ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ከሀላፊነታቸው ሊነሱ ነው።የኢንጂነር አዜብ መነሳት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የልማት ተቋማትን የማሻሻል አንዱ አቅጣጫ መሆኑ ተጠቅሷል። በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ በኩል ውሳኔው መተላለፉን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን ነግረውናል። ሌሎች የመንግስት ድርጅቶች ሐላፊዎችንም ለመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ስምተናል።

Azeb Asnake
Azeb Asnake

ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፈጻሚነት ከመምጣታቸው በፊት የግልገል ጊቤ ሶስት የውሀ ኤሌክትሪክ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ነበሩ። 10 አመት የወሰደውና 1.5 ቢለዮን ዪሮ ወጭ ሲገነባ የነበረው የግልገል ጊቤ ሶስት የሀይል ማመንጫ ብዙ የግንባታ ሂደት ሳይጠናቀቅ ነበር የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን የኤሌክትሪክ ሀይልና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተብሎ ለሁለት ሲከፈል የሀይሉን ዘርፍ በዋና ስራ አስፈጻሚነት የያዙት።

ኢንጂነር አዜብ ወደዚህ ሀላፊነት ከመጡ ወዲህ ራሳቸው በስራ አስኪያጅነት ሲመሩት ከነበረው ጊልገል ጊቤ ቁጥር ሶስትና ከአዳማ ቁጥር 2 የንፋስ ሀይል ማመንጫ ውጭ ወደ ስራ የገባ ፕሮጀክት የለም።ኢንጂነር አዜብ በ2006አ ም ወደ ኤሌክትሪክ ሀይል ስራ አስፈጻሚነት የመጡት በወቅቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ግፊት እንደሆነ ይነገራል።

እሳቸው ወደዚህ ሀላፊነት ከመጡም በሁዋላ በሀይል አቅርቦት ይህ ነው የተባለ ለውጥ በሀገሪቱ አልመጣም። ይልቁንም በኢትዮጵያ በሀይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ትልልቅ ተቋማት ለመስራት የተቸገሩበት እና ተገንብተውም ወደ ስራ መግባት ያልቻሉበት ሁኔታ ጎልቶ ታይቷል።

በሌላ በኩል በኢንጂነር አዜብ የአመራር ብቃት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ጥቂት አይደሉም ።ይህም ብቻ ሳይሆን ተቋሙን ከህወሀት ተጽእኖ ማላቀቅ እንዳልቻሉ ይነገራል።እዚህ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ የሚተኛበት 180 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ላይ ደን እንዲመነጠር ኢንጂነር አዜብ ከሚመሩት ተቋም የህውሀት ጄኔራሎች የሚመሩት የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ያለምንም ጨረታ ውል ያገኘበት ሁኔታ እስካሁን አጠራጣሪ ነው። አስገራሚው ነገር ሜቴክ የምንጣሮውን ገንዘብ ከተቋሙ ከተቀበለ በሁዋላ ስራውን በኮንትራት ለቀድሞ ታጋይ ቤተሠቦች ይሠጠዋል።እነዚህ ታጋዮች ደግሞ ውሉን ለወጣቶች ሰጥተው በዚህ መሀል ከሜቴክ ተወስዶ ታች ድረስ በወረደው ገንዘብና በተከፈለው ገንዘብ መሀልና በተመነጠረ ደን መሀል ልዩነት መጥቶ ገንዘብም ባክኖ ደኑም በቅጡ ሳይመነጠር እስካሁን አለ። የጉዳዩን ዝርዝር እዚህ ሊያነቡት ይችላሉhttps://goo.gl/6cnCqB

የግድቡን የሲቪል ስራ የሚሠራው የጣልያኑ ሳሊኒ  በክፍያ እጥረት ምክንያት ስራውን መስራት አቅቶት እንደነበር ተናግሮ ነበር።በሌላ በኩል አስተማማኝ ያልሆኑና ሜቴክ አምርቻቸዋለሁ ያላቸውን ትራንስፎርመሮችን እንዲገዛ ሜቴክ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ላይ ተጽእኖ ይፈጥር ነበር።

ባለፉት ወራት ዋና ዋና በሚባሉ የድርጅቱ ክንውኖችም ሆነ ከፍተኛ የሀይል ማመንጫ ብልሽት በተከሰተበት ወቅት ሀላፊዋ ወደ ሕዝብ ዕይታ ብቅ አላሉም።