Presentation of Credentialsኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች ብትሆንም ከድርጅቱ ምስረታ አንስቶ የፀጥታው ምክር ቤት ጊዚያዊ አባል የሆነችው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከ1967 እስከ 1968 እና ከ1989 እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ብቻ፡፡ መጀመሪያ ጊዜ በንጉሰ ነገስቱ በኋላ ደግሞ በደርግ ዘመነ-መንግስት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ መቀመጫውን አግኝታ አታውቅም፡፡
በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች የሆነችው ግብፅ ከዘንድሮው ምርጫዋ ጋር በጥቅሉ ለአምስተኛ ጊዜ መቀመጫውን አሸንፋለች፡፡ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ሁለት ጊዜ፡፡ ናይጄሪያም እንዲሁ ለአምስተኛ ጊዜ ደርሷታል፡፡ ኢትዮጵያን እነዚህ ሀገሮች ብቻ ሳይሆኑ ዛምቢያ፣ ኡጋንዳ፣ ቱኒዥያ፣ ጋና፣ ጋቦን እና አልጀሪያም ይበልጧታል፡፡ አሁን እስከ 2017 መጨረሻ አፍሪካን የሚወክሉት ግብፅ እና ሴኔጋል ሆነዋል፡፡

(ቻላቸው ታደሰ በድምፅ ያሰናዳውን ዘገባ እዚህ ያድምጡ)


ሀገራችን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራችነቷ ባሻገር ለድርጅቱ ዓለም ዓቀፍ ሰላም አስጠባቂ ሰራዊት በማዋጣት ረገድም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትመደባለች፡፡ በአህጉር ደረጃም ቢታይ የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫም ነች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በሱማሊያ ሰፍሮ በሚገኘው የአሚሶም ተዋጊ ሃይል ውስጥ ቁልፍ ተሳትፎ እንዳላት ይታወቃል፡፡ በኢጋድ ውስጥ በሰላምና ፀጥታ በተለይም ለደቡብ ሱዳን ሰላም የምታደርገው አስተዋፅኦም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡ እነኝህና ከምዕራባዊያን ጋር ያላት የፀረ-ሽብር አጋርነት እና በቡድን ሃያ ሀገሮች ያላት ተሳትፎ ተደማምረው ሀገሪቱ ዓለማቀፋዊ ተደማጭነት እንዲኖራት እንዳደረጓት መንግስት ሲናገር ይደመጣል፡፡
እንደሚታወቀው የፀጥታው ምክር ቤት ጊዚያዊ መቀመጫ የሚገኘው የየሀገሮችን ድጋፍ በጠንካራ እና ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ በማሰባሰብ እንጂ በችሮታ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሴኔጋል በያዝነው ዓመት መቀመጫውን ያሸነፈችው የምዕራብ አፍሪካው ድርጅት “ኢኮዋስ” የወቅቱ ሊቀመንበር መሆኗን በመጠቀም ባደረገችው ጠንካራ ዘመቻ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ግብፅም እንዲሁ ለተባሩት መንግስታት ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች እያደረገች ያለችውን አስተዋፅኦ እንዲሁም በየመን፣ ሊቢያ እና በጠቅላላው የመካከለኛው ምስራቅ ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ዓብይ ሚና እየተጫወተች መሆኗን በመጥቀስ ቅስቀሳ አድርጋለች፤ ተሳክቶላታልም፡፡
ኢትዮጵያ አልተጠቀመችባቸውም እንጂ የአብዛኛዎቹን የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች ነበሯት፤ አሁንም አሏት፡፡ ስለሆነም መቀመጫውን ለማግኘት አለመሞከሯ ከኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ዲፕሎማሲ ድክመት ውጭ ሌላ ምክንያት ሊኖረው አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከአፍሪካዊያን ሃያላን ሀገሮች አንዷ መሆኗን መስበክ ትርጉም ያለው የማይመስለው፡፡
በዚህ ወቅት ይህንን ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገው ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ውዝግብ ወደ ተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤት እወስደዋልሁ በማለት መዛት በጀመረችበት ማግስት ዘንድሮ ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ ለሁለት ዓመታት መቀመጫውን በማሸነፏ ነው፡፡ መቀመጫውን ለማግኘት ከፈለገችበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይኸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብ ሊሆን ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫውን ለማግኘት አለመፎካከሩ ብቻ ሳይሆን የግብፅንም ጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማክሸፍ ምንም ጥረት ሲያደርግ አልታየም፡፡ በአንፃሩ ግን ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንድትቸራቸው ለጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ይፋዊ ደብዳቤ ልከው ነበር፡፡ መንግስትም የግብፅን ጥያቄ እንደ መልካም ዜና በሜዲያዎቹ ሲያስተጋባው ተደምጧል፡፡
መቼም የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያንዣበበው አለመግባባት የተለሳለሰ መስሎ ቢቆይም ሰውዬው ግን ብዙ አማራጮችን ከማየት ወደ ኋላ አላሉም፡፡ እንደ ቀደምቶቻቸው ዛቻን ከመጠቀም ይልቅ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ብዙ መንገዶችን እያፈላለጉ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ለነገሩ ባለስልጣናቶቿም ይህን አልደበቁም፡፡ በቅርቡም “አህራም ኦንላይን” የተሰኘው የግብፅ የድረ ገፅ ጋዜጣ የግብፁ የመስኖ ሚንስትር ሆሳም ኤል-ሞጋዚ ሀገራቸው በህዳሴው ግድብ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚስችሏት ካርዶች በእጇ እንዳሉ ተናግረው ነበር፡፡ ከካርዶችም አንዱ ውዝግቡን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰድ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ከሚያጠኑት ሁለት አማካሪ ኩባንያዎች መካከልም የሆላንዱ “ዴልታሬስ” ገለልተኛ እና ደረጃውን የተበቀ ጥናት ለማድረግ የሚያስችለኝ የተመቻቸ ሁኔታ የለም በማለት በመስከረም ወር መጀመሪያ ከስራው በፍቃዱ ራሱን በማግለሉ ምክንያት ጥናቱ ተቋርጧል፡፡ ተተኪ ድርጅትም አልተቀጠረም፡፡ ግብፅም በዚህ ደስተኛ እንዳልሆነች ከካይሮ የሚወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
ይህንን ተከትሎም የግብፅ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር ሌላ አማራጭ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ግብፅ በዚህ ወር መጨረሻ ካይሮ ላይ እንዲካሄድ ጠርታው የነበረው አስቸኳይ የሦስትዮሽ ስብሰባም ስላልተካሄደ ጥናቱን እንደገና የማስቀጠል ፍላጎቷ ተኮላሽቶባታል፡፡ በዚህ ሁሉ መጓተት ውስጥ ደግሞ የግድቡ ግንባታ መቀጠሉ አሳስቧታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎችም ውዝግቡን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንድትወስደው ሊገፋፏት ይችላሉ፡፡
በጥቅሉ ሲታይ በኢትዮጵያ እና ግብፅ መካከል ቀስ በቀስ ልዩነቶች እየሰፉ ነው፡፡ ግብፅም ከሁለት ወራት በኋላ የፀጥታው ምክር ቤት መቀመጫዋን ስትረከብ ምን እንደምታደረግ ጊዜው ሲደርስ ይታያል፡፡ በኒውዮርክ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲም የግብፅን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምን ያህል እንደሚከታተል እንዲሁ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ከዚያም በፊት ሁኔታዎች የተለየ መልክ ሊይዙም ይችላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የውዝግቡም ሆነ የግድቡ የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