regionsዋዜማ ራዲዮ-የኢትዮጵያ መንግስት የፌደራል እና ክልል መንግስታትን ግንኙነት የሚመራበትን ረቂቅ ህግ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀቱን ሰሞኑን ገልጧል፡፡ ረቂቅ ህጉ ከህገ መንግስቱ መረቀቅ በኋላ ሳይዘገይ ይወጣል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም መንግስት ግን ህጉን ለማውጣት ሃያ ዓመታት ወስዶበታል፡፡ በመሆኑም ላለፉት በርካታ ዓመታት በፌደራሉ መንግስት እና ክልሎች መካከል ያለው ሁለንተናዊ መስተጋብር ኢመደበኛ እና ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ነበር ሲካሄድ የኖረው፡፡ አሁን ህጉ መውጣቱ ከተነገረ ዘንዳ ካሁን ቀደም የፌደራሉን እና ክልል መንግስታትን ግንኙነት የሚዳኝ ህግ ባለመኖሩ በፌደራል ሥርዓቱ ላይ ምን ጉድለቶች ታይተው ይሆን? ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ረቂቅ ህጉን አሁን ለማውጣት ለምን ፈለገ? ለመሆኑ ረቂቅ ህጉ ምን ገጽታዎች እና ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎችን መመርመር ያሻል፡፡ ቻላቸው ታደሰ ይህን ዝርዝር ያስነብበናል

ፌደራላዊ ሥርዓት በምትከተለው ኢትዮጵያ ህገ መንግስቱ ለሁለቱም የመንግስት እርከኖች የስልጣን ክፍፍል አድርጓል፡፡ አንቀጽ 52፣ ንዑስ አንቀጽ 3፣ የክልል መንግስታት የራሳቸውን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ልማት ስትራቴጂ እና ዕቅድ ማውጣት እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡ በተለይ ለፌደራል መንግስቱ በተለይ ወይም ለሁለቱም በጋራ ተለይተው ያልተሰጡ ስልጣኖች በሙሉ የክልሎች ስልጣን መሆናቸውን መደንገጉ ለክልሎች የተሰጠውን ትኩረት ሊያሳይ ይችላል፡፡ ሁለቱ መንግስታት በተለይ በማዕድን፣ ጋዝ፣ ነዳጅ እና ሌሎችም መስኮች ረገድ በጋራ እንዲጠቀሙ የሚደነግግ የጋራ ስልጣን ስላላቸው በመካከላቸው የሚኖረው ሁለንተናዊ መስተጋብር ከህገ መንግስቱ የሚቀዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የህገ መንግስቱ መንፈስ የሚነግረን በፌደራሉ መንግስት እና ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በእኩልነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንጂ ፌደራል መንግስቱ የበላይ፣ ክልሎች ደሞ የበታች የሚያደርግ ተዋረዳዊ ግንኙነት አለመሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በመካከላቸው ዘርፈ ብዙ የመንግስታት ግንኙነት መስኮች አሉ፡፡ እናም ጉዳዩ በርከት ያሉ እና አወዛጋቢ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ሊነሱበት የሚችል እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ባንጻሩ ግን የፌደራላዊ ሥርዓቱን አወቃቀር በሚመጥን ደረጃ የመንግስታቱ መስተጋብር ህገመንግስታዊ ይዘት እና የአፈጻጸሙ ህገመንግስታዊነት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን፣ ባለስልጣናት እና ምሁራን በቂ ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡ ባብዛኛው የትኩረት ማከል ሆኖ የቆየው የፌደራል መንግስቱ እና የክልሎች የተናጥል ስልጣን እና አተገባበሩ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በምሁራን ደረጃ ግን በቂ ነው ባይባልም የምርምር እና ውይይት ትኩረት መሳቡ አልቀረም፡፡

የህገ መንግስቱ መንፈስ የሚያሳየው የመስተጋብሩን አይነት እንዲሁም ሁለቱ መንግስታት የሚኖሯቸውን መብቶች እና ግዴታዎች በዝርዝር የሚወስን ህግ ወይም የፖሊሲ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ቢሆንም የፖሊሲ ማዕቀፉ ወይም ህጉ ግን ገና ሰሞኑን መረቀቁ ነው እየተገለጸ ያለው፡፡ ህገ መንግስቱን መሠረት በማድረግ የመንግስታቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚወስነውን የፖሊሲ ማዕቀፍ፣ መሠረታዊ መርሆዎች ወይም ህግ ሥራ አስፈጻሚው አካል ወይም ህግ አውጭው አካል ሊያወጣው ይችላል፡፡ አሁን የተመረጠው አካሄድ ግን ህግ አውጭው አካል በአዋጅ መልኩ እንዲያወጣው የተፈለገ ይመስላል፡፡ በርግጠኝነት የሚታወቀው ለፓርላማው ቀርቦ ሲጸድቅ ወይም በሚንስትሮች ምክር ቤት ብቻ የሚወሰን ደንብ መሆኑ ሲታይ ይሆናል፡፡

