ዋዜማksa ራዲዮ- በኳታር እና ሳዑዲ-መራሽ ዐረብ ባህረ ሰላጤው ሀገራት መካከል የተካረረው ሁለንተናዊ ቀውስ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አሻራውን ማሳረፉ የሚቀር አይመስልም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ በቀጥታ የውዝግቡ አካል ባትሆንም ዳፋው ግን በተለይ በኤርትራ እና ሱማሊያ ባላት ጅኦ-ፖለቲካዊ ጥቅሞች ላይ ምን አወንታዊ ወይም አሉታዊ አንድምታ ያስከትል ይሆን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

ከኳታርም ሆነ ከሳዑዲ ወዳጅ የሆኑ የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ከማ ጎን እንደሚቆሙ ሲቸገሩ ታይተዋል። በተለይ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ኤርትራ። ኢትዮዽያ ሁለቱም ወገኖች በድርድር ጉዳያቸውን እንዲፈቱ ፍላጎቷ መሆኑን ገልፃለች። ይህ ቀውስ ለአፍሪካ ቀንድ የረጅምና የአጭር ጊዜ መዘዝ እንዳለው ከወዲሁ የሚናገሩ ብዙ ናቸው።

ላለፉት ጥቂት ዐመታት ኢራን፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ሳዑዲ እና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በአፍሪካ ቀንድ ክፍለ አህጉር የየራሳቸውን ጅኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ለመጫን የሚራኮቱበት ቀጠና ሆኗል፡፡ በተለይ ቱጃሮቹ ሳዑዲ እና ኳታር የኤርትራን እና ሱማሊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአማላይ ገንዘባቸው ሲጫረቱት ይታያሉ፡፡ የባህረ ሰላጤው መንግስታት የሱኒ እና ሺዓ ክፍፍልን ወደአፍሪካ ቀንድ በማጋባት እና በእስልምና ሐይማኖት ውስጥ የውዝግብ ምንጭ እንዲሆን በማድረግ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የሚከራከሩ ታዛቢዎችም ቀላል አይደሉም፡፡

በተለይ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሱማሊያ ከኳታር ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጎማ ሲያገኙ ስለቆዩ ቀውሱ ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ኳታር፣ ሳዑዲ እና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በተለይ ለሱማሊያ ሰብዓዊ ርዳታ በማቅረብ እና መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የክፉ ቀን ደራሽ ከመሆናቸው ባሻገር ተቀናቃኝ የጎሳ ሃይሎችን በገንዘብ በመደጎም የየራሳቸውን ጆኦፖለቲካዊ ፍላጎት ለመጫን ሲታትሩ ይታያሉ፡፡ በቅርቡ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ያደረጉት ይህንኑ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ፈርማጆም ከኳታር እና ሳዑዲ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ስላላቸው ያሁኑ ቀውስ አሰላለፋቸውን ለማስተካከል የሚገደዱበት ሁኔታ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ መንግስታቸው ላሁኑ ገለልተኛ አቋም መያዙን ይፋ ቢያደርግም ይህ አቋም ግን ሳዑዲን እና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስን እንደማያረካ ነው ታዛቢዎች የሚገልጹት፡፡ ባለፈው ዐመት እንኳ ሱማሊያ በሳዑዲ ግፊት ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ስታቋርጥ የ50 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ እንደተሰጣት የሚያስታውሱ ወገኖች ሳዑዲ አሁንም ተመሳሳይ ተፅዕኖ እና ማባበያ እንደምትጠቀም በጽኑ ያምናሉ፡፡

የሳዑዲ ግንባር ቀደም አጋር የሆነችው የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በያዝነው ዐመት የሱማሌላንዱን በርበራ ወደብ በኩንትራት ከመረከቧም በላይ አወዛጋቢ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ስለመሰረተች ኳታር ከዋናዋ ሰማሊያ ጋር ትስስሯን ማጠናከር አንዱ የመገዳደሪያ መንገዷ ነበር፡፡ በተለይ ማዕቀቡ እና እገዳው በኳታር ላይ ከተጣለ ወዲህ የኳታር አየር መንገድ የሱማሊያን አየር ክልል በብዛት መጠቀሙ ሳዑዲን ማስኮረፉ የሚቀር አይመስልም፡፡ የኳታርን ጠቀም ያለ ድጎማ ለሚሻው የፕሬዝዳንት ፎርማጆ መንግስት ግን ከኳታር ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ የገንዘብ ድጋፉን ማጣት በቀላሉ የሚዋጥለት አይሆንም፡፡ ለዚህም ይመስላል ፈራ ተባ ሲል ቆይቶ ገለልተኛ አቋም መያዙን ያስታወቀው፡፡

በተለይ ሳዑዲ በኳታር ላይ እያስፈጸመች ያለቸው ሁለንተናዊ እገዳ በአፍሪካ ቀንድ የኳታርን እና ኢራንን መስፋፋት በማክሸፍ በቀጠናው ብቸኛ የሱኒ ዐርብ ሃያል ሀገር ሆና ለመውጣት መቁረጧን ጠቋሚ ነው፡፡ ለዚህም መሳካት የሳዑዲ መሪዎች ገንዘባቸውን በገፍ ከማፍሰስ ወደኋላ የሚሉ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በኳታር ላይ የቀረበው ሽብርተኛ ድርጅቶችን በገንዘብ የመርዳት ውንጀላ እና የተጣለባት ሁለንተናዊ ማዕቀብ የአንዳንድ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶችን ድጋፍ ማግኘቱ ደሞ ለሳዑዲ የልብ ልብ የሰጣት ይመስላል፡፡ ሳዑዲ የቀጠናውን ፖለቲካ የምትዘውር ብቸኛ የሱኒ ዐረብ ሃያል ሀገር ሆና መውጣቷ ግን ለኢትዮጵያ መልካም ዜና አይደለም፡፡

