Kiflu Tadesse latest book cover page
Kiflu Tadesse latest book cover page

በኢህአፓ ዙሪያ በሚያጠነጥኑት እና “ያ ትውልድ” በሚል ስያሜ በታተሙት ሶስት መጽሐፍቱ የሚታወቀው ክፍሉ ታደሰ አዲስ መጽሐፍ ትላንት (ሀሞስ)  ለንባብ አበቃ፡፡

“ኢትዮጵያ ሆይ…” የሚል ርዕስ የተሰጠው የክፍሉ አዲስ መጽሐፍ ፖለቲካን ከታሪክ ጋር ቀይጦ “የትውልድ እና የሀገርን ውጣ ውረድ” ይዳስሳል፡፡ መጽሐፉ ተከታይ ቅጽ

የሚኖረው ሲሆን አሁን ለገበያ የበቃው የመጀመሪያው ቅጽ “በትግሉ ዘመን በተነሱ ጥያቄዎችና ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ምን አንድምታ እንዳላቸው የሚያሳይ” መሆኑን ደራሲው በ’መግቢያ’ው ላይ አስቀምጧል፡፡

ከኢህአፓ መስራቾች አንዱ የነበረው ክፍሉ ከባለ416 ገጽ መጽሐፉ ውስጥ አብዛኛውን የሰጠው ለደርግ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ በአስራ ሁለት ምዕራፎች በተከፋፋፈለው መጽሐፉ ስለ “ደርግና የወታደሩ የውስጥ ትግል” በሁለት ወቅቶች ከፋፍሎ ያስነብባል፡፡ የደርግን የውስጥ ልዩነት እና ደርግ ከሰራተኞች ጋር ስለነበረው ቁርቋሶ በሁለት ምዕራፎች ይተነትናል፡፡

በመኢሶን ይዘወር እንደነበር ስለሚነገርለት “የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽህፈት ቤት”ም በሁለት ምዕራፎች ውስጥ ዳሰሳ ያቀርባል፡፡ የግራ ፖለቲካ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ከነበሩት ውስጥ “መሬት” እና “የሴቶች ጥያቄን” በመጽሐፉ ውስጥ አጽንኦት ሰጥቶ በስፋት አንስቷል፡፡ ለሁለቱም ጉዳዮች ሙሉ ምዕራፍ መድቦ በወታደራዊው አገዛዝ ጊዜ የነበረውን እውነታ ቃኝቷል፡፡

ለለውጥ መንስኤ ስለነበረው የአጼ ኃይለ ስላሴ አስተዳዳር ሁኔታም እንደዚሁ በሁለት ምዕራፎች ውስጥ የነካካቸው ጭብጦች አሉ፡፡ ወደ ኋለኛው ታሪክ ተመልሶ የአክሱም እና የምኒልክን ጊዜ ከኢትዮጵያነት ጋር ያላቸውን መቆራኘት በጨረፍታ ሊፈትሽ ይሞክራል፡፡በአብዛኛዎቹ የመጽሐፉ ክፍሎች እዚህም እዚያም የሚያነሳው ግን በተከታታይ ቅጾች ብዙ ስለተረከለት የኢህአፓ ጉዳይ ነው፡፡

ደራሲው በኢህአፓ ውስጥ የነበረው ከፍተኛ ሚና ፣ ከለጋነቱ ጀምሮ መሳተፍ የጀመረበት “የለውጥ እንቅስቃሴ” እና አብረውት ከታገሉት መካከል የብዙዎቹ በህይወት አለመኖር ታሪኩን የመተረክ ኃላፊነት እንዳሸከመው በመጽሐፉ “መቅድም” ይገልጻል፡፡

“ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደው ትግልም ሆነ የኢህአፓ ታሪክ ዛሬ እንደ አዲስ ሆኖ በመውጣቱ የብዙ ሰውን ቀልብ ከመሳቡም በላይ መነጋጋሪያ ሆኗል” ሲል በመቅድሙ መክፈቻ ላይ ጽፏል፡፡ “የ ‘ያ ትውልድ’ መድብሎችን ከደረስኩ ጊዜ ጀምሮ ባላሰብኩትና ባልጠበቅሁት ሁኔታ ከበድ ያለ ኃላፊነት ትከሻዬ ላይ ወደቀ” በማለት ከጸሀፊነቱ ጀርባ ያለውን ምክንያት ያስረዳል፡፡

Kiflu Tadesse former senior leader of  EPRP
Kiflu Tadesse former senior leader of EPRP

