(ለዋዜማ ራዲዮ)

ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!

a

ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡  ምስጉን ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡ ዉሎና አዳሬ ‹‹ብሔራዊ››፣ ጠባዬ የባሕታዊ፣ ‹‹ላየን ባር›› ቤቴ፣ ‹‹ቴሌ ባር›› ግዛቴ…፡፡

ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ…ሄሄሄ የዛሬ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!!

እውነቴን እኮ ነው፡፡ ሰሞኑን ለምሳሌ በጭራሽ ፋታ አልነበረኝ፡፡ ላንዱ ስገዛ፣ ላንዱ ሳጋዛ፣ ላንዱ ስሸጥ፣ ላንዱ ሳሻሸጥ፣ ላንዱ ስሸመጥጥ፡፡ ሰው እንዴት ለመተንፈስ ጊዜ ያጣል?!!

የዚህ ወር ዉሎዬን ለየት የሚያደርገው ከሚሊየነር ቺስታ ደንበኞች በቀጥታ ወደ ቢሊየነር ደንበኞቼ መሸጋገሬ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በድለላ ዓለም እምብዛምም ነው፡፡ ዳንጎቴና ሼኩን ባንድ ሳምንት አስተናገድኩ ብል አሁን ማን ያምነኛል…? በአጭሩ በሁለት ቢሊየነሮች የሚንቀረቀብ የጨርቅ ኳስ ኾኜ ሰነበትኩ እልዎታለሁ፡፡

ሼካው ያገኙኝ ለወልዲያ ስታዲዮም ምረቃ በመጡበት ዋዜማ ነው፡፡ ከዶክተር አረጋ ጋር በጨርቅ ኳስ መቻሬ ሜዳ ላይ ከመጋጠማቸው ቀደም ብሎ ማለት ነው፡፡ ድንገት ሸራተን ቪላ ትፈለጋለህ ተባልኩ፡፡ እኔ ደሞ ለኦፊስ ባሩ ካልሆነ ለቪላው ባዳ ነኝ፡፡ ትንሽ ፍርሃት ቢጤ ሽው አላለብኝም አልልዎትም፡፡ ደላላምእኮ አንዳንዴ ይፈራል፡፡ ሼካው ግን ጨዋታ ወዳጅ ናቸው፡፡ ገና ከመተዋወቃችን እስቲ ምላስህን አዉጥተህ አሳየኝ አሉኝ፡፡ አሳየኋቸው፡ ይቅርታ! ደላላ በምላሱ ጤፍ ይቆላል ሲባል ሰምቼ ነው ብለው አሳቁኝ፡፡ ተያይዘን አስነካነው…..ካካካካካካካካካካካካካ..!! ከሞጃ መሳ ለመሳ መሳቅ እድሜ ይቀጥል የለም እንዴ!

ለማንኛውም ሼካው የፈለጉኝ ቤት እንድገዛላቸው ነው፡፡ ለርሳቸው አይደለም፡፡ እርሳቸው ቤት ለምን ይፈልጋሉ፡፡ አገሪቱስ የርሳቸው ማድቤት አይደለችምን!? ለሁለት ወጣት ልጆች ነው ቤት እንድገዛ የፈለጉት፡፡ ልነግርዎት እኮ ነው…

ሼኩ ሰው ለሰው የሚባል ድራማን ወደድኩ አሉ፡፡ እናም ለድራማው ፈጣሪዎች አሁኑኑ ቤት ካልገዛክላቸው አሉኝ፡፡ ራሳቸው አይገዙም እንዴ? ብላቸው…አንተ ደሞ ደራሲ ፊደል እንጂ መች ቁጥር ያውቃል?! ብለው አሳቁኝ፡፡ ካካካካካካካካካካ….ከሞጃ ጋር መሳ ለመሳ መሳቅ ቦርጭ ያስጠፋ የለም እንዴ!

