ዋዜማ-  በኢትዮጵያ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አዲስ አበባ የሚገኙት የባንኮቹ ዋና መስሪያ ቤቶች ከክልል ቅርንጫፎቻቸው ጥሬ ገንዘብ ለማምጣት መቸገራቸውን ዋዜማ ራዲዮ ከተለያዪ ምንጮቿ መረዳት ችላለች።

በተለይም አዲስ አበባ ያሉት የተለያዩ ባንኮች ከቅርብ ወራት ወዲኽ የገቡበት ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አንዱ ምክንያት ይኸው በክልሎች ካሏቸው ቅርንጫፎች  ጥሬ ገንዘብ ማምጣት ባለመቻላቸው እንደሆነ ዋዜማ ተረድታለች።

ከምንጮቻችን እንደተረዳነው ከሆነ፣ በኦሮምያ ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ያሉ  ቅርንጫፎች በጸጥታ ችግር ሳቢያ ከሚሰበስቡት ቁጠባ ውስጥ ራሳቸው ጋር አስቀርተው ወደ ማዕከል መላክ እያቃታቸው ነው። ይህም የሆነውም ቅርንጫፎቹ ገንዘቡን ሲያጓጉዙ ከጸጥታ አካላት በቂ እጀባ እያገኙ ባለመሆኑ እንደሆነ ስማቸውን መጥቀስ ካልፈለጉ የተለያዩ የባንክ አመራሮች ሰምተናል። 

ጥሬ ገንዘብ በአየር ትራንስፖርት መጓጓዝ ቢኖርበት እንኳን ከባንክ ቅርንጫፍ ወደ አውሮፕላን እና ከአውሮፕላን ወርዶ ደግሞ የሚፈለገው ቦታ እስኪደርስ ድረስ በቂ የጸጥታ አካላት እጀባ መገኘት አለመቻሉንም ተረድተናል። በዚህም ሳቢያ በክልሎች ያሉ ቅርንጫፎች መያዝ ካለባቸው ገንዘብ በላይ ይዘው ለመቆየት እየተገደዱ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው ሰምተናል። 

ባንኮች ለሰው ሰራሽም ሆነ ለተፈጥሮ አደጋ የሚሆን ዋስትና የሚገቡት በቅርንጫፎቻቸው ማደር የሚገባውን የብር መጠን ከወሰኑ በኋላ እንደመሆኑ ከወሰኑት በላይ ባለው የገንዘብ መጠን ላይ ለሚደርስ ማንኛውም አደጋ ምንም ዓይነት የመድኅን ሽፋን አያገኙም። 

ከዚኽ አንፃርም የተለያዩ ባንኮች በ’የቅርንጫፎቻቸው እንዲቀመጥ የሚወስኑት የገንዘብ መጠን ከ1.5 እስከ 4 ሚሊየን ብር እንደሚደርስ ምንጮቻችን ይጠቅሳሉ። ይኽም ኾኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲኽ በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች ያሉ ባንኮች የተጋነነ ጥሬ ገንዘብ በካዝናቸው ውስጥ ለማቆየት መገደዳቸውን ዋዜማ መረዳት ችላለች።

በአንዳንድ የክልል ከተሞች ቅርንጫፎች ከ30 እስከ 40 ሚሊየን ብር ተከማችቶ ለረጅም ቀናት እንደቆየም ሰምተናል። ለዚኽም ቅርንጫፎቹ ያከማቹትን ጥሬ ገንዘብ ወደ ማዕከሎቻቸው ለመላክ በቂ ጥበቃ ማጣታቸው እንደኾነም ተሰምቷል። ምንጮች እንደነገሩን ጥበቃ ያጡበትን ምክንያት ከጸጥታ ተቋማቱ ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት አዳጋች ኾኖባቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ባንኮች ያለው የጥሬ ገንዘብ እጥረት መቀጠሉን ታዝበናል። በ10 ሺዎች የሚቆጠር ብር ማውጣት ፣ እንዲኹም ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ መላክ አዳጋች ሆኖ ቀጥሏል።

ያነጋገርናቸው የተለያዩ የባንክ ቅርንጫፎች ስራ አስኪያጆች እንደነገሩን  በፊት በየሁለት ቀኑ ከ2 እስከ 3 ሚሊየን ብር ከየማዕከሎቻቸው ሲላክላቸው ከቅርብ ወራት ወዲኽ ግን የሚላክላቸው ከ200 ሺ ከፍ ያላለ ኾኗል። ይህ የገንዘብ መጠንም አንድ ከፋይ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ  ከፍሎ የሚጨርሰው እንደመኾኑ የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ ከደንበኞቻቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ እየጨመራቸው መሆኑንም ነግረውናል።

ይህን መሰል ችግር ውስጥ የገቡት በዋና ከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ባንኮችም የተሻለ የጥሬ ገንዘብ ክምችት ካላቸው ሌሎች ባንኮች እና ከብሄራዊ ባንኩ ብድር መውሰድን  ወቅታዊ መፍትሔ ለማድረግ መገደዳቸውንም ለመረዳት ችለናል። [ዋዜማ]

If you wish to contact Wazema editorial team please write to wazemaradio@gmail.com