ዋዜማ- በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች ተገድቦ የነበረው የኤርትራ መገበያያ ገንዘብ ናቅፋ ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር ተያይዞ ወደ ሌሎች ከተሞችም በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን ዋዜማ ከነዋሪዎችና በንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ ግለሰቦች ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።
የኤርትራ ናቅፋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እሰከ አዲግራት እና አደዋ ከተሞች ድረስ እየተሰራጨ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ናቅፋ በትግራይ ከተሞች እንዲሰራጭ ያደረገው በድንበር ከተሞች እና በውስን ተዋንያን ተገድቦ የነበረው የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋቱን ተከትሎ ነው፡፡
በኤርትራና በትግራይ መካከል ያለው ድንበር ተከፍቶ የኮንትሮባንድ ንግድ እያደገ ሲመጣ በውስን ነጋዴዎች እጅ የነበረው ናቅፋ አሁን ወደ ትናንሽ ነጋዴዎች እጅ መድረሱን በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ነገረውናል።
የናቅፋ መስፋፋት በተወሰነ መልኩ በትግራይ ከሚታየው የብር አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ እንደሆነ በባንክ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በትግራይ ባለው የፀጥታ ስጋት ምክንያት በርካታ ሰዎች ጥሬ ገንዘብ ከባንክ አውጥተው በቤታቸው መያዝ መጀመራቸው የብር አቅርቦት እጥረት ማስከተሉን የባንክ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በድንበር አካባቢ ያለው ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና ከሁለቱም ወገን አዳዲስ ነጋዴዎች፣ ደላሎችና የኮንትሮባንድ አንቀሳቃሾች በስፋት እየተሳተፉበት መሆኑን ከነዋሪዎች ሰምተናል።
በዚሁ የድንበር ንግድ ላይ የተሰማራ አንድ የትግራይ ባለሀብት እንደነገረን እንደ ሳሙና፣ ዘይትና ኤሌክትሮኒክስ የመሳሰሉ ፍጆታዎችን ከአዲስ አበባ ከሚገዛበት ዋጋ ባነሰ በድንበር በኩል ስለሚመጣ ፍጆታውን ወደ አቅራቢያ ከተሞች ወስዶ በተሻለ ትርፍ ለመሽጥ መቻሉን ያብራራል።
ከትግራይ ወደ ኤርትራ ድንበር የሚሻገሩት በአመዛኙ እንደ ነዳጅ፣ የእህል ምርቶች፣ የቁም እንሰሳት እና ሸቀጣ ሸቀጦች ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች በድንበር አካባቢዎች በከፍተኛ ዋጋ ስለሚሸጡ ወጣቶች በአነስተኛ መጠን ጭምር፣ በድንበር ከተሞች ለኤርትራ ገበያ ያቀርባሉ፡፡
መደበኛ ባይሆንም አነስተኛ መጠን ያለው የወርቅ ምርት ድንበር ላይ ለኤርትራ ነጋዴዎች እንደሚቀርብ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የኤርትራ ነጋዴዎች ወርቅ ሲቀርብላቸው አልፎ አልፎ ከናቅፋ በተጨማሪ፣ በዶላር ጭምር የሚከፍሉም ተገልጧል፡፡
መቀሌን ጨምሮ በትግራይ ከተሞች ነዳጅ በየመስመሩ መሸጥ የተለመደ መሆኑን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በየአካባቢው የሚለያይ ቢሆንም አሁኑ ወቅት የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ በመቀሌ ከተሞች እሰከ 220 ብር ድረስ ሲሆን፣ በኤርትራ ድንበር አካባቢዎች ከ300 ብር በላይ መሻገሩን ስምተናል፡፡
ከትግራይ ወደ ድንበር የኤርትራ ከተሞች ለጥቃቅን ንግዶች የሚያቀኑ ወጣቶች ለኤርትራ ገበያ የሚያቀርቡትን ምርት የሚሸጡት በናቅፋ ሲሆን፣ ወደ ትግራይ ተመልሰው በጥቁር ገበያ እንደሚመነዝሩ ዋዜማ ተረድታለች፡፡
በጥሬ ገንዘብ ላይ በተመሰረተው የድንበር አካባቢ ንግድ ወደ ትግራይ የሚገባው የኤርትራ ናቅፋ በትይዩ ገበያ ወደ ብር ይቀየራል፡፡ የናቅፋ እና ብር ልውውጡን የሚያሳልጡ ደላሎች እስከ ትግራይ መዲና መቀሌ ከተማ ድረስ መኖራቸው ተመላክቷል፡፡
እንደ አዲግራት ባሉ የድንበር አቅራቢያ ከተሞች አንድ የኤርትራ ናቅፋ በኢትዮጵያ እሰከ ከ12 እሰከ 15 ብር ድረስ እየተለወጠ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ የኤርትራ ናቅፋ ይፋ ዋጋ የሚወጣለት ባይሆንም፣ መደበኛ ዋጋው አንድ ናቅፋ ሰባት ብር መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የድንበር ንግድ በስፋት የሚካሄድባቸው ከተሞች እንደ ባድመ፣ ራማ፣ ጾረና፣ ዛላምበሳ ያሉ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በድንበር ላይ የተሰማሩ የኤርትራ እና የትግራይ የጸጥታ አካላት ነጋዴዎችን የማለፊያ ገንዘብ ቢጠይቁም እንቅስቃሴ ግን አይከለክሉም ተብሏል፡፡ የኤርትራ ወታደሮች አልፎ አልፎ ከትግራይ ነጋዴዎች ላይ በግዳጅ ገንዘብ እንደሚቀሙና ድብደባ ጭምር እንደሚፈጽሙ ስምተናል።
በጉዳዩ ላይ የአድዋና የአዲግራት ከተማ ከንቲባዎችን አስተያየት እንዲሰጡ ብንጠይቃቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። [ዋዜማ]