አራት መጽሐፍትን አንባቢያን ዘንድ ያደረሰው ክፍሉ ሌላ መጽሐፍ ለመጻፍ በመዘጋጀት ላይ እያለ “ሁኔታዎች ሲቀያየሩ” እቅዱን በይደር አቆይቶ እዚህኛው መጽሐፍ ላይ እንዲያተኩር መገደዱን ይገልጻል፡፡ “የአብዮታዊው ትውልድ ታዋቂ መሪዎች” ሲል የሚጠራቸው ጓዶቹ በህይወት ቆይተው ገድላቸውን ባለመጻፋቸው “የቀጣፊዎች የብዕር ሰለባ” መሆናቸውን በቁጭት የሚያስታውሰው ክፍሉ ታሪክ የማስተካከሉ ግዳጅ የወደቀው በእርሱ መሳይ ከሞት እና ከእስር የተረፉ “ቋሚዎች” ላይ እንደሆነ ያብራራል፡፡

የ”ያ ትውልድ” ተከታታይ መጽሐፍት ለንባብ ከበቁ በኋላ የተለያዩ መጽሐፍት እና መረጃዎች መውጣታቸውን የሚናገረው ክፍሉ እነርሱን እና ሌሎች ማጣቀሻዎችን በመጠቀም “ኢትዮጵያ ሆይ…”ን መጻፉን ይገልጻል፡፡ ተገኙ ከተባሉ መረጃዎች መካከል የኢህአፓ መስራች የነበረው ብርሃነ መስቀል ረዳ ያዘጋጀው ሰነድ ይገኝበታል፡፡

“ብርሃነ መስቀል ሰፊ ጽሁፍ አዘጋጅቶ ለደርግ እንደሰጠ ከብዙ ዓመታት በፊት በመወራቱ፣ ሰነዱ መኖሩ ይታወቅ ነበር” የሚለው ክፍሉ ሰነዱን ሰው እንደላከለትና እጁ እንደገባ ይገልጻል፡፡ “ሰነዱን አነበብኩት፡፡ የተነሱ ብዙ ጉዳዮች አስደመሙኝ” ሲል ሌሎች ጓዶቹ በህይወት ኑረው ‘ምነው ባነበቡት’ ብሎ መመኘቱን ይተርካል፡፡

የብርሃነ መስቀልን ጨምሮ በሌሎች አዳዲስ መረጃዎች ላይ የተመረኮዘው መጽሐፉ ከዚህ በፊት ያልተዳሰሱ ጉዳዮችን መዳሰሱን፣ በልዩነት ለቀረቡ መረጃዎች ምላሽ መስጠቱን እና በሌሎቹ መጽሐፍቱ ማንነታቸውን የደበቀላቸውን ግለሰቦች ይፋ ማውጣቱን ይናገራል፡፡ ከዚህ በፊት ያልታተሙ ፎቶዎችም የመጽሐፉ አካል ናቸው፡፡

“የአጻጻፍ ስልቱን በተመለከተ ታሪክ፣ ግምገማ፣ ትንተና… ወዘተ ላይ ብቻ የተመሰረተ በማድረግ ፈንታ ተሞክሮዎችን፣ ልምዶችን እና ገጠመኞችን በማካተት ሰብዓዊ ገጽታ በማላበስ የአንባቢያንን ቀልብ ለመሳብ ሞክሬያለሁ” ይላል ክፍሉ፡፡

ስለ ትግሉ የግል አስተያያቱን እና ግምገማውን በመጽሐፉ ውስጥ ያካተተው ክፍሉ “ያ ትውልድ” በዘመነኛው ትውልድ እንዴት አንደሚታይ እና እርሱ እንዴት እንደሚመለከተው እንዲህ ጽፏል፡፡

“የዛሬው ትውልድ፣ ከእሱ በፊት የነበርነውን ‘እኛን ችግር አውርሰውን ሄዱ’ ቢል ሊገርምን አይችልም” የሚለው ክፍሉ “እኛ ጊዜአችንን እየጨረስን ነው፡፡ ለመጪው ትውልድ ልናወርሳቸው የምንችላቸው ጥቂት ነገሮች ቀርተውናል፡፡ ታሪካችንና የመንፈስ ጽናታችንን!” ሲል አሁን ላለው ትውልድ ከ “ያ ትውልድ” ሊቀስም የሚችለውን ትምህርት ያስቀምጣል፡፡