ትዛዛቸውን ወድያው ፈፀምኩ፡፡ ለገጣፎ በርሬ፣ ካንትሪ ክለብ ዞሬ፣ ሮፓክ ዉስጥ ሁለት ቪላ አገኘሁ፡፡ ደግነቱ ልጆቹም ምርጫዬን ወደዱት፤ እንዳውም ገፀባሕሪ የሚመስል ቤት ነው ያጋዛከን አሉኝ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ መተወን እፈልግ እንደሆን ጠየቁኝ፤ ደላላ መቼ ከመተወን ወጥቶ ያውቃል አልኳቸው፡፡ ተያይዘን…..ካካካካካካ…ከአርቲስት ጋር መሳቅ እድሜ ያሳጥር የለም እንዴ ገበዝ! እኔ መች አውቄ!

ግን እኮ ዓይን ቦታ እኮ ነው ያስያዝኳቸው፡፡ ለያንዳንዳቸው 7 ሚሊዮን ሼኩ በቼክ ከፈሉኝ፡፡ ፊርማቸው ሲያምር!! በዲቪ እንደተለየችኝ ፍቅረኛ ለአንድ ሰዓት ያህል በተመስጦ አየሁት፡፡ በዓለም ላይ ተጽእኖ ከሚፈጥሩ መቶ ፊርማዎች አንዱ እንደሆነ አሰብኩ፡፡ በአገሬ አንድ መቶ ሺ ዜጎች በልተው የሚያድሩት በዚህ ፊርማ የተነሳ መሆኑን አሰብኩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሳይቀር የሚጎመዡለት ፊርማ እንደሆነ አሰብኩ፡፡ ታምራት ላይኔ ጌታን ከመቀበሉ በፊት የተንበረከከለት፣ የታሰረለት ፊርማ እንደሆነ አሰብኩ፡፡ ሞባይሌን አውጥቼ ከፊርማው ጋር የማስታወሻ ፎቶ ተነሳሁ፡፡

የሚገርመው በዚያው ሳምንት ሼኩ ለሌሎች 6 ሰዎች ቤት ገዝተዋል፡፡ ባይኔ በብረቱ ባላይ አላምንም ነበር፡፡ ጓደኛዬ አላምረው ነው ሦስቱን የደለለው፡፡ ለነገሩ ይሄ ምኑ ይገርማል! መቻሬ ሜዳን ለልጅነት ትዝታቸው ሲሉ በግማሽ ቢሊዮን ወደ ስታዲዮምነት የለወጡ ጌታ ጥቂት አርቲስቶችን ከትቢያ አንስተው ቪላ ቤት ቢያስገቡ በእውነቱ ምኑ ይገርማል? እንደው እኛ ደላሎች ነገር ማዳመቅ እንወዳለን እንጂ ይሄ ምኑም አይገርምም፡፡

ብቻ የሼኩን ጉዳይ ጨርሼ እፎይ ስል ወይዘሮ ቲቲ ደወሉ፡፡ ለብርቱ ጉዳይ ፈልገውኝ ነፍሴን አስጨነቋት፡፡ ቲቲን ያውቋታል ጌታዬ? የታላቁ የሼክ ላሙዲ የቀድሞ ወዳጅ ናቸው፡፡ ሞናኮ ዉስጥ ደሴት የሚያክል ቤት ተገዝቶላቸው የሚኖሩ የናጠጡ ሴት ቱጃር፡፡ ብሉ ላይን የሚባል ግዙፍ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት፡፡ እንደው ቤት ንብረታቸው በዝቶብኝ ነው አንቱ የምላቸው እንጂ እሳቸውስ….፡፡ ገና የሞናኮ ጉብል፣ የፈረንሳይ ኮረዳ እንጂ…በጭራሽ አንቱ የሚባሉ ወይዘሮ አይደሉም፡፡ ቲቲ ብሎ አንቱታ የለም፡፡ ስለዚህ አንቺ በሚለው እቀጥላለሁ፡፡

