እስካሁን ስምንት ቢሊየን ብር ወጪ አድርጓል

 ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመስሪያ ቦታ ተከራይተው ለሚሰሩ አምራቾች በሊዝ ፋይናንስ አሰራር የማሽን ብድር ወይንም የኪራይ  አገልግሎቱን ለማቆም መወሰኑን ዋዜማ ራዲዮ ከባንኩ ምንጮቿ ሰምታለች። 


     ባንኩ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ነበር ለአነስተኛና  መካከለኛ   ኢንተርፕራይዞች  የካፒታል ዕቃዎች   ኪራይ   /የሊዝ   ፋይናንስ/   አገልግሎት መስጠት የጀመረው።የካፒታል እቃዎች ኪራይ ወይንም ብድር የመጀመሩ አላማም ብዙ ሰው ቀጥረው የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ነገር ግን በመደበኛ ባንክ መያዣ አስይዘው መበደር የማይችሉ ግለሰቦችን ለመድረስ ታስቦ ነው።ልማት ባንኩ በዚህ ብድር አሰራሩ እስካሁን ስምንት ቢሊየን ብር ወጪ አድርጓል።


   ሆኖም አሁን ላይ ቦታ ተከራተው ለሚሰሩ ሰዎች ወይም ማህበራት የሊዝ ማሽን ኪራይና ብድር ለማቆም መወሰኑ ነው የተሰማው።


 ለዚህ ውሳኔው ባንኩ ያቀረበው ምክንያት  በሊዝ ፋይናንስ ማሽን የወሰዱ ደንበኞች የመስሪያ ቦታ ኪራይ መክፈል ሲያቅታቸው ባንኩ በኪራይ ያቀረበላቸውን ማሽን እንደ መያዣ ሲጠቀሙ በመታየቱ ነው። በዚህም ምክንያት ልማት ባንኩ በገዛቸው ማሽኖች ላይ ለኪሳራ በሚዳርግ መልኩ ከሶስተኛ ወገን ጋር የህግ ክርክር ውስጥ ለመግባት መገደዱንም ነው የሰማነው።ይህም ባንኩን ለኪሳራ እየዳረገው በመሆኑ በቦታ ኪራይ ስራ ለሚሰሩ የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ላለመስጠት ከውሳኔ ላይ ደርሷል።


ከዚህ ባሻገር በባንኩ በሊዝ ፋይናንስ ከሚቀርቡ ማሽኖች ውስጥ ውስብስብና ለመትከል አስቸጋሪ የሆኑ ማሽኖች በመኖራቸው ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ቢፈለግም ከቦታ ቦታ በቀላሉ ማንቀሳቀስ የማይቻል መሆኑ ችግር እየፈጠረ መምጣቱም በምክንያትነት ተነስቷል። 


ነገር ግን በአዲስ አበባ የባንኩ የካፒታል ዕቃዎችን ኪራይ ተጠቃሚ ደንበኛ በመሆን እየተንቀሳቀሰሱ ከሚገኙ አምራቾች ውስጥ እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት በኪራይ ቦታ የሚሰሩ በመሆናቸው አዲሱ የባንኩ አሰራር ዘርፉን  በእጅጉ ሊጎዳው እንደሚችል ይገመታል።


የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛ እና መካከለኛ  ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃዎችን ገዝቶ  በዱቤ  ግዥ  ሥርዓት ለኪራይ የሚያቀርብላቸው ዘርፎች በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፣ የመፈብረኪያ ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ፣ የማዕድን እና ቁፋሮ ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ሆነው ከስድስት በላይ ሰራተኞችን የያዙ ወይም የሚቀጥሩ እንዲሁም አጠቃላይ ካፒታላቸው ከብር 500 ሺህ እስከ ብር 7.5 ሚሊዮን የሆኑ አንቀሳቃሾችን ስለመሆኑም በመመሪያው ላይ አስቀምጧል። [ዋዜማ ራዲዮ]