- ትርፉ ቅናሽ አሳይቷል፤ ባንኩ አዲስ የምክትል ፕሬዝዳንቶች ሽግሽግም አድርጓል
ዋዜማ- በኢትዮጵያ መንግስት ባለቤትነት የተያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰጠው አጠቃላይ ብድር ከአንድ ትሪሊየን ብር ማለፉን ዋዜማ ከባንኩ ምንጮቿ ሰምታለች።
ባንኩ በተጠናቀቀው የ2015 አ.ም የበጀት ዓመት ብቻ የሰጠው አዲስ ብድር 151 ቢሊየን ብር ሲሆን ፣ ይህም ባንኩ በጥቅሉ የሰጠውን ብድር 1.05 ትሪሊየን ብር አድርሶታል።
ባንኩ በዚህ አመት ያበደረው ገንዘብ ብቻው በአጠቃላይ የሀገሪቱ ባንኮች በአመቱ የሰጡትን ብድር ከ32 በመቶ በላይ ድርሻ ይይዛል። በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክም አንድ ትሪሊየን ብርን የተሻገረ ብድርን የሰጠ አንድ ብቸኛ ባንክ ሆኗል።
ባለፈው አመት የባንኩ አጠቃላይ ቁጠባ አንድ ትሪሊየን ብር ደርሶ ነበር። በዚህ አመት ደግሞ የሰጠው አጠቃላይ ብድርም አንድ ትሪሊየን ብርን ተሻግሯል።
ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2015 አ.ም በጀት አመት ውስጥ ንግድ ባንኩ ተጨማሪ 165.3 ቢሊየን ብር ቁጠባ እንደሰበሰበም ሰምተናል። ንግድ ባንክ ያለው ቁጠባ ሌሎች የኢትዮጵያ ባንኮች ተደምረው ካላቸው የቁጠባ መጠን ብቻውን 50 በመቶውን ገደማ ይዟል። የኢትዮጵያ ባንኮች ያላቸው አጠቃላይ ቁጠባ 2.1 ትሪሊየን ብር ነው።
የባንኩ የ2015 አ.ም ትርፍ ከታክስ በፊት 20.6 ቢሊየን ብር ሲሆን ፣ ትርፉ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር አንድ ቢሊየን የሚጠጋ ቅናሽን አሳይቷል። የትርፉ ቅናሽ ምክንያት ለተሰጠ ብድር የያዘው መጠባበቂያ ከፍ ያለ በመሆኑ እንደሆነ ሰምተናል።
በዚህ ዓመት በርካታ የግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት አጋጥሟቸው ብድር ለማቅረብ ተቸግረው አሳልፈዋል። ባጋጠማቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ከባንክ ወደ ባንክ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውርን ከልክለዋል፣ ለሰራተኞቻቸው የሚሰጧቸውን የቤት መግዣ እና መሰል ብድሮችን አቋርጠው ቆይተዋል።
ያጋጠማቸውን የጥሬ ገንዘብ ችግርን ለማስታገስም የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ለሚያመጡላቸው ደንበኞቻቸው ከፍ ያለ ወለድን እስከማቅረብ ደርሰዋል። ደንበኞች ባልተለመደ ሁኔታ ተቀማጭ ገንዘባቸውን አብዝተው ማውጣታቸው የግል ባንኮች ለገጠማቸው የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት ዋና ምክንያት ነበር። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን በዚህ አመት ከግል ባንኮች በተለየ ሁኔታ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አልገጠመውም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ የምክትል ፕሬዝዳንቶች ሽግሽግ ማድረጉን ሰምተናል። ሽግሽጉ ከአንድ የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታ ወደ ሌላ የማዘዋወር እንጂ ከኀላፊነት ማንሳት አይደለም ተብሏል። በዚህም ባንኩ ካሉት 18 ምክትል ፕሬዝዳንቶች ውስጥ 12ቱን ከአንዱ ወደ አንዱ የስራ ክፍል ያሸጋሸገ ሲሆን ስድስቱ ባሉበት እንዲቀጥሉ አድርጓል።
ወሳኝ የሚባሉት የብድር እና ኦዲት ክፍሎች የምክትል ፕሬዝዳንቶች ሽግሽግ ከተደረገባቸው ውስጥ ናቸው። የተደረገው ሽግሽግም በጥቂት አመታት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የተደረገ ነው። ሽግሽጉ ወደ ዳይሬክተሮችም ይወርዳል ተብሏል። [ዋዜማ]