• በኢትዮጵያ በህይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ላይ መውደቁን  ኢሰመኮ አስታወቀ

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአይነቱና በይዘቱ የመጀመሪያ ባለው የሰብዓዊ መብቶች የተግባር አፈጻጸም ሪፖርት በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት በህይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ መግባቱን አስታውቋል፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላካ የመጀመሪያ ልዩ ሪፖርት እንደሆነ በኮሚሽኑ የተጠቀሰው ዘገባ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመንግስት የጸጥታ አካላትና ከመንግስት ውጭ በሆኑ የታጠቁ ቡድኖች ሰፋ ያሉ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅተ ኢትዮጵያ በጣም አሳሳቢ በሆነ የሰብዓዊ ቀውስ ውሰጥ እንደምትገኝ የገለጹት ዋና ኮምሽነር ዳንዔል በቀለ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ማንነት ተኮር ግድያዎችና ጭፍጨፋዎችን ቸኩሎ “ጅምላ ጭፍጨፋ” ብሎ የመሰየም ሁኔታ በተደጋጋሚ ቢደመጥም ኢሰመኮ እሳከሁን ባደረገው ምርማራ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በዚያ ደረጃ ለመግለጽ ተጨማሪ የምርመራ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ 

የኮሚሽኑ ሪፖርቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስፈጻሚው አካል ላይ የሚያደርገውን ክትትል የሚያግዝ መሆኑን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ሃምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ሪፖርቱን አስመልክቶ ለጋዜጠኖች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርቱ የሚሸፍነው በኢትዮጵያ የበጀት ዓመት አቆጣጠር መሰረት ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ያሉትን 12 ወራት ነው፡፡

በሪፖርቱ የሚዲያ ሰራተኞች አዲሱን የሚዲያ ህግ በጣሰ መልኩ ከህግ ውጭ በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነና ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ተግባር በተደጋጋሚ መተያት አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት በአንክሮት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡

የአገሪቱን ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚያመላክተው የኮሚሽኑ ሪፖርት በተገባደደው በጀት ዓመት የተከናወኑ የክትትል፣ የምርመራ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የዳሰሳ ጥናቶች እና ልዩ ልዩ ተግባራት የተመለከታቸውን መልካም ጅማሮዎችን፣ እንዲሁም በአፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ እና ሊሻሻሉ የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮችን የሚያካትት መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።   

 የሪፖርት ጥንቅሩ እጅግ አስከፊ የሆኑ በማለት ያመላከታቸውን የበርካታ ሰዎች ሞት፣ የአካልና ሥነልቡና ጉዳት፣ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት፣ መፈናቀልና፣ ንብረት ውድመት ጥሰቶች በመንግሥት ኃይሎችና ከመንግሥት ውጭ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎችና ቡድኖች በጦርነትና ግጭት አውድ ውስጥ የተፈጸሙ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችንም ጨምሮ በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ የተፈጸሙ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ይገኙበታል፡፡

ከ አራት ሚልየን በላይ የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሁንም ዘላቂ መፍትሔ የሚጠብቁ መሆናቸውንና የእርዳታ አቅርቦቱም ሆነ በአጠቃላይ አገራዊው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተጠለሉ ስደተኞች ሕይወት ላይም ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑም በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል  ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ወቅቶች፣ በትግራይ ክልል ተይዘው የሚገኙ መሆናቸውን የተገለጹ 15 የሚድያ ሠራተኞችን ጨምሮ 54 የሚዲያ ሠራተኞች ተይዘው ከቀናት እስከ በርካታ ወራት ለሚሆን ጊዜ በእስር መቆየታቸውን በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ አካላት ከፍርድ ውጪ ግድያ፣ እንዲሁም ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የዘፈቀደ እስር፤ የተራዘመ የቅድመ-ክስ እስር፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የህጻን ልጆች ሕገ-ወጥ እስር፤ በጋዜጠኞች፣ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ያነጣጠረ እስር እና አስገድዶ መሰወር መፈጸሙን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ በአገሪቷ የተከሰተው ጦርነት፣ ግጭት እና የተስፋፉ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች መንስዔያቸው የፖለቲካ አለመግባባትና አለመረጋጋት ውጤት ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝብ መሆኑን ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተቋረጠውን የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት እንዲያስጀምር የጠየቀ ሲሆን በተመሳሳይ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በተለያዩ ጊዜያት በአመለካከታቸው፥ በሚያራምዱት ሃሳብ እና ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለጻቸው ምክንያት በበርካታ ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሱትን ወከባ፥ ዛቻ፥ ማስፈራራት፥ እንዲሁም ዘፈቀደ እስር ድርጊት በማቆም የአመለካከት፣ እና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብቶቻቸውን እንዲያከብሩ ጠይቋል፡፡

ኢሰመኮ በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ባደረጋቸው የምርመራ ግኝቶች የተለዩትን በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶችን እንዲሁም በዓመታዊ ሪፖርት ለሚመለከታቸው ተጠሪ ሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች መፈጸማቸውን እንዲከታተል፣ ጥሰቶቹን ለማስቆም አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስድና ቁጥጥር እንዲያደርግ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አሳስቧል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]