ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሁለት ወራት በፊት የተሸከመው 40 በመቶ የተበላሽ የብድር መጠን አሁን 51.6 በመቶ (20ቢሊያን ብር) መድረሱን ዋዜማ ከባንኩ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። የባንኩ ሹማምንት ስንበት ያለ አሀዝ በመጥቃስ የማረጋጋት ስራ ለመስራት እየሞከሩ ነው። የፋይናንስ ቀውሱ ሀገሪቱ የልማት ስራዎችን ለመፈፀም ቀርቶ መደበኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን እንዳያስቆም ስጋት አለ።

ቀውሱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ  ከሰጠው ብድር ውስጥ የተበለሸውን ወይንም መመለሱ አጠራጣሪ የሆነውን እንዲሁም ባለሙያዎቹ እደሚሉት የ non performing loan ምጣነኔውን ከሰጠው ብድር አንጻር 51.6 በመቶ እንዲሆን አድርጎታል።

ባንኩ ከሰጠው 39 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ከግማሽ በላዩ ማለትም 20 ቢሊየን ብሩ በተበላሸ ብድር ውስጥ ከገባ በመንግስት የሚገባውን ትኩረት ያላገኘና ፈጣን እርምጃዎች ሊቀመጡለት እንደሚገባ  የልማት ባንኩ ምንጮቻችን ነግረውናል።

ዋዜማ ራዲዮ ከሁለት ወራት በፊት ባቀረበችው ዘገባ የልማት ባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከሰጠው ብድር 40 በመቶ መድረሱንና ይህም በገንዘብ ሲቀመጥ 14 ቢሊየን ብር እንደሚጠጋ መዘገቧ ይታወሳል።

በሁለት ወር ውስጥ ታድያ የባንኩ የተባላሸ ብድር መጠን በስድስት ቢሊየን ብር አድጓል።ከልማት ባንኩ ምንጮቻችን እንደተረዳነው በነዚህ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 45 የባንኩ ተበዳሪዎች ብድራቸውን “መክፈል ካልቻሉ”  የተበዳሪዎች መዝገብ ውስጥ  ገብተዋል።

የባንኩ ባለስልጣናት የገቡበትን ቀውስ አስመልክተው በዚህ ሳምንት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡ ሲሆን የተበላሸ የብድር መጠንን በተመለከት ከሁለት ወራት በፊት የነበረውን 40 በመቶ በመጥቀስ በቅርቡ የተደረሰበትን አዲስ የዕዳ መጠን ሳይገልፁ ቀርተዋል።

የባንኩ ከፍተኛ የስራ አመራር አባላት መስከረም 8 ቀን 2018 ባደረጉት ስብሰባ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የልማት ባንክ በወቅቱ ያልተመለሰ ብድር አሳሳቢ መሆኑንና ፈጣን እርምጃ እንደሚያስፈልገው መክረውበታል። ሆኖም እርምጃው ላይ እንደተለመደው ደንበኞች ላይ ክትትል ይደረግ ከማለት ውጭ የተለየ አቅጣጫ አልተቀመጠም።

ለባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ መጨመር  የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ዝርፊያ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተበደሩ መጥፋት ፣ በጋምቤላ ክልል ለተደራረቡ የሰፋፊ እርሻ መሬቶች ብድርን መስጠት፣ በርካታ የሰፋፊ እርሻ አልሚዎችም ተበድረው መጥፋታቸው ፣ ብድሮች አዋጭ ላልሆኑ ዘርፎች ማለትም በዝናብ ለሚለሙ እርሻዎች በገፍ መሰጠቱ ፣ ብድር አለቃቀቁም ቢሆን ከዚህ ቀደም ከብቃት ይልቅ በትውውቅና በሀገር ልጅነት ሲስጥ የነበረ መሆኑ ፣ ብድር ማስመለሻ በሚል ጨረታ የሚወጡ ፋብሪካዎች በተደጋጋሚ ማስታወቂያ እንኳ ገዥ ማጣታቸው (እዚህ ጋር ከአንድ ቢሊዮን ብር በለይ ብድር ያለበት ኤለሲ አዲስ ጨርቃ ጨርቅን መጥቀስ ይቻላል)። እነዚህ የቀጠሉ የባንኩ ነባር ችግር ሆነዋል።