ፑሉቶ ሪልስቴት የቲቲ ነው፡፡ የራሷ፣ ብሉላይን የቲቲ ነው፤ የግል ንብረቷ፡፡ ፑሉቶ በኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ስህተት ላይ ተመስርቶ የተጀመረ የፊንፊኔ ቁጥር አንድ ሪልስቴት ነው፡፡ የሲኤምሲ ግቢን የመሰለ ዩኒቨርስቲ የሚያህል ትልቅ ግቢ አጥሮ ይዞ፣ አልታድ ሚካኤል ጀርባ፣ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር ሕንጻ ጎን ይገኛል፡፡ ለሞጃዎች ብቻ ባይነት ባይነቱ ቤት ያቀርባል፡፡ ቤት ቢባሉ ተራ ቤት እንዳይመስልዎ! ፊንፊኔ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ቤት  ነው እየሠራ የሚሸጥ፡፡  ማለቴ ቲቲ ናት ገንብታ የምትሸጠው፡፡ ብዙዎቹ ቤቶች ጣሪያ ለብሰዋል፡፡

ጌታዬ! ቲቲ የምትገነባቻቸው የ40-60 መናኛ ዳስ ቤቶች  መስሎዎ ፊጥ ለማለት እንዳይቸኩሉ፡፡ አንዱ ቤት ብቻ 680 ካሬ ላያ ያረፈ ነው፡፡ ቢያምኑም ባያምኑም ቤቱ ዉስጥ አደባባይ አለ፡፡ ባጭሩ ቤት ሳይሆን አብያተ መንግሥት ነው የገነባችው፡፡ ካላመኑኝ ዋጋውን ይስሙ፡፡ የአንዱ መኖርያ ዋጋ ያለ ፊኒሺንግ 21 ሚሊዮን ብር ሲሆን፤ ጣጣው አልቆለት ቁልፉ ይሰጠኝ ካሉ ደግሞ 28 ሚሊዮን ሆጭ ያደርጋሉ፡፡

ጉድ እኮ ነው! በዚህ ብር ድሮ ምን የመሰለ ሕንጣ ይቆም ነበር፡፡ የዛሬን አያርገውና ወዳጄ ታደለ ካሳ የቦሌ መድኃኒዓለሙን ሸገር ሕንጻ ለመጨረስ 10 ሚሊዮን ብር ነበር የፈጀበት፡፡ በድሮ በሬ አይታረስ ነገር!

እንዴት ነዎት ግን እርስዎ!

በወይዘሮ ቲቲ ወሬ ጠመድክዎ አይደል? በነገርዎ ላይ ወዳጄ ቲቲ አገር ቤት የሚመጡት ከስንት አንዴ መሰለዎ፡፡ አይመቻቸውማ፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ወይዘሮ ቢኾኑም ቅሉ አገሪቱ ግን ብዙም አትስማማቸውም፡፡ ሞናኮ ነው ለርሳቸው የሚስማማ፡፡

አሃ ልክ ነዋ! …ፊንፊኔ ሰው በየመንገዱ እየሸና ወይዘሮ ቲቲን የመሰሉ ክቡር ደንበኞቼን ለጉንፋን ዳረጋቸው እኮ! ሕዝቡ ንጽሕና ላይ ይቀረዋል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንጃ! ደላላ በምላሱ ኢንቨስት ከማድረግ ሌላ ምንስ ማድረግ ይቻለዋል፡፡


ብቻ ወይዘሮ ቲቲ ሞናኮ ሲኖሩ ነው አሉ ከዕለታት አንድ ቀን አንዳንድ የሞናኮ አርክቴክቶች ጋር የተገናኙት፡፡ ብዙ ገንዘብ አለኝ! ወገኔን መርዳት በአገሬ መሥራት እሻለሁ፣ ድሀ አገር አለችኝ፤ በአገሬ የምገነባውን ቤት ቀይሱልኝ ብለው አስቸገሩ አሉ፡፡ ወይዘሮ ቲቲ እንዲሁም ዐይነ ግቡ ናቸው፤ የጠየቁት ሰው አያሳፍራቸው፣ ለዐይን እጅግ ማራኪ ቤቶችን ደዘኑላቸው፡፡ ማ….ን? የሞናኮ አርክቴክቶች፡፡ ያውም ከዳቦ ስም ጋራ፡፡