በይዘት ደረጃ ረቂቅ ህጉ በዋናነት የሚያተኩረው ሁለቱ አካላት የጋራ ስልጣናቸውን በምን ሁኔታ መምራት እንዳለባቸው መሆኑን ነው መንግስት ሰሞኑን የገለጸው፡፡ በርግጥ በመርህ ደረጃ የመንግስታትን መስተጋብር የሚወስን ማንኛውም የህግ ማዕቀፍ ክልሎች ርስበርስ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጭምር በማካተት ሊወስን ይችላል፡፡ ያሁኑ ረቂቅ ህግ ግን ከፌደራል መንግስቱ እና ክልሎች መስተጋብር አልፎ የክልሎችን የርስበርስ ግንኙነት የሚመለከት ስለመሆኑ ገና በርግጠኝነት አልታወቀም፡፡

የፖሊሲ ማዕቀፍ ወይም ወጥ የሆነ ህግ ማውጣት የሚያስፈልገው ህገ መንግስቱም ሆነ ሌሎች ህጎች በሁለቱ መንግስታት መካከል መኖር የሚገባው የትብብር ግንኙነት በግልጽ ባለመቀመጡ ነው፡፡ በጊዜ ሂደት ግን በተለምዶ ሲሰራባቸው የኖሩ ጊዚያዊ፣ ኢመደበኛ፣ ተቋማዊ ያልሆኑ እና ህገ መንግስታዊ መሰረትም የሌላቸው አሰራሮች መዳበራቸውን ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ዶክተር አሰፋ ፍስሃ ቀረብ ብሎ ያጠናው አንድ ጥናት በክልል እና ፌደራል መንግስታት የተለያዩ አካላት መካከል በጋራ የትብብር መድረኮች፣ ጊዚያዊ እና ቋሚ ኮቴዎች፣ ስብሰባዎች፣ የደብዳቤ ልውውጦች እና በኢመደበኛ የገዥው ፓርቲ ሰንሰለት አማካኝነት የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ሲቀላጠፍ መቆየቱን ያትታል፡፡

በሥራ አስፈጻሚው ደረጃ የፌደራል እና ክልል ግንኙነቶችን ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ለማስተባበር ሙከራ የተደረገው እስከ 1993ቱ የህወሃት ክፍፍል ድረስ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ስር ተዋቅሮ በነበረው የክልል ጉዳዮች ዘርፍ በሚባለው ተቋም አማካኝነት ነበር፡፡ ክልሎችን በማዕከል ሆኖ እንደ ሞግዚት ይጠረንፍ የነበረው ይኸው ዘርፍ ግን ጠንከር ያሉ ትችቶች ይቀርቡበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዚያት ፌደሬሽን ምክር ቤት እና ፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር በተወሰነ መልኩ የበይነ-መንግስት ግንኙነትን ለማቀላጠፍ ኢመደበኛ አካላትን ለማዋቀር መሞከራቸው ተጠቃሽ እንደሆነ ጥናት ያደረጉ ወገኖች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፌደራሉ ህግ ውጭ አካላት እና የክልል አፈ ጉባዔዎች የጋራ የምክክር መድረኮች ማካሄድ መመራቸው አንዱ ተጠቃሽ እምርታ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በበኩሉ ከስድስት ዓመታት በፊት በአዋጅ ተሸሽሎ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በየሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የመንግስታት ግንኙነትን የሚመለከቱ ዘርፎች ለማቋቋም ጥረት ሲያደርግ ኖሯል፡፡ መስሪያ ቤቱ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ከተሰጠው ስልጣን ጋር በማይጋጭ መልኩ በፌደራሉ እና ክልል መንግስታት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማዕከል ሆኖ የመስራት ህጋዊ ስልጣን አለው፡፡ ሰሞኑን በተረቀቀው ህግ ግን የሁለትዮሽ መስተጋብሩን ለመምራት ሌላ አዲስ ተቋም እንደሚቋቋም ነው የተነገረው፡፡

