PM Abiy Ahmed and IMF director Kristalina Georgieva – FILE
  •  አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ 400 ሚሊየን ዶላር ድጎማ (Grant) ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል

ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት የኮሮና ወረርሽኝ እየፈጠረ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ሰራተኞች ከስራቸው እንዳይባረሩ ይረዳል ያለውን መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ወደተግባር ለመግባት እየተዘጋጀ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ሰምታለች። መርሀግብሩ ከሰሞኑ በይፋ ለህዝብ እንደሚገለፅም ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል።

ለውጭ ገበያ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች በተቀባይ ሀገራት ኮሮና ቫይረስ በፈጠረው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ኪሳራ ውስጥ ገብተዋል። የቫይረሱ ስርጭት ለቀጣይ ወራት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ተቀጣሪዎች ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉም መንግስትም መግለጽ ጀምሯል።ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለመደጎም የአበባ የወጪ ንግድ ላይ የተጣለ የዋጋ ገደብን ማንሳትን ጨምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይፋ አድርጎ ነበር። እንዲሁም ባንኮች ባበደሩት ገንዘብ 27 በመቶውን አስልተው እንዲገዙ ካደረገው የቦንድ ዋጋ ውስጥ 15 ቢሊየን ብሩን ከመመለሻ ቀነ ገደብ በፊት እንዲመለስላቸው አድርጓል።


ሆኖም የኮሮና ቫይረስ የሚያመጣው ተጽእኖ በቀላሉ የሚቆም አይደለም በሚል መነሻ መንግስት ተጨማሪ ድጎማዎችን ማሰቡን ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ተረድታለች።ይህም የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲን በማሰባጠር ተግባራዊ ለማድረግ ነው የታሰበው።

ከዚህ ውስጥ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ያለባቸውን ብድር በመክፈል ሂደት ውስጥ ጫና ውስጥ ገብተው ሰራተኞቻቸውን እንዳይቀንሱ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ እንዲደረግላቸው ፣ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ይደረጋል ተብሏል። የተወሰኑ ንግድ ባንኮች በጊዜ ገደብ ከተበዳሪዎቻቸው ወለድ እንደማይቀበሉ የገለጹ ሲሆን የአሁኑ እርምጃ ደግሞ ሁሉንም የንግድ ባንኮችን በማስማማት ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የብድር መክፈያ ጊዜ የማራዘምና የወለድ ምጣኔ ቅናሽ የማድረግ ስራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደሰማነው ከሆነም ተጨማሪ ብድር የማቅረብ ሀሳብም አለ። ይህ ለኢኮኖሚውም ድጎማ የተባለው ብድር እንዴትና በማን በኩል እንደሚቀርብም ግን በቅርቡ በመንግስት ይፋ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።

ቀጣሪ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾችም ያሉባቸው የተለያዩ የግብር ግዴታዎቻቸው እንደሚነሱላቸው ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። ይህም ቢያንስ የቫይረሱ ጫና ከመባባሱ በፊት ባገኙት ገቢ በየዘርፋቸው ቆይተው ሰራተኞቻቸውንም እንዳይቀንሱ ለመርዳት ይጠቅማል ተብሎ ታስቧል።ነገር ግን አብዛኞቹ የታሰቡት የኢኮኖሚ መደጎሚያ እቅዶች የኮሮና ቫይረስ ጫና ረዘም ላለ ጊዜ ከቆየ መፍትሄነቱ ብዙም አይሆንም የሚል ስጋት አለ ። ምክንያቱም የግብር ቅናሽና ብድር ኖሮም የተመረተ ምርት ገበያ የማያገኝ ከሆነ ኢንዱስትሪዎች ሰራተኞቻቸውን ማቆየት ሊሳናቸው ይችላል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ለተለያዩ ዘርፍ አንቀሳቃሽ ባለሀብቶች የሰራተኛ ደሞዝን እስከመጋራት ማሰብ አለበት ብለው ሀሳብ ያቀረቡ ባለሙያዎች አሉ።


ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) በኮሮና ቫይረስ የሚመጣባትን ጫና ለመቋቋም የሚያግዝ 400 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ድጎማ (Grant) ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ከኮሮና ጋር በተያያዘ ይደርሳት የነበረው ኮታ 200 ሚሊየን ዶላር የነበረ ቢሆንም የገንዘብ ተቋሙ በኮቪድ19 ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ችግር ውስጥ ለገቡ ሀገራት መታደጊያ እንዲሆን መድቦት የነበረውን ገንዘብ በመጨመሩ የኢትዮጵያም ኮታ ወደ 400 ሚሊየን ዶላር ከፍ ይላል ተብሏል።

አይ ኤም ኤፍ ከቀናት በፊት ለበርካታ ሀገራት የብድር ማቃለያ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ውስጥ አለመካተቷ ብዙዎችን ያነጋገረ ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ ቀድሞ ተደርገው በነበሩ ድርድሮች ጭምር በየአመቱ የምትከፍለው ብድር በአንጻሩ ቀለል እንዲል በመደረጉ ከ25 ጫና ከበዛባቸው ሀገራት የእዳ ማቃለያ መርሀ ግብር ውስጥ እንዳልገባች መረዳት ችለናል። አሁን ከገንዘብ ተቋሙ የሚጠበቀው 400 ሚሊየን ዶላርም በቅርቡ ይለቀቃል ተብሏል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከአለም ባንክ ከ82 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ ገንዘብን ከኮሮና ቫይረስ ተጽእኖ ኢኮኖሚዋን መታደጊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]

To reach the editors – wazemaradio@gmail.com