ቪላ አልፋ፣ ቪላ ሪገል፣ ቪላ አቪዮር፣ ቪላ ቬጋ፣ ቪላ ፖላሪስ፣ ቪላ ካፔላ፣ ይባላሉ ቤቶቹ፡፡ እነዚህ ቄንጠኛ ቤቶች ናቸው አሁን በወይዘሮ ቲቲ የሚቸረችሩት፡፡ ይቺ ዓለም ግን እንዴት ገራሚ ናት ጌታው፡፡ አንዳንዱ ሽንኩርት ይቸረችራል፤ አንዳንዱ ፎቅ ይቸረችራል፡፡

###

የወይዘሪት ቲቲን ስጨርስ ወደ ናይጄሪያ ተዛወርኩ፡፡ የገረመው ዝና እንደሁ ምራብ አፍሪካን ከተሻገረ ቆየ፡፡  በውነት ለመናገር አሊጎ ዳንጎቴ ጥሩና ኩሩ ሰው ናቸው፡፡ እንዳገራቸው ሰው አመለጥፉ አይደሉም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቤት አጋዛኝ ብለውኝ በ220 ሚሊዮን ብር ምን የመሰለ ቪላ አፈጣጥምኳቸው፡፡ ለያውም በፊንፊኔ ተራራ፡፡ ስለተደረገልኝ ሁሉ ወይዘሮ አርቲስት ሮማንን እድሜ ይስጥልኝ ለማለት እሻለሁ፡፡ ቀን እንዲወጣልኝ ያረገች እርሷው ናት፡፡ እርሷ ናት ለዳንጎቴ ስለኔ አብጠርጥራ የነገረች፡፡ እርሷ ናት በዚህ አገር ከገረመው የተሻለ ሰው አታገኝም ያለችው፡፡ ኢንተርናሽናል ደላላ እንድሆን መንገድ የጠረገች እርሷው ናት፡፡ ወዲያውኑ ወደዱኝ፡፡ እኔም ወደድኳቸው፡፡ አሊጎ ዳንጎቴን አጎቴ ዳንጎቴ ብሎ ለመጥራት ደቂቃም አልወሰደብኝም፡፡

ሮማን ሲፈጥራት ቸር ናት፡፡ እድሜ ለርሷ ይኸው ከርሷ ለተወዳጁት የቀድሞ የሞያ ሰዎች ሁሉ ቀን ወጣላቸው፡፡ ምድረ ሠራዊት፣ ምድረ ቴድሮስ ቀዝቃዛ ወላፈን፣ ምድረ  አርቲስት ሲሚንቶ አከፋፋይ ኾነ፡፡ ስቱዲዮው ዳንጎቴ ነው፤ ካሜራው ዳንጎቴ ነው፡፡ ለካንስ ፊልም ተመልካቹ በየሲኒማው ዐይኑን አስሬ የሚያሸው ወዶ አይደለም፡፡ የሲሚንቶው ብናኝ ገብቶበት እንጂ፡፡

ጌታዬ! መቼስ ሰፊው ሕዝብ ታክሲ ሲጋፋ አይተውት ይሆናል፤ በየፌርማታው፡፡ የአገርዎ አርቲስት የት እንደሚጋፋ ያውቃሉ? ሼራተን ቪላ፡፡ ሁኔታውን ግልፅ ለማድረግ ያህል…በ3ቁጥር አውቶቡስ ላስረዳዎ! 3 ቁጥር አውቶቡስ ከሰዓቷ ዘግይታ ስትመጣ ብዙ የዘነበወርቅ ድሆች ነፍሳቸውን እንስኪስቱ ወደ በሩ ይንደረደራሉ፡፡ ሼካው አዲስ አበባ ሲረግጡ በሕዝብ ዘንድ እጅግ የታፈሩና የተከበሩ አርቲስቶች ራሳቸውን ስተው በሸራተን በር ላይ ይራኮታሉ፡፡

ኩሩ ደላላነቴ ምን አለኝ!!