Ogaden crude oil inauguration at the presence of PM Abiy Ahmed
Ogaden crude oil inauguration

ዋዜማ ራዲዮ- የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር በሶማሌ ክልል የተጀመረውን ነዳጅ የማውጣት ፕሮጀክት እንደሚቃወምና የኦጋዴን የራስን ዕድል በራስ መወሰን ሳይረጋገጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ህገ ወጥ ዝርፊያ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታወቀ።
የኦጋዴን የነዳጅ ጉድጓድ ተመርቆ የሙከራ ስራ በተጀመረ በሰዓታት ውስጥ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክቶቹ የክልሉን ህዝብ ጭቆናና የመብት ጥሰት ሊጋርዱት አይገባም ብሏል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ የክልሉ የፖለቲካ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አለበለዚያ ግን ተግባራዊ መደረጉን አጥብቆ እንደሚቃወም ተናግሯል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የጀመሩት የፖለቲካ ተሀድሶን በበጎ እንደሚመለከት የገለፀው ድርጅቱ የኦጋዴን የራስን ዕድር በራስ መወሰን መብት እንዲከበር ከዚያም በኦጋዴንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በሚኖር ስምምነት ብቻ የተፈጥሮ ሀብቱን በፍትሐዊነት መጠቀም ተገቢ ነው ብሎ ያምናል።
ከ 11 ዓመታት በፊት የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር በቻይና የነዳጅ ፍለጋ ስራተኞች ላይ ባደረሰው ጥቃት 63 ኢትዮጵያውያንና 9 ቻይናውያን መገደላቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው ሚሊሻ በማደራጀትና ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍቶ ነበር። በድርጊቱም ስፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙ በተደጋጋሚ ተነግሯል።