የዲፕሎማሲያዊ ቀውሱ ዳፋ በተለይ ወደኳታር እና ሳዑዲ በመመላለስ በሁለት ማንኪያ ለመብላት የሚፈልጉት የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂን ከባድ አጣብቂኝ ላይ እንደሚጥላቸው መገመት አያስቸግርም፡፡ ቀደም ሲል በተፅዕኖ ሳዑዲ-መራሹን የመን ጸረ-ሁቲ ዘመቻ እንዲደግፉ የተገደዱት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ድጋሚ አሁንም ከተመሳሳይ ተጽዕኖ ላያመልጡ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ፕሬዝዳንቱ ድጋሚ ያጎበድዱ ይሆን የሚለው ጥያቄ አጓጊ መሆኑ አልቀረም፡፡ የኤርትራው መሪ ግን ከኳታር ጋር ያላቸውን ጥብቅ ወዳጅነት አቋርጠው ለተዳከመው ኢኮኖሚያቸው መደጎሚያ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ ለማጣት ይወስናሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ከወዲሁ ታዛቢዎችን ማነጋገሩ አልቀረም፡፡ ኤርትራ ከኳታር የምታገኘው የድጋፍ ምንጭ ከቀረ ወይም ከቀነሰ ግን ኢትዮጵያን ጮቤ ማስረገጡ አይቀርም፡፡

ዞሮ ዞሮ ግን የኳታር መገለል ቀጥሎ በሂደቱም ለውጭ ሀገራት የምትረጨው የፋይናንስ አቅም ከተመናመነ ሱማሊያ እና ኤርትራ ምናልባትም ሱዳን በሳዑዲ ብቸኛ ተፅዕኖ ስር መውደቃቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ በተለይ በሱማሊያ ኳታር፣ ቱርክ እና ኢራን ጭራሽ ቦታ እንዳይኖራቸው ለማድረግ አልማ እየተንቀሳቀሰች ይመስላል፡፡ ሳዑዲ ለሱማሊያ ብቸኛዋ አለሁልሽ ባይ ከሆነች ደሞ ኢትዮጵያ በሱማሊያ የሚኖራትን ተሰሚነት መሸርሸሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሱማሊያን መልሶ በመገንባት ቁሳዊ ወይም የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ የማትችለዋ ኢትዮጵያ ለጊዜው ያላት መጫወቻ ካርድ በተናጥል ያዘመተችው ጦር ሠራዊቷ ብቻ መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ጥቅም የተሻለ የሚሆነው ሱማሊያ ላንድ ሃያል ዐረብ ሀገር ጥገኛ መሆኗ ሳይሆን ለተለያዩ ባላንጣ ዐረብ ወይም ሙስሊም ሃገራት መራኮቻ መሆኗ ነው፡፡

በሌላ በኩል ሲታይ የባህር በር ያላት ኳታር በምታራምደው የውጭ ፖሊሲዋ ሳቢያ የተጣለባት ሁሉን ዓቀፍ ማዕቀብ የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ እንደ ማስጠንቀቂያ ደወል ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ከኤርትራ እና ከግብጽ ጋር ያሏት ያልተቋጩ ውዝግቦች በተጨማሪ ወደፊት ሱማሊያ ስትረጋጋ ታሪካዊ ቁርሾዎች ካገረሹ የኢትዮጵያ ጅኦፖለቲካዊ አጣብቂኝ እየከፋ ሊሄድ እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡

ኢትዮጵያ እና ኳታር የጠበቀ የንግድ ትስስር ባይኖራቸውም በኳታር ላይ የተጣለው ሁለንተናዊ ማዕቀብ ግን በዚሁ ከቀጠለ በአቬሽን ንግድ ላይም አንድምታ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ገና ከወዲሁ በብዙ የመካከለኛው ምስራቅ ሰማይ እንዳይበር እገዳ የተጣለበት የኳታር ኤርዌይስ የገበያ ድርሻውን ሲያጣ ተጎጂ መሆኑ አይቀርምና፡፡ ይህም በመካከለኛው ምስራቅ ሰፊ የአቬሽን ገበያ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጥመው ፉክክር እንዲቀንስለት ስለሚያደርግ ዲፕሎማሲያዊ ቀውሱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰማይ እንደወረደ መና ሊቆጠር ይችላል፡፡

ከኤርትራ ጋር ያልተቋጨ የድንበር ውዝግብ፣ ከግብጽ ጋር ደሞ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሰጣ ገባ የገባችው የባህር በር አልባዋ ኢትዮጵያ መሪዎችም የኳታርን እና ሳዑዲ ዐረቢያን ደጅ ሲጠኑ መክረማቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ባሁኑ ቀውስ ግን ሳዑዲ ከኢትዮጵያ ብዙም የምትጠብው ርምጃ ያለ አይመስልም፡፡ ቀውሱ በሱማሊያ እና ኤርትራ ላይ በሚያሳርፈው ዳፋ ግን በተዘዋዋሪ መነካካቷ ላይቀር ይችላል፡፡