ልማዳዊውን አሰራር የሚተቹ ወገኖች ግን ተቋማዊ እና በህጋዊ ማዕቀፍ የታጠረ ግንኙነት አለመኖሩ በየደረጃው የተንዛዙ፣ ጊዜን እና ሃብትን የሚያባክኑ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ በር ከፍቷል በማለት ይተቹታል፡፡ በፌደራል ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች እና በክልል አቻዎቻቸው መካከል የሚካሄደው የደብዳቤ ልውውጥም የፌደራል ተቋማት በተለምዶ መመሪያ አውራጅ የሆኑበት ተዋረዳዊ ግንኙነት አስፍኗል፤ ይህም የክልሎችን ሉዓላዊ እና ህገመንግስታዊ ሥልጣን ሸርሽሯል የሚሉ በማስረጃ የተደገፉ ሙግቶች ይቀርቡበታል፡፡ የሁለትዮሽ የጋራ ስብሰባዎችም በገዥው ፓርቲ ደንብ መሰረት በሙሉ ስምምነት የሚፈጸሙ እንጂ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ክርክር የሚደረግባቸው መድረኮች አይደሉም፡፡ ዶክተር አሠፋ ፍስሃ በጥናቱ እንደጠቆመው የጋራ መድረኮቹ በፌደራሉ መንግስት ፍላጎት እና ጊዜ ሰሌዳ የሚወሰኑ እንጂ የክልሎች እጅ ስለሌለበት እውነተኛ የሁለትዮሽ መስተጋብር መፍጠር አላስቻሉም፡፡

መንግስት እስካሁን ህጉን ለማውጣት ያልተቻኮለበት አንዱ ምክንያት በገዥው ፓርቲ መዋቅር አማካኝነት በሚከናወነው ኢመደበኛ አሰራር በመተማመኑ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ በቀጥታ የሚያስተዳድረው አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልልን ቢሆንም ቀሪዎቹን ታዳጊ ክልሎችም በአጋር ፓርቲዎች አማካኝነት መጠርነፉ የልብ ልብ ሰጥቶታል፡፡ የፓርቲውን መዋቅር ፖሊሶወቹ ሳይሸራረፉ በሁሉም ክልሎች እንዲተገበሩ ለማድረግም ተጠቅሞበታል፡፡ በታዳጊ ክልሎች ይቅርና በትላልቆቹ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል ሳይቀር የፓርቲውን መዋቅር በመጠቀም የክልል ፕሬዝዳንቶችን እና ካድሬዎችን እንደፈለገ ሲቀያይር ይስተዋላል፡፡ በዚህም ተዋረዳዊ ግንኙነት ሳቢያ የክልሎችንም ሆነ የፌደራል መንግስቱን ህገ መንግስታት ወይም የሁለቱን አካላት የጋራ ስልጣን እና ግንኙነት የሚፈታተን ጉልህ ቅራኔ ተከስቶ አያውቅም፡፡

በየትኛውም ፌደራላዊ ሥርዓት በሁለቱ መንግስታት ትብብር እና ፉክክር መኖሩ የሚጠበቅ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ሁሉም ክልሎች በብዙ መልኩ በፌደራል መንግስቱ ላይ ጥገኞች መናቸውን እና ግንኙነቱም ተዋረዳዊ መሆኑን እነ ፕሮፌሰር አለም ሃብቱ፣ ፕሮፌሰር ኤድመንድ ኬለር እና ፕሮፌሰር ሳራ ቮግን ጨምሮ ለሥርዓቱ ቅርበት ያላቸው እነ ዶክተር አሠፋ ፍስሃ በተለያዩ ጥናቶቻቸው ማስረጃዎችን እያጣቀሱ አስረግጠው ይተቻሉ፡፡ በዕደገት ኋላቀርነታቸው ሳቢያ ከፌደራል መንግስቱ በየዓመቱ የበጀት ድጎማ ቢቀበሉም ያልተመጣጠነውን ተዋረዳዊ የወጭ እና ገቢ አቅም ግን ለማጥበብ አለመቻሉን ነው ሪፖርቶች እና የባለሙያዎች ጥናቶች የሚያረጋግጡት፡፡ ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ጋር ከሚጋሯቸው የጋራ ሃብቶቻቸው ከሚገኘው ገቢ ክፍፍል ምጣኔ ላይ ቅሬታ ቢያነሱ ቀዳሚ ተፈጻሚ የሚሆነው የፌደራሉ መንግስት ጥቅም እንደሆነ ነው ጥናት አድራጊዎቹ የሚያምኑት፡፡ ምክንያቱም ክልሎች ፌደራል መንግስቱን የሚገዳደሩበት ብቃትም ሆነ ስነልቦና ለማዳበራቸው አንዳች አብነት መስጠት እስኪቸግር ድረስ መጠነኛ ቅራኔ እንኳ አይሰማም፡፡

