• ከማዳበሪያ እና ነዳጅ ውጪ ሌሎች ምርቶችን ማስገባትንም መመሪያው ለውጭ ባለሀብቶች ይፈቅዳል

ዋዜማ- መንግስት ለበርካታ አመታት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ እንዲሳተፉበት ተከልሎ የቆየው ቡናን ፣ ጫትን ፣ የቁም እንስሳትን እና ቆዳና ሌጦን ለውጭ ገበያ የመላክ ስራ ለውጭ ባለሀብቶች የሚፈቅድ መመሪያ ማዘጋጀቱን ዋዜማ ተረድታች።

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በሚመራው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የተዘጋጀው እና ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ (መመሪያ) መንግስት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ውሳኔን ለመወሰን ያበቃውን ምክንያት ያትታል።

የመመሪያው መግቢያ እንደሚለው ከሆነ የግብርና ምርቶቹን ለውጭ የመላኩ እና የአስመጪነትን ዘርፍ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ መከለሉ የተጠበቀውን ውጤት እንዳላስገኘ ይገልጻል። ብሎም ከለላውን ለህገ ወጥ ተግባር የሚጠቀሙ አካላትን እንደፈጠረ ፣ ላልተገባ ውድድር መንገድን እንደከፈተ ፣ በርካታ ቅሬታዎችን እንዳስከተለ እና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማከናወንም እንዳላስቻለ አክሎም ገልጿል።

መመሪያው አክሎም በእያንዳንዱ የወጪ ንግድ ዘርፎች ለመሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች ዘርዝሯል።

በመመሪያው መሰረት ከኢትዮጵያ ገበያ ጥሬ ቡናን ገዝቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚፈልግ የውጭ ባለሀብት ላለፉት ተከታታይ ሶስት አመታት፣ ቢያንስ በአማካይ በየአመቱ ከኢትዮጵያ 10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ቡናን የገዛ መሆን እንደሚጠበቅበት እና ፍቃዱን ባገኘበት አመት ቢያንስ 10 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ቡናን መላክ እንደሚችል የንግድ ውልን ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም መመሪያው ያዛል።

ሆኖም የውጭ ባለሀብቱ ከኢትዮጵያ ቡና የመግዛት ታሪክ የሌለው ከሆነ ቡና የመላክ ፍቃድን ለማግኘት የተረጋገጠ እና አስተማማኝ ገበያ ያለው መሆኑን የሚያሳያ ሰነድ እና ፍቃድ ባገኘበት አመት 12.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ቡናን እንደሚልክ የንግድ ውል ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ያትታል።

የቅባት እህልን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ደግሞ አንድ የውጭ ባለሀብት ወይንም ኩባንያ ቢያንስ ላለፉት ሶስት አመታት በአማካይ በየአመቱ አምስት ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የቅባት እህል የገዛ እንዲሁም ፍቃዱን ባገኘበት አመት አምስት ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የቅባት እህልን ለመላክ የሚያስችለውን የንግድ ውል ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም መመሪያው ያዛል።

ነገር ግን የውጭ ኩባንያው ወይንም ባለሀብቱ ከኢትዮጵያ የቅባት እህል የመግዛት ታሪክ ከሌለው አስተማማኝ ገበያ ያለው መሆኑን እና ፍቃድ ባገኘበት አመት ቢያንስ 7.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የቅባት እህልን መላክ እንደሚችል ውል ማቅረብ ይጠበቅበታል ይላል መመሪያው።

በጫት የወጪ ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልግ ባለሀብትን በተመለከተ መመሪያው ፣ ባለሀብቱ ወይንም ኩባንያው ባለፉት ሶስት አመታት ፣ በአማካይ በየአመቱ አንድ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ጫትን ከኢትዮጵያ የገዛ እና እንዲሁም ፍቃድ ባገኘበት አመት አንድ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ጫትን ለውጭ ገበያ መሸጥ እንደሚችል የንግድ ውል ማቅረብ እንዳለበት ያዛል። ካልሆነ ግን ባለሀብቱ ፍቃዱን ባገኘበት አመት 1.5 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ጫትን ለመሸጥ የሚያስችለውን ውል ማቅረብ እንዳለበት ያትታል።

