ዋዜማ – የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር ውስጥና የውጪ አጠቃላይ ብድር ከሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን የገንዘብ ሚኒስቴር በየሶስት ወሩ የሚያወጣው የሀገሪቱን የብድር ሁኔታ የሚያትተው ሰነድ አመለከተ። 

አጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ብድር በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2022 ላይ 57.3 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን ፣ ይኸው ቁጥር መጋቢት 2023 ላይ 60.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይሄም በመቶኛ ሲገለጽ የሀገሪቱ አጠቃላይ ብድር የስድስት በመቶ ጭማሬን አሳይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለተነሱላቸው ጥያቄዎችን ምላሽ ሲሰጡ የኢትዮጵያ ብድር ከሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት አንጻር ከነበረው የ59 በመቶ ድርሻ ወደ 38 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናርግረው ነበር።

ሆኖም የብድር ምጣኔው ከሀገራዊ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ ይውረድ እንጂ የብድሩ መጠን ግን በራሱ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። 

ለብድር መጠኑ መጨመር የውጭውም የሀገሪቱም የብድር መጠን ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ ማብራሪያ አመልክቷል።

የውጭ ብድር እ.አ.አ ሰኔ 30 2022 ከነበረበት 27.9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እ.አ.አ መጋቢት 2023 ወደ 28.1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አድጓል። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል።አንዱ የአሜሪካ ዶላር የምንዛሬ አቅም ተለዋዋጭ ሆኖ በአንጻሩ ደግሞ ላለፉት ወራት ከሌሎች ሀገራት ምንዛሬዎች አንጻር በትንሹም ቢሆን ደከም ብሎ መታየቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

ሌላው የኢትዮጵያን የውጭ ብድር ከፍ እንዲል ያደረገው በተጠቀሱት ዘጠኝ ወራት ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ብድር  ፣ ወለድን ሳይጨምር ከተከፈለው ዋና ብድር ከፍ ብሎ በመታየቱ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር ጠቅሷል።

ካለፈው አመት ሀምሌ ወር መጀመርያ አንስቶ እስከዚህ አመት መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ የአለም አቀፍ የልማት ድጋፍ ብዙ ድርሻ ያለበት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ብድር የገባ ሲሆን፣ ወለድን ሳይጨምር የተከፈለው ዋና ብድር ግን 948 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ነው። 

የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ከሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ 13 በመቶ እንደሆነ ተጠቅሷል። ከሀገራዊ ምርት አንጻር የውጭ ብድር ምጣኔው ኢትዮጵያን አስጊ ጫና ካለባቸው ሀገራት ተርታ ያስወጣት ቢሆንም የዕዳ ከፋይነት ዋና መለኪያ በሆነው መመዘኛ ግን ሀገሪቱ አሁንም ችግር ውስጥ ነች። 

የዕዳ ከፋይነት አቅም መለኪያ የሆነው የሸቀጦች እና አገልግሎቶች የወጪ ንግድ ገቢ ከሀገሪቱ እዳ አንጻር ያለው ምጣኔ ሲሆን ፣ በዚህ እይታ ሲቃኝ አሁንም የኢትዮጵያ የዕዳ ከፋይነትም ሆነ ተሸካሚነት አቅም አሁንም ችግር ውስጥ ያለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ለዋዜማ እንደገጹት “ኢትዮጵያ አለባት የሚባለው የውጭ ብድር ብዙ የሚባል አይደለም ፣ ችግሩ ያለው ሀገሪቱ ምርትና አገልግሎቶችን ለውጭ ገበያ አቅርባ በውጭ ምንዛሬ ያለባትን ዕዳ  የመክፈል አቅሟ ደካማ መሆኑ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ባለፈው አመት ሀገሪቱ ክብረ ወሰን በተባለ ደረጃ ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ አግኝታለች። በዚህ አመት የሚኖረው የሸቀጦች የወጪ ንግድ ያሉ አመላካቾች ግን ገቢው ከአምና ዝቅ እንደሚል ያሳያሉ። እነዚህ ምክንያቶች የሀገሪቱን የብድር መክፈል አቅም ያዳክሙታል።

ሌላው ለኢትዮጵያ መንግስት ብድር መጨመር አስተዋጽኦ ያደረገው የሀገር ውስጥ ብድር ሲሆን ፣ ይህም ባለፈው ሀምሌ ወር ላይ 1.5 ትሪሊየን ብር የነበረው የመንግስት የሀገር ውስጥ ብድር በዚህ አመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የ14 በመቶ እድገት አሳይቶ 1.7 ትሪሊየን ብር ደርሷል። [ዋዜማ ]