ክልሎች የፌደራሉ መንግስቱ በሚያወጣው ህግ መሰረት መሬትን እና የተፈጥሮ ሃብትን የማስተዳደር ስልጣን ቢኖራቸውም እስካለፈው ወር ድረስ ለበርካታ ዓመታት ከ5000 ሄክታር በላይ ያሉ ለም መሬቶቻቸውን በአደራ ሲያስተዳድር የቆየው ፌደራል መንግስቱ ነው፡፡ ፌደራል መንግስቱ ግን አስዳደራዊው ስልጣኑን ከሁሉም ክልሎች ባንዴ የተረከ በተፅዕኖ ነው ወይንስ በጋራ መግባባት ነው የሚለውን ጥያቄ በርግጠኝነት ለመመለስ አስቸጋሪ ያደረገውም ይኸው የተዛባ ግንኙነት ነው፡፡ ክልሎች ፌደራል መንግስቱ መሬቱን ባስተዳደረበት አግባብ ወይም ባስገኘው ትሩፋት እና ጉዳት ላይ አንዳችም ይፋዊ ቅሬታም ሆነ ጥያቄ ሳያነሱ ስልጣኑ መመለሱም ይህንኑ የተዛባ ግንኙነት የሚያጠናክር አብነት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በተለይ በቅርቡ የታየው መጠነ-ሰፊ ህዝባዊ አመፅ ገዥው ድርጅት አለኝ የሚለውን የተጋነነ ቅቡልነት አጣብቂኝ ውስጥ ስላስገባበት ለሰሞኑ ህግ መረቀቅ ምክንያት ሆኖ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ ለዚህም ይመስላል የሰሞኑ ረቂቅ ህግ መውጣቱ ፌደራል መንግስቱ እና አንድ ክልል በተለያዩ ሁለት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርተዎች ቢመሩ ህጉ ፖለቲካዊ እና ህጋዊ አለመግባባቶችን ከወዲሁ ለመቅረፍ ይረዳል የሚል ምክንያት እየቀረበ ያለው፡፡ አሁን ባለው ኢመደበኛ አሰራር ከቀጠለ ለአብነት ኦህዴድ/ኢህአዴግ ኦሮሚያ ክልል ላይ በምርጫ ተሸንፎ ላንድ ተቃዋሚ ድርጅት ቢያስረክብ በስልጣን እና ሃብት ክፍፍል ረገድ ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግጭቶች እንደሚነሱ ይጠበቃል፡፡

“አንድ ተቃዋሚ ድርጅት አንድን ክልል ቢያስተዳድር…” የሚለው ምክንያት ባሁኑ ሰዓት ከኢህአዴግ አንደበት መሰማቱ ግን ድርጅቱ ወደፊት ያሰበውን ዕቅድ በተወሰነ ደረጃ የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለምን ቢሉ ምናልባት ሀገሪቱን እስከ ቀጣዩ ብሄራዊ ምርጫ ተቆጣጥሮ መቀጠል ከቻለ ቢያንስ አንድ ክልል ለተቃዋሚ ፓርቲ ለመልቀቅ አስቦ ይሆን? የሚል ጥርጣሬ የሚፈጥር በመሆኑ፡፡ የሁለትዮሽ መስተጋብሩ ተቋማዊ እና ህጋዊ ሲደረግ የገዥው ግንባር ኢመደበኛ አሰራር እና በክልሎች ላይ ያለው ተጽዕኖ ይቀንስ ይሆን? የሚለው ጉዳይ ግን የተማከለ አወቃቀር እና አሰራር ላለው ኢህአዴግ በቀላሉ የሚዋጥለት አይሆንም፡፡

ህገ መንግስቱ አንድ የጋራ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ቢያልምም በተለይ በክልሎች መካከል የርስበርስ መስተጋብር እንዳልዳበረ ማስረጃ መጥቀስ አያሻውም፡፡ በተቋማዊ ባህል ላይ የተገነባ ግንኙነት አለመዳበሩ ክልሎችን የሚያስተዳድሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀላሉ የብሄርተኝነት ስሜቶችን በመቀስቀስ ግጭት እና የመገንጠል አዝማሚያዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚለው ስጋትም ከጊዜ ወደጊዜ ስር መስደዱ ይሰማል፡፡ ስለሆነም ህጉ እንዲህ ዓይነት አዝማሚያዎችን ባጭሩ ለመቅጨት እንደሚረዳ የሚያምኑ ታዛቢዎች በርካታ ናቸው፡፡ ረቂቅ ህጉ ምን ያህል ክልሎችን እንዳሳተፍ እና ጥቅሞቻቸውንስ ምን ያህል እንደሚያስጠብቅላቸው ግን ወደፊት የሚታይ ነው፡፡