የቁም እንስሳት ለውጭ ገበያ ማቅረብን በተመለከተ መመሪያው አስገዳጅ የቀድሞ የግዥ ታሪክ እንደማይጠየቅ ጠቅሷል።እንዲሁም ቆዳ እና ሌጦን እንዲሁም የደን ምርቶችን በተመለከተ፣ በነዚህ የውጭ ንግድ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ላለፉት ሶስት አመታት በአማካይ በየአመቱ እያንዳንዳቸው 500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ምርቶቹን የገዙ እና ፍቃዱን ባገኙበት አመት 500 ሺህ ዶላር የሚያወጡ እያንዳንዳቸው ምርቶችን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ ውል ማቅረብ እንዳለባቸው መመሪያው ይገልጻል።

ባለሀብቶቹ በቆዳ እና ሌጦ እንዲሁም በደን ምርቶች ዘርፍ ከኢትዮጵያ የመግዛት ታሪክ ከሌላቸው ፍቃድ ባገኙበት አመት ቢያንስ 750 ሺህ ዶላር የሚያወጡ እያንዳንዳቸው ምርቶችን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡና ለዚህም አስተማማኝ ገበያ እንዳላቸው የሚያሳይ ውል ማቅረብ እንዳለባቸው ይጠበቃል። በሌላ በኩል በሌሎች ምርቶች የወጪ ንግድ ላይ መሰማራት ፈልገው ግን ከኢትዮጵያ የመግዛት ታሪክ የሌላቸው ባለሀብቶች ቢያንስ 500 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸው እነዛን ምርቶች ፍቃድ ባገኙበት አመት ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ የሽያጭ ውል ማቅረብ አለባቸው ተብሏል።

አስመጪነትን በተመለከተም አዲሱ መመሪያ የትኛውም የውጭ ባለሀብትም ሆነ ኩባንያ ከነዳጅ እና ማዳበሪያ ውጭ የትኛውንም ምርት ሀገር ውስጥ ማስገባት ይፈቅዳል። ሆኖም ምርቶችን ማስመጣት የሚፈልገው ኩባንያም ሆነ ባለሀብት ሀገር ውስጥ ለማምረት ጥሬ እቃ የሚያስገባ ከሆነ እና ወኪል ከሆነ የሚጠበቅበት በሁለቱ ስራዎች ላይ የተሰማራ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ምርት አስመጪ ለመሆን የሚፈልገው የውጭ ባለሀብት እና ኩባንያ በአመት በትንሹ 10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ምርት ማስገባት ፍቃድ ለማግኘት እንደ መስፈርት ተቀምጦለታል።

የዚህ መመሪያ መውጣት የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም አቀፍ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ለማግኘት ኢኮኖሚውን ክፍት ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ነገር ግን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ምንጫችን ለዋዜማ  ተናግረዋል። እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ የተፈቀደ ነበር። የውጭ ባለሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ንግድ ለመሰማራት በምርቱ ላይ እሴት መጨመር ይጠበቅበታል።

“እርግጥ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ለውጭ ኩባንያዎች መፈቀዱ በእጅጉ እያጠረ ያለውን የውጭ ምንዛሬን ለማቃለል እንደ መንገድ ቢቆጠርም ፣ በተለይ አሁንም ሀገር ውስጥ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ምርት የላኩበትን የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገራቸው መውሰድ በጣም እየተቸገሩ በመሆኑ፣ አሁንም ቡና እና መሰል ምርቶች ላይ መሰማራት ለውጭ ባለሀብቶች እንደ ስጋት ይቆጠራል ብለውናል” ምንጫችን።

“እንደዚሁም ቢሆን ግን በመመሪያው ለውጭ ባለሀብቶች ለላኪነት የተቀመጡ መስፈርቶች መንግስት ከውጭ አበዳሪዎች ብድር ለማግኘትና ከላኪዎችው የውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ የቸኮለ አስመስሎታል ” ያሉት ምንጫችን “በአንድ አመት 10 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ቡና አስገዳጅ አርጎ ለማስላክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብት መክፈት አያስፈልግም ፣ ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ባለሀብት ሆነው 10 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ቡናን በወር የሚልኩ በርካታ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አሉ” ብለውናል።

“ምርት አስመጪነት ለውጭ ባለሀብቶች መፈቀዱ በአግባቡ ከተተገበረ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዳይጎዱ ተገቢው ስራ ከተሰራ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርም ሊያግዝ ይችላልም “ብለዋል የዋዜማ ምንጭ።

ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በብዙ መልኩ ለውጭ ውድድር ክፍት የሚያደርገው መመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚመሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የጸደቀ ሲሆን ከመቼ ጀመሮ እንደሚተገበር ግን ዋዜማ በተመለከተችው ሰነድ ላይ አልተብራራም። [ዋዜማ]