• ምክር ቤቱ ጊዜያዊ ሰብሳቢ ከሀላፊነታቸው ለቀዋል
One of recent virtual meetings of the council members

ዋዜማ ራዲዮ- በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) መንግስትን በቁልፍ የኢኮኖሚ ጉዳዮች በምክርና በሙያ እንዲያግዝ የተቋቋመው ገለልተኛ ምክር ቤት በውስጡ በተፈጠረ አለመግባባት እስካሁን ወደ ስራ መግባት እንዳልቻለ ዋዜማ ከአባላቱ ስምታለች።

በኢኮኖሚ ዘርፍ በሀገር ቤትና በውጪ ሀገር የካበተ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ያካተተው ምክር ቤት በአባላቱ አለመግባባት ሳቢያ ላለፉት ስድስት ወራት ወደ ታሰበለት ስራ መግባት አልቻለም።

ይልቁንም አለመግባባቱ ተባብሶ ምክር ቤቱን በጊዜያዊነት ሲመሩ ሲመሩ የነበሩት ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) ራሳቸውን ከምክር ቤቱ አግልለዋል።

የምክር ቤቱ አመሰራረት

የገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት የተቋቋመው በኢትዮጵ ያሉ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለማቃለል ፣ ድህነትን ለመቀነስ እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ እድገት እንቅፋቶችን በመለየት የሚረዱ ሀሳቦችን በማመንጨት ለመንግስት የትግበራ ግብአት እንዲሆን ምክር ማቅረብ ነው።

ምክር ቤቱን የማቋቋሙ ሀሳብ የመጣው በዋናነት በዓለም ባንክ የረጅም አመታት ልምድ ባላቸው ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) እና በአሜሪካ ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ለማ ወልደሰንበት እንዲሁም በማክሮ ኢኮኖሚክስ ባለሙያው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ተጨማሪ አስተያየት ሰጪነት ነበር ።

ምሁራኑ ምክር ቤቱን የማቋቋም ሀሳብ ለመንግስት ካቀረቡ በሁዋላ ፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት አባል መሆን የሚፈልጉ ምሁራን የትምህርተና የስራ ማስረጃቸውን እንዲያስገቡ ባለፈው አመት ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር።

በዚህም መሰረት ማስረጃቸውን ካስገቡት ውስጥ 13 ፣ መንግስት በራሱ መስፈርት ደግሞ ተጨማሪ ሶስት የኢኮኖሚክስ ምሁራንን በጥቅሉም 16 ምሁራን የተካተቱበት የገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት ታህሳስ 5፣ 2013 አ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ፣ ፕሮፌሰር ለማ ወልደሰንበት እና ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) በተጨማሪም እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር); ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሀና ፣ ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ ፣ ፕሮፌሰር ብርሀኑ አበጋዝ እና አለማየሁ ስዩም (ዶ/ር) በምክር ቤቱ አባልነት ተካተዋል።

ከ16ቱ የምክር ቤት አባላት ስድስቱ ስራ እና መኖሪያቸው በውጭ ሀገር ሲሆን አስሩ ደግሞ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።

ምክር ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ ከአሜሪካ የመጡትና የምክር ቤቱ ምስረታ የሀሳብ ጠንሳሾች ከሆኑት መካከል ዮናስ ብሩን (ዶ/ር) ለኢኮኖሚ ምክር ቤቱ ጊዜያዊ ሰብሳቢ አድርጎ የመረጠ ሲሆን የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና እውቁን ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ለማ ወልደሰንበትን ደግሞ ምክትል አድርጎ መርጧል።

የአለመግባባቱ ምክንያት

ዋዜማ ራዲዮ እንደተረዳችው አለመግባባቶች የጀመሩት የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ምክር ቤቱን በሰብሳቢነት መምራት ያለባቸው ሀገር ውስጥ ያሉ አባላት እንጂ መኖሪያቸውን ውጭ ያደረጉት አይደሉም የሚል ጥያቄን አንስተዋል።

ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ደግሞ ለሰብሳቢነት መታየት ያለበት ብቃት ብቻ መሆን መሆን አለበት ፤ እንደውም ስራ እና መኖርያቸው ውጭ ሀገር የሆኑ አባላት ምክር ቤቱን እንዲመሩ መደረጉ ከሚሰሩባቸው አለማቀፍ ተቋማት ወረት በማምጣት ምክር ቤቱን አጠናክሮ ለመምራት የሚል አቋም ያዙ።

አለመግባባቱ ሊቀራረብ ስላልቻለ ሰብሳቢ መመረጥ ያለበት ከሀገር ውስጥ ሙያተኞች ነው የሚል አቋም ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት በቁጥር እንበዛለን የሚል አቋም በመያዝ አዲስ የምክር ቤት ሰብሳቢ ፣ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም ጸሀፊ ለመምረጥ እንቅስቃሴ ጀመሩ።

የምክር ቤቱ አመራር ላይ የተነሳው አለመግባባት ብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤቱን ራእይ እና መተዳደርያ ደንቦችም ላይ ጥላ በማጥላቱ ምክር ቤቱ ስድስት ወር አልፎትም ስራ መስራት አልቻለም።

በዚህ ውዝግብ መሀል ምክር ቤቱ እንዲመሰረት ሀሳብ ካቀረቡት ውስጥ አንዱ የሆኑትና ጊዜያዊ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የነበሩት ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ ሚናቸው ራሳቸውን አግለዋል። ዮናስ ብሩ በዚህ ዙርያ ያላቸው አቋም በማህበራዊ ሚድያ ይፋ መሆኑንም ተመልክተናል።

 አንድ የምክር ቤቱ አባል ለዋዜማ ራድዮ አስተያየት ሲሰጡ የምክር ቤቱ አላማ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቃሚ ሀሳብ ማቅረብ እንደመሆኑ መጠን በሰብሳቢነትና ምክትል ሰብሳቢነት ጉዳይ ላይ አለመግባባት ለምን እንደተፈጠረ ግራ እንደገባቸው ገልጸዋል።

የገለልተኛ የኢኮኖሚ ምክር ቤቱ አላማ መንግስት የኢኮኖሚ ምክር ሲጠይቅ ምክር መስጠት ነው? ወይንስ ለሀገሪቱ ይበጃል ያለውን ራእይ መንደፍ ? የምክር ቤቱ አባላት መካከል ግልፅነት የጎደላቸውና እያወዛገቡ ያሉ ሀሳቦች መሆናቸውን አባላቱ ይናገራሉ።

አዲስ ምርጫ

ዮናስ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ባለፈው ሳምንት ቀሪ የገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ማካሄዳቸውን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። በምርጫው መሰረትም አለማየሁ ስዩም (ዶ/ር) የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ፣ ፕሮፌሰር ብርሀኑ አበጋዝ ምክትል ሰብሳቢ፣ እንዲሁም ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) ጸሀፊ ሆነው ተመርጠዋል። ነገር ግን ሂደቱ ህገ ወጥ ነው በሚል ምርጫው ላይ ያልተገኙ የምክር ቤቱ አባላት እንደነበሩ አረጋግጠናል።

ምክር ቤቱ ገና ከመቋቋሙ እንዲህ አይነት መጠላለፍ ውስጥ መግባቱ ወደፊትም ስራውንም ማከናወን መቻሉ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው መሆኑን ሁለት አባላቱ የነገሩን ሲሆን በነበሩ ውዝግቦች ለምክር ቤቱ መመስረት ምክንያት የሆኑ ምሁራን እንዲገለሉ መደረጉም ተገቢ አለመሆኑን ገልጸውልናል።

ከውዝግቡ ባሻገር ገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ  ምክር ቤቱን ተቋማዊ ቅርጽ ለማስያዝ የተለያዩ ሰነዶች አዘጋጅተው ለመንግስት ማቅረባቸውን ነግረውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]