝበት ሪዞርት ጀምሬያለሁ ሲለኝ ነበር፡፡ ከምን እንዳደረሰው እንጃ እንጂ፡፡ ለነገሩ ገምሹ እንዳላሙዲ አይደለም፡፡ ከጀመረ ይጨርሳል፡፡

እንዴት ነዎት ግን እርስዎ! ከአሳሪ ወገን ነዎት ወይስ ከታሳሪ?

ለአንዳንድ ሰው የስኬት መሰላል ያዳልጠዋል፡፡ አንዳንዱን ደግሞ እንደ ኤስካሌተር በምቾት ይዞት ይወጣል፡፡ ገምሹ ኑግ በሲራራ ነገደ፡፡ ደብረማርቆስ ሾፌር ሆነ፡፡ በሾፌር ደመወዙ ብር አጠራቅሞ ጉድጓድ በኮንትራት መቆፈር ጀመረ፡፡ ተበድሮ ከጓደኛው ጋር 169 ብር አንድ ከርካሳ ኤን ትሬ የጭነት መኪና ገዛ፡፡ ጥርሱን ነክሶ ኤን ትሬዋን የራሱ አደረጋት፡፡ ለጥቆ ከኒያላ ሞተርስ ባለቤት ከነበሩት አቶ ጌታቸው ገብረሥላሴ በረዥም ጊዜ ብድር ሦስት ገልባጭ ኒሳን ገዛ፡፡ ገልባጮቹን እያከራየ ዕዳ ከፍሎ ሌላ ሦስት ደገመ፡፡ አሁን የፊንጫ ፏፏቴ የሚባል የትራንስፖርት ድርጅት አለው፡፡ ባለ አስር ጎማ የሆኑ በርካታ የጭነት መኪኖችን ያስተዳድራል፡፡ እነዚህን መኪኖች ቢሰለፉ ከሞጆ ጅቡቲ አይደርሱም ብለው ነው? ከዚህ ውጭ መአት ዶዘር፣ መአት ሎደር፣ መአት ግሬደር፣ መአት እስካቫተር ያከራያል፡፡ መንገድ ይጠርጋል፡፡ ገምሹ መንገድ አስፋልት ሲያለብስ አብሲት የመጣድ ያህል ቀላል ነው፡፡

የልጅነት ታሪኩን አውግቶኝ አይጠግብም፡፡ ለስንተኛ ጊዜ መሰለዎ የሚተርክልኝ፡፡

በወለጋ ጠቅላይ ግዛት፤ ሆሮ ጉድሩ አውራጃ፤ አባይ ጮመን ወረዳ ሆማ ኩልኩላ መንደር ወተትና ማር እየተቀለብኩ ያደኩ የአንበሳው የበየነ ቦቴ ልጅ ነኝይለኛል ጨዋታ ሲደራ፡፡ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም በወተትና ማር ነው ያደገው፡፡ ቤተሰቦቹን ደርግ በአድሀሪነት ወንጅሎ እስኪያሳድዳቸው ድረስ፡፡ ቤታቸውን እስኪሲያቃጥለው ድረስ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ የጉስቁልና ታሪክ ነው፡፡ ገምሹ የሚላስ የሚቀመስ ያጣበት ዘመን፡፡ ይህን ጊዜ ነው የኑግ ሲራራ ነጋዴ የሆነው፡፡ ሳይደግስ አይጣላም፡፡

ገምሹ በየነ የአሊ ቢራን ሙዚቃ ይወዳል፡፡ ቆየት ያሉትን የአብተው ከበደን ዜማም ያጣጥማል፡፡ ኾኖም የርሱ የሁልጊዜም ውብ ሙዚቃ የቱ ነው ከተባልኩኝ የዶዘርና የሎደር ኳኳቴ ይሆናል ምላሼ፡፡ እየቀለድኩ አይደለም፡፡ ገምሹ ጭር ሲል አይወድም፡፡ ማለቴ የግንባታ ማሽን፣ ጃክ ሀመር፣ ኢስካቫተር ካልተንቋቋ ይረበሻል፡፡ ይቁነጠነጣል፡፡ ሠራተኛን ያመናጭቃል፡፡ እነሱር ይህን ስለሚያውቁ ማሽኖቹን ያንቋቁለታል…..ኳኳኳ

በተደጋጋሚ የሚለው ነገር ነው ይሄ፡፡ ‹‹ገረመው! እኔ መኖሬን የማውቀው የዶዘር፣ የግሬደርና የስካቫተር ድምጽ ስሰማ ነው፡፡ ይለኛል፡፡ እኔም እለዋለሁ፣ ‹‹ገምሹ! እኔ ደግሞ መኖሬን የማውቀው 2 ፐርሰንት ኮሚሽን ሲከፈለኝ ነው››፡፡ ካካካካ….ያቺን ችም ያለች የአገጭ ጢሙን እየነካካ ይስቃል፡፡

ጌታዬ! እርስዎ ግን እንዴት ነዎት? እንደው ለመሆኑ ከአሳሪው ወገን ነዎት ወይስ ከታሳሪ?

ገረመው ነኝ

(ለዋዜማ ራዲዮ)