በአንጻሩ የጸጥታ ችግሮች ትኩረቱን እንደያዙት የሚነገረው የጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ መንግስት ባቋቋመው የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን እንኳ ችግር ውስጥ ላለው ልማት ባንክ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ተብሎ ሲተች ይደመጣል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተሰበሰበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን የልማት ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪና መሰል ዘርፎች ብድር የሚሰጠውን ገንዘብ ለማስገኘት የግል ንግድ ባንኮች ካበደሩት ገንዘብ ከብሄራዊ ባንክ ለሚገዙት የ27 በመቶ ቦንድ የወለድ ምጣኔ ላይ ጭሬማ እንዲኖር መወሰኑ ይታወሳል።ከዚህ ቀደም የግል ንግድ ባንኮች ከሚሰጡት ብደር 27 በመቶ በሚሆነው ገንዘብ ከብሄራዊ ባንክ ቦንድ ሲገዙ ይታሰብላቸው የነበረው ወለድ ሶስት በመቶ ነው ።

ከዚህ ቀደምም ቢሆን የግል ባንኮች በአምስት በመቶ ዝቅተኛ ወለድ የደንበኞችን ገንዘብ እያስቀመጥን እንዴት በሶስት በመቶ ወለድ ቦንድ እንገዛለን የሚል ቅሬታ ነበራቸው።በ2010 ጥቅምት ወር ላይ የብር የምንዛሬ ምጣኔ በ15 በመቶ እንዲዳከም ሲደረግ ዝቀተኛ የወለድ ምጣኔ ሰባት በመቶ እንዲሆን ሲደረግ ባንኮቹ ቦንድ የሚገዙበት ወለድ ባለመሻሻሉ ቅሬታቸው ጨምሮ ነበር።

በቅርቡ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን የግል ንግድ ባንኮች ከብሄራዊ ባንክ ቦንድን ሲገዙ የሚታሰብላቸው ወለድ አምስት በመቶ ይሁንላቸው ብሏል።ይህ ማለት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዚህ በኩል ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችለው አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥልለታል ማለት ነው።ነገር ግን የባንኩን ከፍተኛ ብክነት ለማስቀረት ምንም የተቀመጠ አሰራር የለም።

ብሄራዊ ባንክ ከግል ባንኮች በቦንድ መልክ የሰበሰበው ገንዘብ 70 ቢሊየን ብር ይጠጋል።ከዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛውን ገንዘብ ልማት ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪና ሌሎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች እንዲያበድር ይሰጠዋል።የልማት ባንክ ብድር ደግሞ ካበደረው ከግማሽ በላይ የሚሆነው እየተበላሸ ነው። ልማት ባንኩ የሚሰጠውን ብድር አትርፎ ካላስመለሰ ብሄራዊ ባንክ ከግል ባንኮች ቦንድ ሽጦ የተበደረውን ገንዘብ እንዴት እየመለሰ ነው?  የሚል እያስነሳ ነው። የዋጋ ግሽበት ሰበብና ያልታቀደ የብር ህትመት ውስጥ ከሚያስገቡ ምክንያቶች ውስጥም አንዱ ይህ አይነቱ ቀውስ ነው።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዚህ አክሳሪ ጉዞው ውስጥ እንኳ የሚያበድረው ገንዘብ እንዲያገኝ የግል ባንኮች የብድር አሰጣጣቸው ተጠፍሮ ተይዞለታል።በብሄራዊ ባንክ ህግ መሰረት የግል ባንኮች አጠቃላይ ከሚሰጡት ብድር ውስጥ የረጅም ጊዜ ብድር መስጠት የሚችሉት 20 በመቶ እንኳ መድረስ አይችልም።ቀሪው ብድራቸው የግድ የአጭርና መካከለኛ ጊዜ እንዲሆን ይገደዳሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት የግል ንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድር ብዙ የሚሰጡ ከሆነ ለልማት ባንክ ገንዘብ የሚገኝበት የ27 በመቶ የቦንድ ግዥን ቶሎ ቶሎ መፈጸም አይችሉም ። በዚህ ደረጃ የገበያ መድሎ ተሰርቶለትም ልማት ባንኩ  ውጤታማ ሊሆን አልቻለም።

መሰረተ ልማቶች ላልተሟሉላቸው ባለሀብቶች የተሰጠ ብድርም የኪሳራ ምንጭ ነው።ሆኖም ለዚህም ቢሆን አዋጪነትን የመሰሉ ስራዎች እየተሰሩ ኪሳራን መቀነስ ይቻላል።ልማት ባንክ አሁንም የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አብይ የችግር ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። [ዋዜማ ራዲዮ]